ህወሓት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ለመውጣት ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ አሰራር መዘርጋትና የተቋረጡ መሰረተ ልማት አገልግሎቶች መመለስን ጨምሮ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠ።
የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል የመቆየታቸው ሁኔታ ያለውን የጸጥታ ስጋት ለማስወገድ እንደሆነ የገለጸው ህወሓት ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በመርህ ደረጃ “ከአፋር ክልል ለመውጣት ቁርጠኞች ነን” ሲሉ የህወሃት ቃለ አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ለትግራይ ህዝብ ወሳኝ የሆነው ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ አስተማማኝ መተላለፊያዎች (ኮሪደሮች) ሊኖሩ ይገባል የሚል ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ዘላቂ፣ ያልተገደበ፣ ወቅታዊ እና በቂ የሆነ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት አለበት ብሏል።
“የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጉዳይ ጥቂት የጭነት መኪናዎች ወደ ትግራይ በነዚህ ቀናት ይገባሉ በሚለው ሊወሰን አይገባም። ይልቁንም ጉዳዩ ወደ ትግራይ መደበኛ፣ በቂ እና ያልተገደበ ዕርዳታ እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር አለ የሚለው ነው” ብለዋል አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው።
አክለውም “ዕርዳታ ወደ ትግራይ የማድረስ ሁኔታ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ፍላጎት መሰረት እንዲገባና እንዲቀር የሚሆን የበጎ አድራጎት ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።” በማለት አስፍረዋል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎችም የተኩስ አቁም እንዳደረጉ አስታውቀዋል።
መንግሥት ግጭት የማቆም ውሳኔውን ባስታወቀበት መግለጫው የትግራይ ኃይሎች ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ ጠይቆ ነበር። ከሰሞኑ ህወሃት ሰራዊቱን ኢሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው የአፋር ክልል ያስወጣ ሲሆን እዚህም ውሳኔ ላይ የደረሰው ለሰብአዊነት ሲባል የተደረሰው ስምምነት ተከብሮ ያልተገደብ ሰብአዊ እርዳታ ትግራይ እንዲደርስ ነው ማለቱ ይታወሳል።
“የትግራይ መንግሥት ያለውን ጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ነው ያሉት” አቶ ጌታቸው በሶስተኛ ደረጃም ያስቀመጡት በትግራይ ያለውን “አጸያፊ እገዳ” ሲሉ የጠሩትን መነሳት ነው። ይህ እገዳ ተነስቶም አስፈላጊውው የማህበራዊ ኢኮኖሚ አገልግሎት መመለስ እንዳለበት አስፍረዋል። ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።
በመጨረሻም የነዚህ ሁኔታዎች አፈጻጸም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር እንደ የተባበሩት መንግሥታት ባሉ ገለልተኛ አለም አቀፍ አካላት ሊረጋገጥ ይገባል ብለዋል። የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት የሚገኙ ወረዳዎችን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት በጥር ወር አጋማሽ ላይ ነበር።
ከዚህ ቀደም የአፋር ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ ኻሎይታ የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን ተናግረው ነበር። በኪልበቲ ረሱ ዞን በህወሓት ቁጥጥር ሥር ገብተዋል ተብለው ከነበሩት 5 ወረዳዎች መካከል አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲ እና በራህሌ ይገኙባቸዋል። ህወሓት የአፋር ክልል አካባቢዎችን መያዙን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደነበረ የአፋር ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።
በትግራይ ኃይሎችና በመንግሥት መካከል የታወጀውን የተኩስ አቁም ተከትሎ ተከትሎ የተወሰኑ የእርዳታ ጭነት መኪኖች መግባት ቢችልም እርዳታ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መድረስ አልተቻለም ተብሏል። በትግራይ ክልል ለረጅም ጊዜ እርዳታ ተቋርጦ ስለቆየ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው የእርዳታ መጠን ቦስስት እጥፍ አድጎ፣ 300 መኪኖች በቀን እንዲገባ ከተራድኦ ድርጅቶቹ ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ከሰሞኑ ገልጿል።
በክልሉ 400 ሺህ ህዝብ የሚሆን በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም አስቸኳይ የምግብ እና መድኃኒት እርዳታም ይሻሉ ተብሏል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል። አስራ ስምንት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት መሄድ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።
ምንጭ – ቢቢሲ