በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን ሾኔ በተሰኘች ከተማ ለወራት ታስረው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች መፈታታቸውን ቢቢሲ ከተፈቱ ግለሰቦች ሰምቷል።
ወደ 1 ሺህ 300 የሚሆኑ እስረኞች በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ በአውቶብስ ተጭነው አዲስ አበባ መድረሳቸውን መረሳና አይናለም የተሰኙና በስፍራው ታስረው እንደነበር የገለጹ የትግራይ ተወላጆች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ለዘጠኝ ወራት ያህል ክስ ሳይመሰረትባቸውና የተጠረጠሩበት ወንጀል ሳይነገራቸው እንደቆዩ የሚናገሩት መረሳና አይናለም ሲለቀቁም ምንም መረጃ እንዳልተሰጣቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ከትናንት በስቲያ ከነበሩበት እስር ቤት ውጡ እንደተባሉና በየእያንዳንዱ አውቶብስ ሁለት ፖሊሶች ተመድቦ እንደመጡና በአዲስ አበባ ቃሊቲ እንዳወረዷቸውም መረሳ ተናግሯል። “የት እንደሚወስዱን፣ ወደ የት እንደምንሄድ አናውቅም። ብንጠይቅም፣ አናውቅም የሚል ምላሽ ተሰጠን” ሲለ መረሳ ያስረዳል። በእስር ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጆችን ቢቢሲ ከሰሞኑ ባናገራቸው ወቅት በብሔራቸው ምክንያት በቂ የምግብ፣ የውሃና የመድኃኒት አቅርቦት በሌለበት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ታስረናል ሲሉ ተናግረው ነበር።
የደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን ‘በብሔራችን ምክንያት ነው የታሰርነው’ የሚለውን ክስ ያጣጣሉ ሲሆን በክልሉ ውስጥ በተገለፀው መጠን የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን እንደማያውቁም ተናግረው ነበር። ከእስር የተፈቱት አብዛኞቹ ከአፋር ክልል ተሳፍረው ወደ ሳዑዲ የሄዱና፣ በሳዑዲ እስርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ እንግልትና ስቃይ ደርሶባቸው የመጡ ተመላሾች እንደሆኑ የሚናገረው መረሳ እስከ 12 ዓመት በእስር ተንገላትተው የመጡ እንደሚገኙበት ገልጿል።
ሌሎቹ ደግሞ ከአዲስ አበባና ከአፋር ክልል እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ይገኙበታል ብሏል። ቃሊቲ በወረዱበት ወቅት መረሳና ቤተሰብ ያላቸው ወደ የዘመዶቻቸው ቢሄዱም በርካቶች ማረፊያ እንዲሁም ብርም ስለሌላቸው መሄጃ ጠፍቶባቸው ነበር ብሏል። በስፍራው ላይ መንግሥት እንዲደጉማቸውና አቅም የለንም የሚሉ ሰዎች እንዲመዘገቡ በስፍራው ከነበሩት ባለድርሻ አካላት ጥያቄ ቢቀርብም “ነገር ግን ወደየት እንደሚወስዷቸው እርግጠኛ ስላልሆነ መመዝገብ አልፈለጉም። ወደ እስር ቤት ሊያስገቡን ይችላል” በሚልም እንዳልተመዘገቡ ተናግሯል።
በዚህ በአዲስ አበባም “ቤተሰብ፣ ስልክ እንዲሁም ለዕለት ጉርስና መጠለያም ስለሌላቸው ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው የማያጠራጥር ነው” ይላል። ከሳዑዲ ተመላሾች መካከል አንዱ የሆነው አይናለም በያዝነው ማክሰኞ ተፈትቶ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ለቢቢሲ ገልጿል። ሐምሌ ወር ላይ ከሳዑዲ ተመላሾች አንዱ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን ከሳምንት በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢው ትግራይ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመጓዝ ላይ እያለ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጿል።
“በአፋር ክልል ሎጊያ እንደገባን ተይዘን እዛም ለአንድ ወር አሰሩን። መስከረም ወር ላይ ደግሞ ወደ ደቡብ ክልል ወስደውናል” ብሏል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች ከሳዑዲ አረቢያ የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በዘፈቀደ እንደታሰሩ፣ እንግልት እንደደረሰባቸውና እንደተሰወሩም በያዝነው ዓመት ታህሳስ ወር ባወጣው ሪፖርቱ ማስታወቁ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሳዑዲ አረቢያ የመጡ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ትግራይ በሚወስዱ ኬላዎች እንዲሁም በአፋር ክልል ሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ይዘው ወደ አፋር ወይም ደቡብ ክልል በሚገኙ እስር ቤቶች አዘዋውረዋቸዋል ብሏል ድርጅቱ።
በአዲስ አበባ ስራ ላይ የነበረው መረሳም እረፍት ወስዶ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ትግራይ ሲሄድ በአፋር ክልል ሚሌ ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ያስረዳል ። በኬላው ሶስት ሌሊት ካደሩ በኋላ እሱን ጨምሮ በስፍራው የነበሩ በርካታ ሰዎች በዘጠኝ መኪና ተጭነው ወደ ደቡብ ክልል ዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የእርሻ ምርምር ማዕከል ውስጥ መወሰዳቸውንና በዚያም ለወራት መታሰራቸውን ተናግሯል። በእስር ቤቱ ሴቶችና ህፃናት የነበሩ ሲሆን በአጠቃላይ 130ዎቹ ሴቶች እንደሆኑና በእስር ቤት ቆይታቸውም ሶስት ነፍሰ ጡሮች በእስር ቤት መገላገላቸውን ያስረዳል።
ለባለፉት ዘጠኝ ወራት በከፍተኛ ስቃይ እንዳሳለፉ የሚናገረው መረሳ በርካታ ሴቶች መታመማቸውና የአዕምሮ ጤና እክል ያጋጠማቸውም እንዳሉና እጃቸውና እግራቸው ታስሮ የቆዩና የተሰቃዩም እንዳሉ ገልጿል። ” እጅግ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነበር። እስካሁን በህይወቴ ካየኋቸው የከፉ ነገሮች እሱን እዚህ ነው ያየሁ። ሰው ያለ ወንጀል ያለ ጥፋት በብሔሩ፣ በስም፣ በመታወቂያ እየተለየ መታሰር፣ መቆየትና መሰቃየቱ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው” ብሏል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ወራት ላይ የትግራይ ኃይሎች በአማራና አፋር ክልሎች ያሉ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ መታወጁ ይታወሳል።
የአስቸኳይ አዋጁንም ተከትሎ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ እስሮች መበራከታቸው ስጋት እንዳሳደረባቸው የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጠቅሰዋል። በርካቶች የሰብዓዊ መብቶች ደረጃን ባላሟሉ በተጨናነቁ ፖሊስ ጣቢያዎች መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንና ክስ እንዳልተመሰረተባቸው መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ተቋሟቱ በብሔር ላይ ያነጣጠረ ከህግ ውጭ እስር ነው ቢሉም የኢትዮጵያ መንግሥት በወንጀል ተጠርጥረው ሊታሰሩ እንደሚችሉና ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እስር እንደማይከናወን መግለጹ ይታወሳል።
ለዘጠኝ ወራት በታሰሩበት ወቅት ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና ክስም እንዳልተመሰረተባቸው የሚናገሩት እስረኞቹ ምላሽ የሚሰጥ አልነበረም ይላሉ። በአካባቢው የነበሩት ጠባቂዎች “ከዚህ ዘወር ብለህ እንዳትንቀሳቀስ እኛ ስለ ወንጀላችሁ አናውቅም አትጠይቁን” ይሏቸው እንደነበርና በተጨማሪም” የፖለቲካ ስድብ፣ ማስፈራራት እንዲሁም መሳሪያ መደገንና ድብደባ ነበር” ብሏል መረሳ። “እንደዚህ እንወጣለን ብለን አልጠበቅንም። ሊያመልጡ ብለው በፖሊስ የተመቱም አሉ፣ የሞቱም አሉ፣ አብዛኛዎቻችን ተርፈናል። ይህንን ችግር አልፎ ለዚህ በቅተናል እግዚአብሔር ይመስገን” ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ታስረው ስለሚገኙት ሰዎች ጉዳይ እየተከታተለ መሆኑን ቢቢሲ ከተቋሙ መረጃ ቢያገኝም ነገር ግን ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም። የደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን ክሱ ሐሰት ነው በማለት ባለፈው ሳምንት ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።