ሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከበረው 1443ኛ የዒድ አልፈጥር በዓል ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ከተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ‹‹በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ›› ያላቸውን 76 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡ ግብረ ኃይሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በመስቀል አደባባይ በተለምዶ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም አጠገብ፣ ‹‹ለብጥብጥ መነሻ በማይሆን ምክንያት›› ረብሻና ሁከት አስነስተዋል የሚል ክስ አቅርቧል፡፡

በብጥብጡ ሳቢያ በፀጥታ አካላት፣ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ከትናንት በስቲያ ሚያዝያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው ግብረ ኃይሉ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሕዝበ ሙስሊሙ በተለይም በሴቶች፣ ሕፃናትና በሰላማዊ የሃይማኖቱ ተከታዮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ብርቱ ጥረትና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን ገልጿል፡፡ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው ሁከቱ የተፈጠው ‹‹ለብጥብጥ መነሻ በማይሆን ምክንያት›› መሆኑን ከገለጸ በኋላ፣ የሁከትና ግርግር መንስዔው እየተጣራ እንደሚገኝና ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች፣ ‹‹በአንዳንድ አካባቢዎች ስለታማ ነገሮችን፣ የውጭ አገር አክራሪዎችን ዓርማና የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሑፎችን በመያዝ ጥቃትና በቀል ለመፈጸም ወደ በዓሉ ሥፍራ መጥተዋል፤›› ሲል ግብረ ኃይሉ ክሱን አጠናክሯል፡፡

በመስቀል አደባባይ አካባቢ የዒድ አልፈጥር ስግደት ላይ በተፈጠረው ድርጊት እስካሁን ሕይወቱ ያለፈ ሰው ስለመኖሩ ባይገለጽም፣ ብዙዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል፡፡ በተፈጠረው ግርግር ምክንያትም ብዛት ያላቸው ወላጆችና ሕፃናት ተጠፋፍተዋል፡፡ ስለሁከቱ ቀድሞ መግለጫ ያወጣው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የዒድ ሶላት ከመሰገዱ በፊት እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው በሰማዕታት ሐውልት አካባቢ ረብሻ መነሳቱን አስታውቆ፣ ረብሻውንም ‹‹ጥቂት ግለሰቦች ባስነሱት›› ሲል ገልጾታል፡፡ በረብሻው ምክንያት በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አክሏል፡፡

በስግደት ሥርዓቱ ላይ ግጭት የተነሳበት አካባቢ ስግደቱን በማስተባበር ላይ እንደነበር ለሪፖርተር የተናገረው አቡበከር ራህመቶ፣ ግጭቱ የተነሳው ከመስቀል አደባባይ ወደ ቦሌ በሚወስደው መንገድ ላይ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም አካባቢ መሆኑን አስረድቷል፡፡ አቡበከር እንደሚገልጸው፣ እሱና አብረውት የነበሩ አስተባባሪዎች ለሴት ሙስሊሞች የስግደት ቦታነት የተዘጋጀውን የቀይ ሽብር ሙዚየም አካባቢ ሁለት ፌዴራል ፖሊሶች በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡

የግጭቱ መነሻ የሆነው ድርጊት ከጠዋቱ 3፡10 ሰዓት አካባቢ እንደተከሰተ አቡበከር አስታውሶ፣ በቦታው ላይ ከነበሩት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ውስጥ አንዱ አስለቃሽ ጭስ ወደ መሬት መጣሉን ተናግሯል፡፡ በፌዴራል ፖሊሱ ተጣለ የተባለው አስለቃሽ ጭስ በቦታው ከነበሩ ሴቶች መካከል አንዷ ዘንድ ሲደርስ ያሰማችው ጩኸት ብዙዎች ዘንድ ድንጋጤን መፍጠሩን፣ እሱና አንድ አስተባባሪ አስለቃሽ ጭሱን የጣለውን የፌዴራል ፖሊስ አባል ይዘው ማነጋገር እንደ ጀመሩ አስረድቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ አባሉ አስለቃሽ ጭሱ በስህተት እንደወደቀበት መናገሩን የገለጸው አቡበከር፣ ‹‹በስህተት ነው ቢባል እንኳን ጭሱን በፍጥነት ማንሳት ይችል ነበር፤›› በማለት ጉዳዩ በአጋጣሚ የተፈጠረ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳለው ተናግሯል፡፡ የጭሱን መታየትና የተፈጠረውን ግርግር ተከትሎ በሌላ በኩል የነበሩ ወንድ አማኞች ወደ ቦታው በመምጣታቸው፣ አስለቃሽ ጭሱን የወረወረው የፌዴራል ፖሊስ አባል ሮጦ ወደ ቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም መግባቱን ገልጿል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ ብዛት ያላቸው ሰዎች ወደ ሙዚየሙ ድንጋይ መወርወራቸውንና ደርጊቱን ሊያስቆሙ የሞከሩ አስተባባሪዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው አክሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን ኢብራሂም፣ ‹‹አስለቃሽ ጭስ ጥሏል›› ስለተባለው የፌዴራል ፖሊስ አባል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ጉዳዩ ከሃይማኖት ጋር እንደሚያያዝ በመጥቀስ በመንግሥት ከተሰጠው መግለጫ ውጪ ምንም አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡

‹‹ብዙ ሰዎች ግርግሩ በምን እንደተነሳ አያውቁም›› የሚለው የዒድ ሶላት አስተባባሪው አቡበከር፣ ብዙዎች ድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉት በዕለቱ የተፈጠረውን፣ ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ ከተከሰተው ድርጊት ጋር በማያያዝ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ጭሱ ከተወረወረም በኋላ ቢሆን ሁኔታውን ተቆጣጥሮ ስግደቱን ማስቀጠል ይቻል የነበረ ቢሆንም፣ ትክክለኛው ዕርምጃ ባለመወሰዱ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የተጀመረው የዒድ አልፈጥር በዓል ስግደት ላይ የተፈጠረው ከመስቀል አደባባይ እስከ ለገሃር ድረስ መዛመቱንና በአካባቢው የተሰበሩ መስታወቶች፣ የመኪና መንገድ ማካፈያ ብረቶችና መቀመጫዎች ናቸው፡፡ ግጭቱ በተነሳበት አካባቢ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሙዚየምና ከአጠገቡ የሚገኘው ‹‹ቡክ ወርልድ›› የመጽሐፍት መደብር መስታወቶቻቸው በሙሉ ረግፈዋል፡፡ ሙዚየሙ መግቢያ ላይ የሚገኙ ሁለት መኪኖችም መስታወቶቻቸው ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የመኪና ማቆሚያና መቀመጫዎች እንዲኖረው ተደርጎ ሰኔ 2013 ዓ.ም. የተመረቀው መስቀል አደባባይም የጉዳቱ ሰለባ ሆኗል፡፡

የአደባባዩ በሮች ላይ የሚገኙ የመስታወት ቤቶች ሲረግፉ የሲሲ ቲቪ ካሜራዎች ወድቀው ታይተዋል፡፡ አደባባዩ ዙሪያ የሚገኙ መቀመጫዎችም ተገነጣጥለዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ታደሰ፣ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ መረጃ ተጠናቅሮ ለመንግሥት መቅረቡንና ‹‹መንግሥት ቢገልጸው ይሻላል›› በሚል የጉዳት መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

ከመስቀል አደባባይ አልፎ ወደ ከለገሃር በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኙ ሕንፃዎች ውስጥ የሚገኙ ካፊቴሪያዎች፣ መደብሮች፣ ባንኮችና ቢሮዎችም መስታወቶቻቸው ተሰባብረዋል፡፡ ኦሮሚያ ባህል ማዕከል አካባቢ በሚገኘው ጌታሁን ብርቄ ሕንፃ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ ቢሮ ጉዳት ከደረሰባቸው መሀል አንዱ ነው፡፡ የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ደረጀ በቀለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከምድር ላይ የተወረወሩ ድንጋዮች በቢሮው በረንዳና ቢሮው ውስጥ የሚገኘውን መስታወት ሰባብረዋል፡፡ ከመስታወቱ ያለፉ ድንጋዮች ጠረጴዛ ላይ የነበሩ ኮምፒውተሮች ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ ፖሊሶች ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በቢሮው ላይ የደረሰውን ጉዳት ተገኝተው መመልከታቸውን የተናገሩት አቶ ደረጀ፣ በፓርቲው ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን 84 ሺሕ ብር መገመቱን አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በሙስሊሞችና የእምነት ሥፍራዎች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ፣ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ሙስሊሞች ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ በወራቤ ከተማም የእምነት ሥፍራዎች ላይ ጥቃት መድረሱ ይታወሳል፡፡ ማክሰኞ ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ያለፈውን ሳምንት፣ ‹‹በኢትዮጵያውያን መካከል የተዘረጋውን የአብሮነት ገመድ ለመበጠስ ያቀዱ ወንጀለኞች ብዙ ጥፋትን ለማድረስ በብርቱ የሞከሩበትም ወቅት ነው፤›› በማለት ገልጾታል፡፡ ኅብረተሰቡም ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባባር ወንጀለኞችን አሳልፎ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *