በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ ሪፖርት

1. በሲቪል ሰዎች፣ ሲቪል ተቋማት እና ሌሎች ጥበቃ በሚደረግላቸው ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረስ

52. በመንግሥት ኃይሎች እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ በተፋላሚ ኃይሎች መፈጸማቸው የተዘገቡት ጥሰቶች ሆን ብሎ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደረጉ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ግድያ እና የአካል ጉዳት ማድረስን፤ በሲቪል ሰዎች እና ጥበቃ በተደረገላቸው ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረስን እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የሲቪል ሰዎች ንብረቶች ውድመትን ያካትታሉ። ኢሰመኮ ምርመራውን ባካሄደባቸው የአፋር እና አማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ብቻ በጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎች ከመለየት፣ ጥንቃቄ እና ተመጣጣኝነት መርሆዎች ውጪ በሲቪል ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎች ላይ በተፈጸሙ የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች ቢያንስ 403 ሰዎች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም በሲቪል ሰዎች ንብረቶች እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥበቃ በተደረገላቸው በጤና ተቋማት፤ በትምህርት ቤቶች፤ በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ወታደራዊ ጠቀሜታ በሌላቸው የግልና የመንግሥት ተቋማት ንብረቶች ላይ ያለልዩነት የተፈጸሙ ጥቃቶችንና የደረሱ ውድመቶችን ሰንዷል።

የሕግ ማዕቀፍ
53.ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ በጦርነት ወቅት ጦርነቱ ሊካሄድ የሚችልባቸው መሳሪያዎች እና ዘዴዎች ላይ ወሰን በማድረግ ሲቪል ሰዎችን እና የሲቪል ተቋማትን ከጥቃት ይከላከላል፤ ጥበቃ ያደርጋል። ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግጋት በሲቪል ሰዎችና ሲቪል ግዑዞች (civilian objects) ላይ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ወቅት ጉዳት ማድረስን ይከለክላሉ።

54.“መለየት” መሠረታዊ የሰብአዊነት ሕግ መርህ ሲሆን በጦርነቱ የሚካፈሉ አካላት ያለባቸውን ሲቪል ሰዎችን እና የሲቪል ግዑዞችን/ዕቃዎች ወይም ቁሳቁሶችን ከወታደራዊ ዒላማዎች የመለየት ኃላፊነትን ይመለከታል። አንድ ነገር ወታደራዊ ዒላማ ነው ተብሎ ለመወሰድ በተፈጥሮው፣ በሚገኝበት ቦታ፣ በተግባሩ እና ጥቅሙ የተነሳ ውጤታማ ወታደራዊ እርምጃ ለመፈጸም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆን እና ይህ ነገር ሙሉ ለሙሉ መውደሙ፣ መደምሰሱ፣ መያዙ ወይም ጥቅም እንዳይሰጥ መደረጉ በወቅቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ግልጽ/የማያጠራጥር ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ሆኖ መገኘት አለበት።

55. ሲቪል ሰዎች በውጊያ በቀጥታ እስካልተሳተፉ ድረስ እንዲሁም በውጊያ ሲሳተፉ የነበሩ ማናቸውም ሰዎች ቢሆኑ፤ በውጊያው መሳተፍ ካቆሙበት ወቅት ጀምሮ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ስር ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በውጊያ በቀጥታ ያልተሳተፉ ወይም መሳተፍ ያቆሙ ሰዎች ላይ ሆነ ብሎ ጥቃት መሰንዘር የጦር ወንጀል ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ወታደራዊ እና ወታደራዊ ያልሆኑ ዒላማዎችን ላይ ልዩነት ሳያደርጉ ጉዳት ማድረስን ይከለክላል።

56. ጥንቃቄ የማድረግ መርህ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ መሰረት በጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ሁሉ በሚወስዷቸው ወታደራዊ እርምጃዎች የሲቪል ሰዎች ሕይወት እና የሲቪል ግዑዞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ወይም ጉዳቱ እጅግ እንዲቀንስ የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይገልፃል።

57. በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ሌላው መሰረታዊ መርህ ተመጣጣኝነት ነው። የተመጣጣኝነት መርህ በተዋጊ ኃይሎች በወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የሚፈጽሙት ማንኛውም ጥቃት በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እንዲሁም ሲቪል ዕቃዎች ወይም ንብረቶች ላይ ከፍተኛ እና ሊገኝ ከሚችለው ወታደራዊ ጠቀሜታ አንጻር ተመጣጣኝ ያልሆነ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ጥቃቱ መፈጸም እንደሌለበት ይደነግጋል።

ከመለየት፣ ጥንቃቄ እና ተመጣጣኝነት መርህ ውጪ የተፈጸሙ ጥቃቶች
58.የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል በጋሊኮማ ቀበሌ ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ባደረሱት ጥቃት 27 ሕፃናትን ጨምሮ 107 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል። በዚሁ ጥቃት 35 ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 5 ሕፃናት ይገኙበታል። የትግራይ ኃይሎች የያሎ፣ አውራ እና ጉሊና ወረዳዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ከሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች በጦርነቱ ምክንያት ለደህንነታቸው በመስጋት ተፈናቅለው የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ሰዎች በጋሊኮማ ቀበሌ በሚገኙት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ውስጥ እንዲሁም በአካባቢው በሚገኝ ሜዳማ ስፍራ ላይ በጊዜያዊነት ተጠልለው ይገኙ ነበር። ከጋሊኮማ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ በቅርብ ርቀት (በግምት 3 ኪ.ሜ) ላይ በሚገኘው የኡፋ ተራራ ላይ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ ይገኙ ነበር።

59.የትግራይ ኃይሎች የኡፋ ተራራ ላይ ከባድ መሳሪያ መተኮሳቸውን ተከትሎ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያዎች ተራራውን በመልቀቅ በስተምስራቅ በኩል ወደሚገኘው የጋሊኮማ ተራራ አፈገፈጉ። የትግራይ ኃይሎች የጋሊኮማ ተራራን ማጥቃት ሲጀምሩ በከባድ መሳሪያ እና በተኩስ ድምጽ ተደናግጠው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙት ወናሳ ሜዳ እና ጉሊና ወንዝ በመሸሽ ላይ በነበሩ እንዲሁም በጋሊኮማ ቀበሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው በነበሩት ተፈናቃዮች እና ነዋሪዎች ላይ የትግራይ ኃይሎች በቀላል እና ከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ጥቃት ከፍተዋል። በዚህም ወደ ወናሳ ሜዳ ሲሮጡ የነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ብቻ 23 ሲቪል ሰዎች ወዲያውኑ እንደሞቱ የተጎጂ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ያስረዳሉ። አንድ ተጎጂ ስለ ሁኔታው ለኮሚሽኑ ሲገልጹ፦

የከባድ መሳሪያው ድምጽ ልክ እንደ መብረቅ ነጎድጓድ ነበር ሲተኮስም አካባቢው ላይ ብርሀን ይታይ ነበር። በከባድ መሳሪያው ድምፅ ደንግጠን ወደ ሜዳው ስንሸሽ ጥይት እንደዝናብ እላያችን ላይ ወረደብን ብለዋል።

60.በትግራይ ኃይሎች በጋሊኮማ ትምህርት ቤት ላይ የተተኮሰው ከባድ መሳሪያ ባስነሳው እሳት ምክንያት ለተፈናቃዮች በእርዳታ የመጣ ምግብ የተከማቸበት የትምህርት ቤቱ መጋዘን ውስጥ የነበሩ 8 ሲቪል ሰዎች ተቃጥለው መሞታቸውን፣ እንዲሁም በመጋዘኑ ውስጥ የነበረው የእርዳታ ምግብ ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን የዓይን እማኞች አስረድተዋል። በጥቃቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ዲግዲጋ ጤና ጣቢያ ከሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ከመጡ ሲቪል ሰዎች መካከል 68 ሰዎች (39 ወንዶች እና 29 ሴቶች) ሲሞቱ፣ ከነዚህ ውስጥ 27 ሟቾች ዕድሜያቸው ከ2-15 ዓመት የሆኑ ሕፃናት ናቸው። በተመሳሳይ 43 ሲቪል ሰዎች በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ከሐምሌ 29 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሕክምና እርዳታ የመጡ ሲሆን ከነዚህ መካከል 8 ሰዎች (6 ሴቶች እና አንድ የ9 ዓመት ሕፃንን ጨምሮ 2 ወንዶች) ሞተዋል። ከዚህም በተጨማሪ 35 ሰዎች (አምስት ሕፃናትን ጨምሮ 30 ሴቶች እና 5 ወንዶች) ከቀላል እስከ ከባድ የሆነ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

61. ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በአፋር ክልል በያሎ ወረዳ በትግራይ ኃይሎች ወደ ጎቢ-ዱራ ከተማ በተተኮሰው ከባድ መሳሪያ በመኖሪያ ቤታቸው የነበሩ 3 ሲቪል ሰዎች (አንድ የ85 ዓመት አዛውንት እና አንድ አራስ እናት ከነልጇ) መገደላቸውን የዓይን እማኞች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

62. ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሚገኘው አዲ አርቃይ ከተማ ላይ የትግራይ ኃይሎች ከባድ መሳሪያ በመተኮሳቸው የ6 ወር እና የ5 ዓመት ሕፃናትን እንዲሁም የ60 ዓመት አረጋዊን ጨምሮ 6 ሰዎች (3 ወንዶች እና 3 ሴቶች) የገደሉ መሆኑን ኮሚሽኑ ከተጎጂ ቤተሰብ እና ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።

63. ትግራይ ኃይሎች ከነሃሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በአፋር ክልል በርሀሌ ወረዳ፣ አላ ቀበሌ በሚገኙ ሶስት መንደሮች (ኩሱርቱ፣ አሰዳ እና አድአርዋ) ባደረሱት በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት 13 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል። ከነዚህም ውስጥ 12 ወንዶች እና 1 ሴት ሲሆኑ ስድስቱ ዕድሜያቸው ከ3 ወር እስከ 15 ዓመት የሆኑ ሕፃናት መሆናቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። በእነዚህ ሶስት መንደሮች በትግራይ ኃይሎች በተከፈተው ጥቃት ዕድሜያቸው ከ 10 እስከ 16 ዓመት የሆኑ 3 ሕፃናትን ጨምሮ በ6 ሲቪል ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት ደርሷል።

64. ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በትግራይ ኃይሎች የተተኮሰ ከባድ መሳሪያ አፋር ክልል በጭፍራ ወረዳ አስኮማ ቀበሌ ቡልቡላ ጃራ (ኦንዳ ጃራ) መንደር ወድቆ በፍንጣሪው አንዲት የ 10 ዓመት ሕፃን ስትሞት በአንድ የ30 ዓመት ሴት ደግሞ እግሯ ላይ የአካል ጉዳት ማድረሱን ተጎጂዎች እና ምስክሮች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። ኢሰመኮ ተጎጂዋን ባነጋገረበት ወቅት ይህንኑ ጉዳት የተመለከተ ሲሆን ከባድ መሳሪያው በወደቀበት ወቅት በአካባቢው ምንም አይነት የታጠቀ ኃይል ያልነበረ መሆኑን ገልጻለች።

65. በአማራ ክልል አጣዬ ከተማ ኅዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በትግራይ ኃይሎች በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ በከተማዋ ቀበሌ 03 ልዩ ስሙ አጣዬ አደባባይ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ 6 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም በዚሁ እለት በከተማው ልዩ ስሙ ድሬ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ 2 ሰዎችን ጨምሮ 3 ሲቪል ሰዎች በቤታቸው እያሉ በተተኮሰው ከባድ መሳሪያ መገደላቸውንና ሌሎች 2 ሲቪል ሰዎች መቁሰላቸውን፤ ከባድ መሳርያው የወደቀባቸው የሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውንና አንድ ሕንጻ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰበት ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች፣ ከምስክሮች፣ ከከተማው አስተዳደር፣ የሰነድ ማስረጃዎችና በመስክ ምልከታ በሰበሰበው መረጃ ለመረዳት ችሏል። የትግራይ ኃይሎች ወደ አጣዬ ከተማ ከመግባታቸው በፊት ከከተማው በስተሰሜን አቅጣጫ የሚገኘውን ተራራ በመቆጣጠር በመንግሥት መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ወደነበረችው አጣዬ ከተማ የከባድ መሳሪያ በተደጋጋሚ መተኮሳቸውን እና ከኅዳር 5 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የትግራይ ኃይሎች ከተማውን ተቆጣጥረው መቆየታቸውን ምስክሮች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

66. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ ከተማ ኅዳር 9 ቀን ማታ 12 ሰዓት አካባቢ በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ፍንጣሪ የቆሰለን አንድ ሲቪል ሰው ለማንሳት የሄዱ 4 የአንድ ቤተሰብ አባላትና 1 ጎረቤት (3 ወንዶችና 1 ሴት) በድጋሚ በተተኮሰ ሌላ የከባድ መሳሪያ ፍንጣሪ ሲገደሉ 6 ሲቪል ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ምስክሮች በወቅቱ የትግራይ ኃይሎች በአካባቢው እንዳልገቡና አካባቢውን የተቆጣጠሩት በማግስቱ ኅዳር 10 እንደሆነ ገልጸዋል። ኮሚሽኑ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ከባድ መሳሪያዎቹ በመከላከያ ሠራዊት እንደተተኮሱ ተገንዝቧል።

67. ኅዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ በወቅቱ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስርበነበረው በአማራ ክልል ላስታ ወረዳ ድብኮ ከተማ በተደረገ የድሮን ድብደባ፣ እንዲሁም ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 ሰዓት አካባቢ የተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ለገበያ በወጡ ሲቪል ሰዎች ላይ በማረፉ በድምሩ 5 ሲቪል ሰዎች ሲገደሉ 19 ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠንና ዓይነት ያለው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በጥቃቶቹ ከተገደሉት ሲቪል ሰዎች መካከል አንድ የ 2 ዓመት ሴት ሕፃን፣ የ80 ዓመት አረጋዊ እንዲሁም ከቆሰሉት መካከል ሁለት ሕፃናት እና የ 70 ዓመት አረጋዊ ይገኙበታል፤ ሁለት መኖሪያ ቤቶችም ወድመዋል። ኅዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የደረሰው የድሮን ድብደባ የሁለት ግለሰቦች ቤት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ባሉት ቀናቶች የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃቱ በደረሰበት ቤት እና በአካባቢው ከበሉና ከጠጡ በኋላ በአቅራቢያ ወደሚገኘው ተራራ ይሄዱ እንደነበር ሆኖም ጥቃቱ በደረሰበት ዕለት በስፍራው እንዳልነበሩ ከምስክሮች ለመረዳት ተችሏል።

68. በተመሳሳይ ሁኔታ በመርሳ ከተማ ታኅሣሥ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በተሳቢ መኪና ተሳፍረው ወደ ደሴ አቅጣጫ ለመሄድ በሚል ለጊዜው በመንገድ ላይ ቆመው በነበሩ የትግራይ ኃይሎች ላይ በመከላከያ ሠራዊት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በአካባቢው በግብይት ላይ የነበሩ 9 ሲቪል ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 9 ሲቪል ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

69.ታኅሣሥ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ወልዲያ ከተማ ቀበሌ 02 በተለምዶ ፒያሳ በተባለው አካባቢ በመከላከያ ሠራዊት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በአንድ ሕንፃ በረንዳ ላይ ሻይ ቡና፣ ምግብ፣ ውሃ የሚሸጡ በተለምዶ ‘ሱቅ በደረቴ’ በመባል የሚጠሩ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች እና አገልግሎት በመጠቀም ላይ የነበሩ 6 ሲቪል ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 4 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።36 ከሟቾች መካከል አንድ አካል ጉዳተኛ ይገኝበታል። ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ብዛት ያላቸው የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች
ምግብ እና ሻይ ቡና እየተጠቀሙ የነበረ መሆኑን በጥቃቱ ክንዳቸውና ዓይናቸው ላይ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ተጐጂ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

70.በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት በተፈጸሙ የአየር እና ድሮን ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች እና ተቋማት ላይ ጉዳቶች መድረሳቸውን ለኢሰመኮ መረጃዎች ደርሰውታል። ከእነዚህ ውስጥ የጣምራ ምርመራው ሪፖርት በሸፈነው ጊዜ ውስጥ ተከስቶ የነበረው የሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ በግምት 7፡00 ሰዓት በትግራይ ክልል ደቡብ ምስራቅ ዞን እንደርታ ወረዳ ደብረናዝሬት ጣብያ ቶጎጓ ጎጥ በሚገኘው የመገበያያ ቦታ የአየር ድብደባ የተከናወነ ሲሆን በጥቃቱ ቢያንስ 40 ሰዎች ሲሞቱ ከ 200 በላይ ሰዎች ደግሞ ቀላል እና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች እና ከሕክምና ባለሙያዎች ያገኘው መረጃ ያመላክታል። በአየር ጥቃቱ ሕፃናትን ጨምሮ በስፍራው የነበሩ ሲቪል ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም በአየር ድብደባው ምክንያት የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ የመኖርያ ቤቶች እና የንግድ ቤቶች (በስፍራው የሚኘው ብቸኛ የእህል ወፍጮ ቤትን ጨምሮ) ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።

71.ጉዳቱ በደረሰበት እለት አምቡላንሶች ከመቀሌ ከተማ ወደስፍራው እንዳይጓዙ በመከላከያ ሠራዊት በመከልከላቸው ምክንያት በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ሆስፒታሎች መውሰድ የተቻለው በቀጣይ ቀናት ነበር። በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች እንደገለጹት፣ በነበረው የፀጥታ ስጋት ምክንያት ወደ ቦታው መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ስለነበር ለተወሰነ ሰዓታት ክልከላ እንደነበር፤ ሆኖም ከረፋዱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ግን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አንቡላንሶች ወደ ስፍራው መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ቢነገራቸውም “በተባበሩት መንግሥታት አሰራር መሰረት ከረፋዱ 11፡00 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንችልም” የሚል መልስ በመስጠታቸው
አምቡላንሶቹ በዕለቱ አለመድረሳቸውን አስረድተዋል።

72.በስፍራው የነበረውን ወታደራዊ ዒላማ በሚመለከት ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ምስክሮች እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንደሚሉት በቦታው ታጣቂዎች እንዳልነበሩ እና ስፍራው የገበያ ቦታ መሆኑን ሲገልጹ፤ በአንጻሩ በወቅቱ በስፍራው የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊዎች ግን ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ የሰኔ 15 የሰማዕታት በዓልን ለማክበር በሚል የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ተሰብስበው እንደነበር፤ አካባቢውን የትግራይ ኃይሎች ለወታደራዊ ዓላማ ይጠቀሙበት እንደነበረና በጥቃቱ ሰዓት 200 የሚሆኑ ትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ተሰባስበው እንደነበር በተገኘ መረጃ መሰረት የተወሰደ እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።

73.ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ቀናት በመቀሌ ከተማ እና አካባቢው በደረሱ የአየር እና የድሮን ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች እና ሲቪል ተቋማት ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ኮሚሽኑ በልዩ ልዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ስልቶች አጣርቷል። ከነዚህም ውስጥ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በመቀሌ ከተማ መሶቦ አካባቢ በደረሰ አየር ጥቃት የ9፣ የ12 እና የ14 ዓመት ሕፃናት እረኞች ከነ ከብቶቻቸው የሞቱ ሲሆን በአንድ ሰው ላይም አካል ጉዳት ደርሷል። በተመሳሳይ ዕለት ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት ላይ መቀሌ ከተማ በሚገኘው ፕላኔት ሆቴል ላይ በደረሰ አየር ጥቃት በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በ 6 ሰዎች ላይ አካል ጉዳት ደርሷል። ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ የጎማ መጋዘን ላይ በደረሰ የአየር ድብደባ ምክንያት 2 ሰራተኞች ሲሞቱ በ7 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አሪድ ግቢ አካባቢ ከቀኑ 5፡40 ሰዓት በተደረገው የአየር ድብደባ በ11 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። ጥቅምት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 አከባቢ በመቀሌ ከተማ ላጪ በሚባል አከባቢ ባለው የከተማው መብራት ኃይል ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ (sub station) ላይ የድሮን ድብደባ የተፈጸመበት ሲሆን በድጋሚ በተፈጸመ የድሮን ድብደባ በመጀመሪያው ጥቃት የተቀሰቀሰውን እሳት በማጥፋት ላይ የነበረ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

74.በመቀሌ ከተማ በተለያዩ ቀናት በግለሰቦች ቤቶች ላይ የድሮን ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ሰዓት በመቀሌ ከተማ ሰሜን ክፍለ ከተማ 06 ቀበሌ ደረቅ ወደብ በሚባል አከባቢ በሚገኙት የግል መኖርያ ቤቶች ላይ በተፈጸመ የአየር ድብደባ 2 የ10 ዓመት ሕፃናትን ጨምሮ 6 ሰዎች ሲሞቱ በ24 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል።

75.ኮሚሽኑ ከላይ ከተዘረዘሩት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በሰበሰበው መረጃ ከጥቃቶቹ በፊት ሲቪል ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡ ምንም አይነት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እርምጃዎች እንዳልነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

ሲቪል ሰዎችን እንደ ከለላ መጠቀም
76.የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል የመቄት ወረዳን ከሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ተቆጣጥረው በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ልዩ ኃይል የመቄት ወረዳ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ ባደረጉት ጦርነት በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል። በመቄት ወረዳ ደብረዘቢጥ ቀበሌ፣ የትግራይ ኃይሎች የሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶችን ምሽግ አድርገው ሲዋጉ ከመከላከያ ሠራዊት በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ የሁለት ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል። የትግራይ ኃይሎች ከነሃሴ 12 እስከ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በደባርቅ ወረዳ፣ ቦዛ ቀጠና በሚባሉ የአዲጋግራ፣ የአብርሃም እና የአዳጋት ቀበሌዎችን ይዘው በነበረበት ወቅት፤ የአካባቢው ቀበሌዎችን የውጊያ ሜዳ፤ የአርሶ አደሮችን ቤት እንደ ምሽግ አድርገው ይጠቀሙ ነበር። በዚህ ምክንያት በ መከላከያ ሠራዊት ወደ አርሶ አደሮች ቤቶች በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች 6 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።

77. በነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ደብረዘቢጥ ቀበሌ ውስጥ በነበረ ውጊያ የነዋሪዎችን ቤት እንደምሽግ በመጠቀም ከባድ መሳሪያዎችን አጥምደው ተታኩሰዋል። በዚህ ምክንያት ከመከላከያ ሠራዊት የተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች አርሶ አደሮች ግቢዎች ላይ በመውደቃቸው የሁለት ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል። ኮሚሽኑም ከባድ መሳሪያ ያረፈባቸው ቦታዎችን ተመልክቷል። በዚሁ ቀበሌ በነሃሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የግለሰብ መኖሪያን በምሽግነት በመጠቀም ሲዋጉ የነበሩ የትግራይ ኃይሎች ላይ በመከላከያ ሠራዊት የተተኮሰ ከባድ መሳሪያ የ13 ዓመት ታዳጊ ልጅ ሕይወቱ ማለፉን እና ሌሎች 3 ሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሟች ቤተሰቦች እና ተጎጂዎች ለኢሰመኮ አስረድተዋል።

78.በአርቢት ከተማ አጤ ውኃ ሜዳ እና በከተማዋ ዙሪያ ወደ 7 ኪ.ሜ የሚረዝም የጋሸና ግንባር ተብሎ ይጠራ የነበረ ምሽግ የትግራይ ኃይሎች ሰርተው የነበረ በመሆኑ፤ የመከላከያ ሠራዊት በከተማው ላይ ተደጋጋሚ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ማድረሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በአርቢት ከተማ 017 ቀበሌ ጥቅምት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ገደማ አንድ የግለሰብ መኖሪያ በከባድ መሳሪያ በመመታቱ 3 ሕፃናትን ጨምሮ 7 ሲቪል ሰዎች ሲገደሉ ሶስት ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከባድ መሳሪያው በወደቀበት አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ምሽጎች እንደነበሩና ከባድ መሳሪያው የተተኮሰውም በወቅቱ በመንግሥት መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ከነበረው ከገረገራ
አቅጣጫ እንደነበር ከምስክሮች ለመረዳት ተችሏል። የአካባቢው አስተዳደር ለኮሚሽኑ በሰጠው መረጃ መሰረት ከሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀበሌ 032 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደረጉ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጦች እና የድሮን ድብደባ ምክንያት 45 ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፤ 25 ሲቪል ሰዎች ቆስለዋል፤ 460 መኖሪያ ቤቶችም በከባድ መሳሪያ ወድመዋል። በዚሁ ከተማ ቀበሌ 017 በተመሳሳይ ጥቃቶች 42 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ 59 ሰዎች ቆስለዋል፤ 678 መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የእርሻ ሰብልና መኖም ተቃጥሏል።

79.በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው የሃይቅ ከተማ ቀበሌ 01፣ 02 እና 05 ከጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማዋ ውስጥ በነበሩት የትግራይ ኃይሎች እና በ መከላከያ ሠራዊት መካከል በተካሄደ ከፍተኛ የከተማ ውስጥ ውጊያ በሁለቱም ኃይሎች በተተኮሱ ከባድ መሳርያዎች እና በተኩስ ልውውጥ 7 ወንድ፣ 2 ሴት እና 1 ሕፃን፣ በድምሩ 10 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውንና 5 ወንድ እና 3 ሴት፣ በድምሩ 8 ሲቪል ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም በከተማው በርካታ የመኖሪያ ቤቶች ላይ በተደጋጋሚ በመተኮሱ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች፣ የከተማው አስተዳደር እንዲሁም በምልከታ ለመረዳት ችሏል።

80.በዚሁ ከተማ ቀበሌ 05 አንድ ወጣት ልጃቸው በከባድ መሳሪያ ፍንጣሪ ከሞተባቸው ቤተሰቦች እንዲሁም ከጎረቤቶቻቸው ለመረዳት እንደተቻለው በአካባቢው ከባድ መሳሪያ ከሁለቱም ወገን ይተኮስ ነበር፣ እንዲሁም ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች የሲቪል ሰዎች ቤቶችን እንደምሽግ በመጠቀም በከተማው ላይ ከባድ ውጊያ ተካሂዷል። ወጣቱ በከባድ መሳሪያ ፍንጣሪ በሞተበት ጊዜ ከአባቱ ጋር በመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የጸጥታ ሁኔታ በአግባቡ መቅበር እንኳን ስላልተቻለ ቤተሰቦቹ በመኖሪያ ቤታቸው ሳሎን ውስጥ ለመቅበር ተገደው እንደነበር እና ከአንድ ሳምንት በኋላ አስክሬኑን አውጥተው በሙስሊም መካነመቃብር እንደቀበሩት ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። 

81.በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራ ክልል መርሳ ከተማ ነሃሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማው በመግባት በከተማው ቀበሌ 04 መኖሪያ ሰፈሮች ውስጥ ከነበሩ የትግራይ ኃይሎች ጋር ባደረጉት ውጊያ ከ30 በላይ ሲቪል ሰዎች በተባራሪ ጥይት ከመኖሪያ ቤታቸው እና መንገድ ላይ በመሸሽ ላይ ሳሉ መገደላቸውን እንዲሁም ሁለቱም ኃይሎች ከግለሰቦች መኖሪያ ግቢዎች በመግባት ቤቶችን እደከለላ ይጠቀሙ የነበረ መሆኑን ኮሚሽኑ ከምስክሮች ያገኘው መረጃ ያስረዳል። በዚሁ ዕለት በከተማው ቀበሌ 01 እና 03 ውስጥ የሚገኙ ሁለት የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች በመመታታቸው 3 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውንና 3 መቁሰላቸውን ኮሚሽኑ ከምስክሮች ያገኘው ማስረጃ ያሳያል። 

82.ታኅሣሥ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ በወልዲያ ከተማ መቻሬ በተባለው አካባቢ በመኖሪያ ቤት በራፍ ላይ ከባድ መሳርያ ወድቆ አንድ የ16 ዓመት ልጅ ተገድሏል። ጥቃቱ የተፈጸመበት መኖሪያ ቤት አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ከባድ መሳርያዎችን አስቀምጠው ወደ መንግሥት ጦር በደቡብ አቅጣጫ ሲተኩሱ የነበረ መሆኑን እና ልጃቸው የተገደለው የመንግሥት ኃይሎች ለተኩሱ በሰጡት ምላሽ መሆኑን የሟች ቤተሰቦች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። የሟች አባት
የአደጋውን አሰቃቂነት ሲገልጹ፦
“ልጄ መሞቱ ብቻ ሳይሆን አሟሟቱ እንደወጉ አለመሆኑ እጅግ ያሳዝነኛል ምክንያቱም አስከሬኑን ከባድ መሳርያው ወደመሬት ውስጥ ሰርስሮ አስገብቶትና አካሉ ተበጣጥሶ ተቆፍሮ ወጥቶ የተቀበረ በመሆኑ ልረሳው የማያስችለኝና እጅግ ዘግናኝም በመሆኑ ነው” ብለዋል።

በሰብአዊነት ሕግ ጥበቃ የተደረገላቸው ንብረቶች ላይ የደረሰ ውድመት
83.በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማው የሚገኙ የተለያዩ በሰብአዊነት ሕግ ጥበቃ የተደረገላቸው ንብረቶች እና ቦታዎች ላይ ጥቃት ደርሷል። የካሳጊታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ እና አባስ መስጂድ ላይ በተለያየ ጊዜያት በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በነበረው የተኩስ ልውውጥ እንዲሁም በከባድ መሳርያ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከዓይን እማኞችና ከመስክ ምልከታ በተሰበሰበው መረጃ ለመረዳት ተችሏል። የትግራይ ኃይሎች ካሳጊታ ከተማ በቆዩበት ጊዜ የመስጂዱ ቅጥር ግቢ እና የካሳጊታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን እንደ ወታደር ካምፕ መጠቀማቸውን እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ጀርባ ታንክ አስቀምጠው እየተኮሱ እንደነበረና የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው የአፀፋ ጥቃት ትምህርት ቤቱ እና መስጂዱ እንደተጎዱ ለመረዳት ተችሏል።

ፈንጂዎችን ያለልዩነት ጉዳት በሚያደርሱ መልኩ መጠቀም
84.የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል በወረባቡ ወረዳ ከነሃሴ 24-29 ቀን 2013 ዓ.ም በቆዩባቸው ቀናት ውስጥ በየአከባቢው የተለያዩ ዓይነት ፈንጂዎችን ቀብረው እንደሄዱ እና ይህ ምርመራ እስከተካሄደበት ጊዜ ድረስ ተቀብረው ያሉ እና ያልወጡ ፈንጂዎች መኖራቸውን ከምስክሮች እና ከአገር ሽማግሌዎች ለመረዳት ተችሏል። በወረዳው ቀበሌ 018 ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እና በእርሻ ስራ ላይ የነበሩ ሕፃናት በመስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ተቀብሮ እና ተጥሎ ያገኙትን ፈንጂ በመነካካት ላይ እያሉ በመፈንዳቱ 5 ሕፃናት (3 ሴቶች እና 2 ወንዶች) ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ 1 ሕፃን ጉዳት ደርሶባት በደሴ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገላት እንደነበር ተገልጿል። ኮሚሽኑም በአከባቢው የተቀበሩ ፈንጂዎች መኖራቸውን ተመልክቷል።

ተፅዕኖ
85.ከዚህ በላይ የተገለጹት በተለያዩ መንገዶች የተፈጸሙ ጥቃቶች ለበርካታ ሲቪል ሰዎች ሞትና የአካል ጉዳት ምክንያት በመሆናቸው የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ጥሰዋል። በተጨማሪም በርካታ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት (በተለይም የጤና እና የትምህርት ተቋማት) ፣ የኃይማኖት ተቋማት እና የግል ንብረቶችም ለወታደራዊ ዓላማ ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በተጨማሪ በተለያዩ ጥቃቶች ለጉዳትና ለውድመት ተዳርገዋል። ከነበረው ጦርነት እና ጥቃት ሕይወትን ለማትረፍ እንዲሁም በተፈጠረው የሕዝብና የመንግሥት መሠረተ-ልማቶች አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት በርካታ ሲቪል ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።

ማጠቃለያ
86.ኢሰመኮ በሰበሰበው መረጃ መሠረት በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው ሲቪል ሰዎች (በወንዶች፣ በሴቶች፣ በወጣቶች፣ በሕፃናትና ታዳጊዎች፣ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን ጨምሮ) እንዲሁም በሲቪል ሰዎች ቁሶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። ጥቃቶቹ በዓለም አቀፍ ሰብአዊነት ሕግ መሠረት የተቀመጡትን የመለየት፣ ተገቢ ጥንቃቄ የማድረግ፣ የተመጣጣኝነት፣ ሲቪል ሰዎችን እንደ ከለላ ያለመጠቀም እንዲሁም ያለልዩነት ጉዳት የሚያደርሱ ፈንጂዎች አጠቃቀም ላይ የተቀመጡ ክልከላዎችን እና መርሆዎችን በመተላለፍ የተፈጸሙ ናቸው።

87.በጦርነት ምንም ዓይነት ተሳትፎ የሌላቸው ሲቪል ሰዎች እና/ወይም የሲቪል ሰዎች ቁሶች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ወታደራዊ ጥቃት ማድረስ ከባድ የሆነ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰት ነው፤ የጦር ወንጀልንም ሊያቋቁም ይችላል። በተጨማሪም ሲቪል ሰዎችንና ቁሶችን እንደከለላ በመጠቀም ለተዘዋዋሪ ጥቃት ተጋላጭ ማድረግ እንዲሁም ይህንን ያደረገን ተፋላሚ ለማጥቃት ሲባል የሚደረግ ልየታ፣ ጥንቃቄ እና ተመጣጣኝነት መርሆዎችን ያልተከተለ ወታደራዊ እርምጃ ተመሳሳይ የተጠያቂነት እና የኃላፊነት ውጤት አለው። በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ መሠረት ፈንጅዎችን ያለልዩነት ጉዳት በሚያደርስ መልክ መጠቀምም ተመሳሳይ ተጠያቂነት እና ኃላፊነትን ያመጣል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *