ሀይማኖትን ሽፋን ያደረጉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፡
በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ እና ሳንኩራ ወረዳ ሚያዝያ 20ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ ሶስት የፕሮቴስታንት እምነት አብያተክርስቲያናት እና አራት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አብያተክርስቲያናት የተቃጠሉ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱንና በርካታ የኦርቶዶክስ እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ላይ ድብደባ መፈጸሙን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ እለት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ በተደራጁ ኃይሎች የክርስቲያን ሆቴሎችን እየመረጡ እቃዎችን በመሰባበርና በማቃጠል ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ጉዳት ከደረሰባቸው ሆቴሎች መካከል ቤተሰብ ባህል ምግብ ቤት፣ መሃሪ ሆቴል፣ ሳንጆርጅ መጠጥ ቤት፣ ዳን ስማርት ክለብ እንዲሁም ፋና ሆቴል እንደሚገኙበት ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በ24/08/2014 ዓ.ም የኢድ አልፈጥር በዓል በሚከበርበት ወቅት በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በኩል ተሰብስበው በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ በተተኮሰ አስለቃሽ ጭስ ምክንያት ችግሮች መፈጠራቸውንና ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስትና በግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በተፈጠረው ግርግር ምክንያት የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ ሰዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን እና ልጆች በግርግሩ ምክንያት ከወላጆቻቸው ተለይተው ጠፍተው እንደነበር ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
ደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፡
በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል በደራሼ ልዩ ወረዳ ጊዶሌ ከተማና አካባቢው በተነሳ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣ የደራሼ ልዩወረዳ አስተዳዳሪና ካቢኔዎች እንዲሁም የጸጥታ ኀይሎች መገደላቸውን፣ በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ብዙ ሰዎች ይህንን ግጭት ተከትሎ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና በአካባቢው አሁንም የጸጥታ ችግር መኖሩን ኢሰመጉ ከአካባቢው ነዋሪዎች ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በመጨረሻም ኢሰመጉ ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች አስመልክቶ በቀጣይ ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን በማከናወን ሰፋ ያለ ዘገባን እንደሚያዘጋጅ ከወዲሁ ያሳውቃል፡፡
ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 6(1) እና 9(1) ላይ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃል-ኪዳኑ (ICCPR) የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2(1) እና 2(2) ይደነግጋል። የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት መብቱ ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 16 ላይ ማንም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው ሲል ያስቀምጣል፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 17 ማንኛውም ሰው ብቻውንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመተባበር የንብረት ባለቤት የመሆን መብት እንዳለውና ማንም ሰው በዘፈቀደ ንብረቱን እንዲያጣ እንደማይደረግ ያረጋግጣል፡፡ የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) በአንቀጽ 14 ላይ የንብረት ባለቤትነት መብት እንደሚረጋገጥ እና ሊጣስ የሚችለው ለህዝብ ፍላጎት ወይም ለህብረተሰቡ አጠቃላይ ጥቅም እና አግባብ ባላቸው ህጎች በተደነገገው መሰረት ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይኸው ቻርተር በአንቀጽ 1 ላይ በዚህ ቻርተር ውስጥ የተካተቱት ሀገሮች በቻርተሩ ውስጥ የተካተቱትን መብቶች፣ ተግባሮች እና ነፃነቶች ተገንዝበው ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ አውጭ ወይም ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 40 ሥር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንደሚከበርለት ይደነግጋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) እና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) ሁለቱም ስምምነቶች በአንቀጽ 18 ላይ ማንም ሰው የሀሳብ፣ የኅሊናና የሀይማኖት ነጻነት አለው ሲሉ ደንግገዋል፡፡ በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገመንግስት በአንቀጽ 27 ላይ ማንም ሰው የማሰብ፣ የህሊና እና የሀይማኖት ነጻነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሀይማኖት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሀይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በጋራ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል ሲል ይደነግጋል፡፡
የኢሰመጉ ጥሪ፡
- በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አብሮ የመኖር እና የመቻቻል ባህላችንን በመዘንጋት በሀይማኖት ሽፋን እየተነሱ ያሉ ግጭቶች እየተደጋገሙ እየመጡ ስለሆነ ይህ ችግር በቂ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ ችግሮች ሳፈጠሩ እና በአለመግባባቶች ምክንያት የሰዎች ህይወት ሳይጠፋ፣ አካል ሳየጎዳ እና ንብረት ሳይወድም በሰላማዊ መንገድ ለአለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አንዲቻል፣ መንግስትም ግጭቶች ተፈጥረው ጉዳቶች ከመድረሳቸው አስቀድሞ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ሃላፊነቱ እንደሆነ በማመን እንዲንቀሳቀስ፣
- በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ እና ሳንኩራ ወረዳ የተነሳው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እና በሰዎች ላይ የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት በአፋጣኝ ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ፣
- በአዲስ አበባ የኢድ አልፈጥር በዓል በተከበረበት ወቅት ለተፈጠረው ችግር መነሳት ምክንያት የሆኑ እንዲሁም የግለሰብም ሆነ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ድርጅት ንብረቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት ላይ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ጉዳት የደረሰባቸው ንብረቶች በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው እንዲደረግ፤ በተጨማሪም በመንግስት የጸጥታ አካላት የሚፈጠሩ ስህተቶች ወደፊት እንዳይፈጠሩ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ፣
- በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል በደራሼ ልዩ ወረዳ ጊዶሌ ከተማና አካባቢው ጥቃት የፈጸሙ አከላትን መንግስት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ በደቡብ ክልል መሰል ግጭቶች እና ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየደረሱ መሆኑን ኢሰመጉ በተለያዩ ጊዜዎች ባወጣቸው መግለጫዎች ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም አሁንም መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ መሰል ጥቃቶች እየደረሱ ይገኛሉ ስለሆነም የደቡብ ክልል መንግስት እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተነሱ ላሉ ግጭቶች ሁሉንም ያሳተፈ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጁ፣
- በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጎንደር ከተማ በአስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ተፈጽመው የነበሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ኢሰመጉ ሚያዚያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ የዳሰሰ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን መንግስት ተጠያቂ እንዲያደርግ እና መሰል ችግሮች በአካባቢው ወደፊት እንዳይፈጠሩ ቅድመ ጥንቃቄን እንዲያደርግ፣
- አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ብሄራዊ መዝሙርን እና ባንዲራን ተከትሎ አንዳንድ አለመግባባቶች እየተፈጠሩ መሆኑን እና ይህንን ተከትሎም የትምህርት ስርዓቱ ላይ መስተጓጎል እየተፈጠረ መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ የከፋ ችግር ሳይፈጥር መንግስት ከወዲሁ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ፣
- መንግስት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሕብረተሰቡ በአጠቃላይ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የኖረውን የመቻቻል የመከባበር እና አብሮ የመኖር ባህልን በመዘንጋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀይማኖት ሽፋን እና በታጠቁ ሀይሎች እየተነሱ ያሉ ግጭቶች እና እየደረሱ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመፍታት ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ እና መሰል ችግሮች ወደፊት እንደዳይፈጠሩ አስቀድሞ በመከላከሉ ላይ ምትክ የሌለውን ሰፊ ድርሻቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ