በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግሥት ኃይሎች መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም አልፎ አልፎም ግጭቶች ሪፖርት መደረጋቸው እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

የነዚህ ውጥረቶች መባባስና ይህንንም የሚያጋግሉ ትርክቶች በሰሜኑ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል ብሏል ኢሰመኮ በዛሬው ዕለት ግንቦት 7፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ። በተለይም አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ሌላ ጦርነትም ሆነ ግጭት መሸከም እንደማትችል አፅንኦት ሰጥቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ግሽበት ፣ የመሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረትና ከሰሜን ኢትዮጵያ ሰፊ አካባቢዎች የሚደረጉ የምርት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸው፣ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው ሰብዓዊ ፍላጎቶችም የሃገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን በእጅጉ ጎድተውታል ብሏል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ቀጣይ ግጭት እና ጦርነት የሚያስከፍለው በዋጋ የማይገመት ነው ያለው መግለጫው ሲቪል ህዝቦችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳ እና ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ ህግ ጥሰቶችን እንደሚያስከትልም አጽንኦት ሰጥቷል። በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ለአስራ ስምንት ወራት የዘለቀው ጦርነት መቋጫ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋን ዘርቶ የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ ዳግም ጦርነት ይከሰት ይሆን የሚሉ ፍንጮች ጥያቄ ፈጥረዋል።

ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆኑት ከትግራይና ከአማራ ክልልሎች የተሰሙ መግለጫዎች እንዲሁም በድንበሮች አካባቢ አልፎ አልፎ ተከስተዋል የተባሉ ግጭቶች ናቸው። በትናንትናው ዕለት የአማራ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት ከህወሃት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ላለው “ወረራ” የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፏል። ህወሓት “በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት እያነሳሳ በአማራ ክልል ላይ ዳግም ጦርነት አውጇል” ብሏል። በዚህ ሰሞንም የትግራይ አመራሮች ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ችግሮችን በዲፕሎማሲ ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት አለመሳካቱን ጠቅሰው የትግራይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማረጋገጥ የመጨረሻ የትግል ምዕራፍ ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።

የትግራይ ክልል አመራር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል በተለያዩ የትግራይ ዞኖች ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይት የትግራይ ህዝብ ያለበት የከፋ ስቃይ እንዲገታ ነጻነቱን ለማረጋገጥ የክልሉ ህዝብ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል። ከነዚህ መግለጫዎች በተጨማሪ የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑት ራማ እና ባድመ ባሉ አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ግጭት ተካሂዷል። ኢሰመኮ እያንሰራራ ያለው ግጭት እንዲቋጭም ለሁሉም አካላት የመፍትሄ ሃሳብ ያላቸውንም ሰንዝሯል። የግጭቱ ተሳታፊዎች፣ ሃገር አቀፍ ተዋናዮች ሲቪክ ማህበራት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች አካላት ገንቢ ውይይቶችን ጨምሮ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በማደስ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምክረ ኃሳቡን ሰንዝሯል።

ለዚህም ግጭቱን ከሚያባብሱ ተግባራትና ቅስቀሳዎች እንዲሁም ከጥላቻ ንግግሮች በመቆጠብ ይልቁንም ለጋራ መግባባት፣ መቻቻል እና ሰላም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጠይቋል። በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ አለም አቀፍ አጋሮች ጦርነቱን ለመከላከል፣ ሰላም ለማስፈንና ብሄራዊ ጥረቶችን እንዲደግፉና ውይይቶችን እንዲያመቻቹ ጠይቋል። ለፌደራል መንግሥቱ ፣ እንዲሁም ለአፋር እና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ወደ ትግራይ የሚገቡ ሰብአዊ እርዳታዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ እና ባልተደናቀፈ መልኩ መሆኑን እንዲያመቻቹ ሃሳቡን ለግሷል።

በተጨማሪም የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ለሰብአዊ እርዳታ አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርጉ፣ ህዝቡ የሚፈለገውን እርዳታ እንዲያገኝ በአጎራባች ክልሎች ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚገቡባቸውን ቦታዎች ከመያዝ እንዲቆጠቡ እና ሰብአዊ እርዳታ የሚያጓጉዙ መኪኖችን እንዳይወስዱም ምክረ ሃሳብ አስቀምጧል። ኮሚሽኑ ከሳምንታት በፊት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል የተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ያለውን አስከፊ ሰብዓዊ ችግር ለመቅረቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት እና ፖለቲካዊ መፍትሄ ያመጣልም በሚል በበጎ እእንደተቀበለው አውስቷል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ የተሻሻለ የሰብዓዊ እርዳታ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ፣ በአፋር፣ በአማራና በትግራይ የሚገኙ ተጎጂዎችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እንዲሁም ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔና የፍትህ ተጠያቂነት እንዲኖር ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጌያለሁ ብሏል።

ጦርነቱ ባስከተለው ቀውስ በርካቶች በከፍተኛ ስቃይ እያለፉ፣ ኑሯቸውን የተነጠቁ፣ የሚወዷቸውን ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸውን ያጡ፣ አስፈላጊ አገልግሎቶችን የማያገኙ በርካቶች ባሉበት ሁኔታ ማገገም፣ መልሶ ማቋቋም፣ ፍትህ እና ሌሎች በርካታ ተግባራት የሚጠበቅ ነው ብሏል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል። በትግራይ 400 ሺህ ህዝብ የሚሆን በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም አስቸኳይ የምግብ እና መድኃኒት እርዳታም ይሻሉ ተብሏል። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ማወጃቸው ለሰላም በር ሊከፍት ይችላል በሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የግጭት ሁኔታዎች ማንዣበባቸው ሰላሙን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *