ትናንት፣ ማክሰኞ፣ በጎንደር ከተማ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ግጭት ተቀስቅሶ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተገለጸ።

የክልሉ መንግሥት ትናንት ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ. ም. አመሻሹ ላይ ባወጣው መግለጫ በግጭቱ ሳቢያ ሰዎች እንደሞቱ፣ የአካል ጉዳት እንደደረሰ እና ንብረትም እንደወደመ ገልጿል። ነገር ግን የምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ እና ምን ያህል ንብረት እንደወደመ በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥቧል። ይኹን እንጂ በስፋት እየወጡ ያሉ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ትናንት በከተማዋ በተቀሰቀሰው ግጭት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 10 ያደርሱታል።

በመግለጫው የክልሉ መንግሥት “በተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግሥት ጥልቅ ሐዘን የተሰማው መሆኑን እየገለጽን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን እንመኛለን” ብሏል። አክሎም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማሳባሰብ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን ለመግለጽ፣ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል እና ለተጎጅዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሥራዎች መጀመሩን አስታውቋል።

ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቃል ምልልስ ያደረጉት የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፣ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ችግሩን የመቆጣጠር ሥራ እየሠራ እንደሆነና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል። “ሃይማኖትን ለማጠልሸት እና ግጭቱን ለማባባስ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ድንጋይ በመወርወር” ግጭቱን ያባባሱ አካሎች እንዳሉ ጠቁመው፣ የጸጥታ መዋቅሩ ከሃይማኖት፣ ከብሔርና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ ሰፊ ርብርብ እያደረገ እንደሆነም አክለዋል።

የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቱን በቁጥጥር ስር እንዳዋለና የክልሉ የጸጥታ ኃይል፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የጎንደር ከተማ ወጣቶች በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙም አክሏል።

የተፈጠረው ምንድን ነው?

የአማራ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፤ ግጭቱ የተከሰተው በጎንደር ከተማ ታዋቂ የነበሩት ሼኽ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር ትናንት እየተፈጸመ በነበረበት ወቅት ነው። በቀብር ስፍራው ለቀብር የሚሆን ድንጋይ በሚነሳበት ወቀት፣ የመቃብር ስፍራው አጠገብ ያለው ቤተ ክርስቲያን “ድንጋዩ የቤተ ክርስቲያኑ ድንበር ውስጥ” እንደሆነ በመግለጽ ውዝግብ መነሳቱ ተገልጿል።

የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፣ በክርስትና እንዲሁም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ግጭት ለማስነሳት በሚል “የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ድንጋይ መወርወር ተጀምሯል” ብለዋል። የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ፣ ለቀብር የሚሆን ድንጋይ “እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው” በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተጀመረ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል የአካል ጉዳትም ደርሷል። የተለያዩ ንብረቶችና ተቋማትን የማጥፋት እንቅስቃሴዎችም ተስተውለዋል ብሏል።

ክልሉ “በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሚፈጠር የሰላም መደፍረስንም ኾነ በንጹሃን ሕይወት፣ አካልና ሀብት ንብረት ላይ የሚደርስን ጥፋት የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም” በሚል አቋሙን ከገለጸ በኋላ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የሆኑ አካሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ትናንት ምሽት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ “በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሙስሊም እና ክርስቲያን ወገኖቻችንን ለማፋጀት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ሁሉም የማኅበረሰባችን ክፍል ተባብሮ ሊያስቆመው ይገባል” ብሏል።

የትናንትናውን ክስተት በተመለከተ አብን ባወጣው መግለጫ “ሕዝባችንን ማኅበራዊ እረፍት መንሳት የሚፈልጉ አካላት አጀንዳ” ብሎታል። የእስልምና ሃይማኖትና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች “አጥፊዎችን በመቆጣጠር ላይ ርብርብ እንዲያደርጉም” ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል። ትናንት ምሽት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ምሥሎችና ቪድዮዎች በጎንደር የተከሰተውን ግጭት በመቃወም በተለያዩ ስፍራዎች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን ያመላክታሉ።

ምንጭ – ቢቢሲ