ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባው ህወሓት እየተካሄደ ባለው ጦርነት ልጆቻቸው ያልዘመቱ ወላጆችን እያሰረ እንደሚገኝ የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ህወሓት በበኩሉ መሰል ተግባራት ቆመዋል ይላል። ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የትግራይ ተወላጅ፣ ልጆች ለመዝመት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ወላጅ አባቱ እና አጎቱ እንደታሰሩ ገልጿል። ለራሱና ለቤተሰቡ ደኅንነት ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ወጣት፣ “ቢያንስ ከቤተሰብ አንድ ሰው ውትድርና መላክ አለበት፤ መዋጣት አለበት የሚል ሕግ አለ” ይላል። ይህ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ውጪ የሚገኘው ወጣት፣ “አባቴን ልጅህን አምጣ አሉት። ማምጣት ስላልቻለ ለአንድ ወር አሰሩት። ከዚያ ደግሞ ወንድሜን እንዲያመጣ ብለው ለቀውት ነበር። አሁን ያለበትን ሁኔታ ባላውቅም ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ ሳገኛቸው አባቴን አስረውት ነበር” በማለት ይናገራል።

ይህ ወጣት እንደሚለው አዋቂ የሆነው ወንድሙ በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት የለውም። “ወንድሜ እኮ ትልቅ ነው። ከፈለገ የአባቴን ፍቃድ ሳይጠይቅ ይሄድ ነበር። የያዙት ግን አባቴን ነው” ይላል። ልጆቻቸውን ወደ ጦር ሜዳ ባለመላካቸው አጎቱም ጭምር ለእስር መዳረጋቸውን ይህ ወጣት ይናገራል። “ከሁለት ወር በፊት አጎቴንም ሴት ልጁን አምጣ ብለው አስረውት ነበር። 18 ዓመት እንኳን አይሆናትም” ብሏል። “የደረሱ ልጆች የሉትም። በቤቱ ውስጥ ከትንንሾቹ መካከል ተለቅ ያለችው እሷ ነች። ስልክ ስለሌለ አሁን ያሉበትን ሁኔታ አላውቅም” ይላል።

ይህ ወጣት እንደሚለው ከሆነ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የትግራይ ክፍል እያስተዳደረ ያለው ህወሓት ለመዝመት ፍቃደኛ ያልሆኑ ልጆች ወላጆችን ማሰር ከመጀመሩ በፊት ሰዎችን አስገድዶ ወደ ጦር ሜዳ ይልክ ነበር ይላል። “ከዚህ በፊት በኃይል አስገድዶ የመውሰድ ተግባር ነበር። ይሄ ብዙ አላስኬድ አላቸው። ከዚያ ‘ወላጆችን ብንይዝ ይገባሉ [ወደ ትግል]’ የሚል አካሄድ መጥቷል። ይሄ በትግራይ በጣም ችግር እየሆነ ነው። እንደ ሕግ ነው የወረደው” በማለትም ያለውን ሁኔታ ያብራራል። ከዚህ ወጣት በተጨማሪ በጦርነቱ ለመዋጋት ፍላጎት ስለሌላቸው ወላጆቻቸው እንደታሰሩባቸው ከሚናገሩት መካከል በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ክብሮም በርሀ ይገኙበታል።

የባይቶና ዓባይ ትግራይ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ክብሮም በርሀ፣ ታናሽ እህታቸው ለመዝመት ፍላጎት ስለሌላት ወላጅ እናታቸው በህወሓት መታሰራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል። “እኛ ቤት ሁሉም ስደት ላይ ናቸው። ከ18 ዓመት በታች የሆነች እህቴ ብቻ አለች [በትግራይ]። እህቴ ‘ለምን ትግል አልሄደችም’ ብለው ነው እናቴ ያሰሯት” ሲሉ ተናግረዋል። ህወሓት በበኩሉ ከዚህ በፊት ልጆች ለምን አልዘመቱም በሚል ወላጆችን የማሰር ምልክቶች ቢኖሩም አሁን ላይ ግን ይህ ቆሟል ይላል። የትግራይ የውጭ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት “እንዲህ ዓይነት ነገሮች በካድሬዎች ደረጃ ምልክቶች የነበሩ ቢሆንም ወላጆችን በዚህ መንገድ የማሰር ሁኔታ የለም። ምክንያቱም ሰዎች በፈቃዳቸው ይታገላሉ” ብለዋል።

አቶ ክብሮም በርሀ ግን “ትግል መሄድ አለመሄድ የግል ምርጫ ነው፤ ወደ ትግል አልወጣህም ተብሎ ወላጅን ማሰር ግን በዓለም ታይቶ የሚታወቅ ነገር አይደለም” ይላሉ። “ወላጅ እናቴ እዚጊእምን ተክለሃይማኖት ትባላለች። በጣም ያሳዝናል። ያልጠበቅኩት ነገር ነው። የእኔ እናት ስለሆነች ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ረሀቡ፣ ችግሩ እና መደፈር ሳያንሰው አሁን ደግሞ የኔ በሚላቸው ካድሬዎች መንገላታቱ ያሳዝናል” ብለዋል። የባይቶና ዓባይ ትግራይ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው የትግራይ ተወላጆች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ፍትሕ ሳያገኙ መታሰራቸውን አውስተው “አሁንም ይህ በትግራይ ሲደገም ያሳዝናል” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ክብሮም ልጅ አልዘምትም ካለ የታመሙ ወላጆች ሳይቀሩ ለእስር እንደሚዳረጉ የገለጹ ሲሆን ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ሁኔታ ሳይኖር በርካታ ሰዎችም ትምህር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ይናገራሉ። ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገረው የትግራይ ክልል ነዋሪ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ገልጾ ከእነዚህም መካከል አንዱ ወላጆች ልጆቻቸውን ለትግል እንዲልኩ መገደዳቸው መሆኑን ይገልጻል። ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የትግራይ ክልል ነዋሪ፤ “ልጆቻችሁን አዋጡ እየተባልን ነው። መስተዳድር የለንም” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በዘለቀው የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሰራ አስከትሏል። ከትግራይ ክልል ተነስቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል። በርካቶችም ለስደት ተዳርገዋል። ሚሊዮኖችን ደግሞ ለረሃብ ከማጋለጡ ባሻገር ለመሠረተ ልማት ውድመትም ምክንያት ሆኗል። መጋቢት 15/2014 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ የተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ፣ ህወሓትም ተኩስ ለማቆም ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልን ጨምሮ ሌሎችም የተራድኦ ድርጅቶች ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እየላኩ ይገኛሉ። ሆኖም ግን በክልሉ እርዳታ ከሚሹ ዜጎች ቁጥር አንጻር ምግብ፣ መድኃኒት እንዲሁም ሌሎችም መሠረታዊ ቁሳቁሶች በበቂ ሁኔታ እየደረሱ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። በዚህ መካከል ደግሞ በትግራይ ልጆቻቸው ያልዘመቱ ወላጆች በህወሓት ለእስር እየተዳረጉ ነው የሚለው ዜና ከሳምንታት በፊት መሰማት ጀምሯል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *