ከሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ቀናት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን በአሻባሪነት በተሰየመው የኦነግ ሸኔ ኃይሎች በተቀሰቀሰ ግጭት፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የፀጥታ ኃይሎችና ንፁኃን ዜጎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ ግድም ወረዳ ሞላሌ ቀበሌ፣ በሸዋሮቢት ቀወት ወረዳ ጀጀባ ቀበሌ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ብሔረሰብ ዞን ጂሌ ጥሙጋ አካባቢዎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በዜጎች ላይ ግድያ፣ የመቁሰል አደጋና ከቤትና መኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ አድርገዋል፡፡

በተለይም በኦሮሞ ብሔረሰብ በጅሌ ጥሙጋ በኩል አልፈው በመጡት የኦነግ ሸኔና መሰል ኃይሎች የተፈጸመው ጥቃት አደገኛ እንደነበር የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ ይህን ኃይል ለመከላከል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸውን ያጡ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአካባቢው አስተዳደርና የአገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ጥረት አሁን አካባቢው ወደ ሰላም መመለሱን፣ በጥቃቱ ሥጋት ከቀዬአቸው ሸሽተው የነበሩ ዜጎችም ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን አቶ ግዛቸው አክለዋል፡፡

ለጥቃቱ መነሻ ተጨባጭ የሆነ ምክንያት አለመገኘቱንና ይልቁንም የአማራ ክልልን ከአሮሚያ ክልል ጋር ለማጋጨት የታሰበ ስለመሆኑ ያስረዱት ኃላፊው፣ ጥቃቱ በተከሰተበት የመጀመሪያ ቀናት አካባቢ መንግሥት ለማርገብ ቢሞክርም ከአቅም በላይ በመሆኑ ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከማክሰኞ ሚያዚያ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ረፋድ ጀምሮ የአካባቢው ሰላም መመለሱን፣ ቁስለኞችን ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉተን የመመለስ ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ አቶ ግዛቸው ገልጸዋል፡፡

በጥቃቱ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎች መሞታቸውን ቢናገሩም፣ የደረሰው ጉዳት አጠቃላይ አኃዛዊ መረጃ እስካሁን አለመጠናቀሩንና ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ሲረጋጋ የደረሰው አደጋ ተጣርቶ ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ሥምሪት በመሰጠቱ የሰላሙ ሁኔታ በአመዛኙ ወደ ነበረበት መመለሱንና ተዘግቶ የነበረው መንገድ ክፍት መሆኑን በመግለጽ፣ ግጭት መልሶ እንዳያገረሽ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በተጠቀሱት አካባቢዎች በመጋቢት 2013 ዓ.ም. ተመሳሳይ ግጭት ተከስቶ፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲፈናቀሉ በርካታ ዜጎች ደግሞ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *