ማክሰኞ ሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ እጃቸው አለበት የተባሉ 280 ግለሰቦችን መንግሥት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።
ዛሬ ሐሙስ ሚያዚያ 20/2014 ዓ.ም. የፌደራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉና ሁከቱን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብሏል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በዚህ ግጭት 20 ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ ነበር። በግጭቱ ካጋጠመው የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት በተጨማሪም በመስጂዶች ላይ ውድመት መድረሱ እና የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ሀብት ንብረት መዘረፉን የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳይ ምክር ቤት አስታውቆ ነበር።
የፌደራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል በመግለጫው ጎንደር ከተማ በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተቀሰቀሰውን ግጭት መነሻ በማድረግ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብሏል። ይህ የግብረ ኃይሉ መግለጫ የተሰማው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) “ክልሉን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ የሽብር ድርጊት በሚፈጠሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን” ካሉ በኋላ ነው።
ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ ሚያዚያ 20/2014 ዓ.ም. በክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ባስላለፉት መልዕክት በጎንደር ከተማ ያጋጠመውን ክስተት አውግዘው አስተዳደራቸው ጥፋተኞች ለፍርድ እንደሚያቀርብ ቃል ገብተዋል። የደህንነት ተቋማቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ”በጎንደር የተከሰተው ግጭት በተለያዩ እምነቶች መካከል ግጭት በመቀስቀስ ወደ ሃገራዊ ቀውስ እንዲያመራ የሚደረገው ሴራ” ነው ካሉ በኋላ፤ በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሌሎች አካባቢዎችም ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ቅስቀሳዎች እና ሃሰተኛ መረጃዎችም እየተሰራጩ ይገኛሉ ብለዋል።
“በአንዳንድ አካባቢዎችም የእምነት ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግጭቱ ሃገራዊ ቅርጽ እንዲኖረው ሙከራ እየተደረገ ነው።” ሲልም አክለዋል። መግለጫው ሁከት እና ብጥብጡ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፋ በየትኛውም የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት በህግ የሚጠየቁበት አግባብ አለ ካለ በኋላ በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ ባስቸኳይ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስቧል። “ዛሬም ኢትዮጵያን ሌላ የግጭት አጀንዳ በመስጠት ለማተራመስ ሙከራ ቢደረግም በደኀንነትና በጸጥታ መዋቅሩ ከፍተኛ ጥረት በቁጥጥር ስር ውሏል” ብሏል የፌደራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ።
በጎንደር ያጋጠመው ምን ነበር?
የአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ማክሰኞ ሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም. ያጋጠመው ግጭት መነሻ ሼኽ ከማል ለጋስ ተብለው የሚጠሩ እውቅ የአገር ሸማግሌ ቀብር ወቅት በመካነ መቃብሩ ስፍራ አጠገብ ካለው ቤተ ክርስቲያን ድንጋይ ተነስቷል በሚል እንደሆነ ተናግረዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጎንደር ነዋሪ፣ የግጭቱ መነሻ ለሼኹ ቀብር የወጡ ሰዎች ከመካነ መቃብሩ አጎራባች ካለችና አዲስ ከተሠራችው ቤተ ክርስቲያን ድንጋይ ለማንሳት በመሞከራቸው ነው ይላሉ።
“ከቤተ ክርስቲያኗ ድንጋይ ሲያነሱ ለምን ታነሳላችሁ? የሚል ነው የግጭቱ መንስዔ ከዚያ በኋላም ወደ ቡድን ግጭት ተቀየረ” ይላሉ። ሐጂ ዑስማን በበኩላቸው “ይህ የተሳሳተ ነው። ቀብር ሲፈጽሙ ድንጋይ የሚያነሱት እዛው ቦታቸው ላይ ነው። ከቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥ አይደለም። በሌሎች አካላት የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና ወንጀለኞችንና አጥፊዎችን ላለመያዝና ጥፋተኞችን ወደኛ ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ነው” ብለዋል።
ሌላኛው የጎንደር ነዋሪ በበኩላቸው፣ እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ግጭት በጎንደር ተከስቶ እንደማያልቅ ተናግረው “ታላቅ አባት ሞተው በቀብር ድንጋይ ነው ግጭቱ ተነሳ የተባለው። ይህ ምክንያት አይሆንም። በመሃል የገቡ አንዳንድ ችግር ፈጣሪዎች ነበሩ” አሁን ግን በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል። ሐጂ ዑስማን በትናንትናው ዕለት የተፈጠረው ግጭት አዲስ እንዳልሆነና ላለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ።
“በሆደ ሰፊነት ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ በደብዳቤ፣ በአካልም ከሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች ጋር ሰፊ ውይይት ለማድረግ ጥረት አድርገናል” የሚሉት ሐጂ ዑስማን፣ “ነገር ግን የመንግሥት አመራሮች ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው የተፈጠረ ችግር ነው” ይላሉ። የጎንደሩን ክስተት በርካታ የሙስሊም ማሕብረሰብ አባላትን አስቆጥቷል። ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ በአንዋር መስጅድ በትናንትናው ዕለት የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።