በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ በሚገኙ በ ጋዘር (የደቡብ አሪ ከተማ) እንዲሁም በሌጠር፣ ሺሸር፣ ሆለታ፣ በርካማማ እና ቲቲ ቀበሌዎች ውስጥ ከ 28/07/2014 ዓ.ም እስከ 01/08/2014 ዓ.ም ድረስ ቤቶችን በማቃጠል፣ ንብረት በማውደም እና ዘረፈ በመፈጸም “የአሪ ወጣት ነን” የሚሉ ሸኮን የሚባሉ የተደራጁ ቡድኖች ከፍተኛ ጉዳት እድርሰዋል፡፡ እንዲሁም ጂንካ ከተማ ላይ በ01/08/2014 ዓ.ም እነዚሁ የተደራጁ ቡድኖች በመኖሪያ ቤቶች እና በተለያዩ ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በአሁን ሰዓት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የጸጥታ ሀይል ወደ አካባቢው መግባቱን እና የማረጋጋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው የመረጃ ምንጮች ለመረዳት ችሏል፡፡ ለዚህ ክስተት መነሻ ምክንያት ተደርጎ የቀረበው የአሪ ወረዳ የዞን አደረጃጀት ጥያቄ ለደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ያቀረበ ቢሆንም ምክር ቤቱ ጥያቄውን አይቶ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አላስተላለፈም በሚል እንደሆነ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህንን ክስተት ተከትሎ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በአሁን ሰዓት እነዚህ ተፈናቃዮች በኮልታ ቤተክርስቲያን፣ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው በችግር ላይ እንደሚገኙ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡
ተያያዥ የህግ ግዴታዎች፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 6(1) እና 9(1) ላይ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃል-ኪዳኑ (ICPR) የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2(1) እና 2(2) ይደነግጋል። የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 17 ማንኛውም ሰው ብቻውንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመተባበር የንብረት ባለቤት የመሆን መብት እንዳለውና ማንም ሰው በዘፈቀደ ንብረቱን እንዲያጣ እንደማይደረግ ያረጋግጣል፡፡ የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) በአንቀጽ 14 ላይ የንብረት ባለቤትነት መብት እንደሚረጋገጥ እና ሊጣስ የሚችለው ለህዝብ ፍላጎት ወይም ለህብረተሰቡ አጠቃላይ ጥቅም እና አግባብ ባላቸው ህጎች በተደነገገው መሰረት ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይኸው ቻርተር በአንቀጽ 1 ላይ በዚህ ቻርተር ውስጥ የተካተቱት ሀገሮች በቻርተሩ ውስጥ የተካተቱትን መብቶች፣ ተግባሮች እና ነፃነቶች ተገንዝበው ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ አውጭ ወይም ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ–መንግሥት በአንቀጽ 40 ሥር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንደሚከበርለት ይደነግጋል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለመጠበቅ እና ለመደገፍ የወጣው የአፍሪካ ህብረት ኮንቬንሽን (kampala convention) በአንቀጽ 3 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ የኮንቬንሽኑ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ መፈናቀልን መከላከል እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም በአንቅጽ 3 ንኡስ አንቀጽ 1(j) ላይ መንግስት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መሰረታዊ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማሟላት እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ይሁንና እነዚህን ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ህጎች መንግስት ሊያስከብር ባለመቻሉ በዚህ መግለጫ የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡
የኢሰመጉ ጥሪ፡
- በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈጠረው ችግር በአፋጣኝ እንዲቆም፣
- በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በህይወት የመኖር መብት እና
የአካል ደህንነት መብቶችን የጣሱ፣ ቤቶች እና የተለያዩ ንብረቶችን ያወደሙ እና የዘረፉ አካላት ድርጊቱ የሰዎችን በህይወት የመኖር መብት፣ የአካል
ደህንነት መብት እና ንብረት የማፍራት መብት ከህግ አግባብ ውጪ የሚገድብ በመሆኑ ይህንን ድርጊት በፈጸሙ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ አርምጃ
እንዲወስድ፣ - የፌደራል መንግስት እንዲሁም የደቡብ ክልል መንግስት የዜጎችን በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት፣ ንብረት የማፍራት መብትን እና ያፈሩትን ንብረት
በዘፈቀደ ያለማጣት መብትን እንዲያስከብር እና እንዲያከብር፣ ለተፈናቀሉ ሰዎች መንግስት ተገቢውን ጥበቃ እና በቂ ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲያቀርብ እና - በዚህ ክስተት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ላይ ተገቢ የሆነ ህጋዊ እና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ፣
- ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክስተቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣
የሀይማኖት አባቶች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ ሲቪክ ማህበራት እና የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን እያቀረበ ወደፊት
ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን በመስራት ኢሰመጉ ሰፋ ያለ ዘገባን እንደሚያቀርብ ከወዲሁ ይገልጻል፡፡
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ