በአልበም መልክ ተሰንዶ በወይዘሮ አስቴር* ላይ የደረሰውን ጥቃት የሚያሳየውን ፎቶ ያሳዩን ባለቤታቸው አቶ ገሰሰ ናቸው።
ፎቶው ወ/ሮ አስቴር በጥይት ከተመቱበት ቅጽበት ጀምሮ በሕክምና ላይ እስከ ነበሩበት ድረስ የተወሰደ ነው። ሦስቱም ጥይቶች ያረፉት ከደረት በታች በፊት ለፊታቸው ባለው የሰውነታቸው ክፍል ነው። ፎቶው ለማየት እጅግ ሰቅጣጭ ነው። እንደምንም ከራሳችን ጋር እየታገልን ተመለከትነው። ከፊት ለፊቴ የቆሙት ሴት ያንን ተቋቁመው አሁን በእዚህ ደረጃ መቆማቸው ያስገርማል።
ኮምቦልቻ የኅዳር ወርን ያሳለፈችው በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ሆና ነው። የፌደራል ሰራዊት ድጋሚ ከተቆጣጠራት ቢያንስ አራት ወራት አልፈዋል። በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ከጦርነቱ ትውስታ ለመውጣት እየጣረች ነው። የሕዝብና የትራንስፖርት እንቅስቃሴውና የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከጦርነት በፊት የነበረችውን ደማቋን ኮምቦልቻ ለመመለስ እየጣሩ ነው።
በሰዎች አዕምሮ እና አካል ላይ የተቀረጸው የጦርነቱ ጠባሳ ግን አሁንም ከተጠቂዎቹ ጋር አብሮ እንዳለ ነው። ወይዘሮ አስቴር በእዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። ወይዘሮ አስቴር በህወሓት ወደታሮች ጥቃት የተፈጸመባቸው ኮምቦልቻን በተቆጣጠሩ በሁለተኛው/ሦስተኛው ቀን መሆኑን ያስታውሳሉ። በሕይወታቸው መጥፎ የሚባለው ጠባሳ የደረሰባቸው በጥቅምት 23/2014 ዓ.ም እንደነበር ይናገራሉ። “ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን በራችንን አንኳኩተው ‘ክፈቱ’ አሉን” የሚሉት ወይዘሮ አስቴር፣ የ11 ዓመት ልጃቸውን ይደፍሩብኛል ብለው በመስጋታቸው በር “አልከፍትም” እንዳሉ ይናገራሉ።
ወይዘሮ አስቴር ኮምቦልቻ ውስጥ መለስተኛ ሆቴል አላቸው። መኖሪያ ቤታቸው ደግሞ ከሆቴላቸው ፊት ለፊት ነው። በወቅቱ ከመኖሪያ ቤታቸው ባለቤታቸው እና የ11 ዓመት ልጃቸው ጋር ተኝተው ነበር። ሆቴል ውስጥ የሚያስተናግዱላቸው አራት ሴቶች ደግሞ እዚያው ሆቴሉ ውስጥ ነበሩ። ወይዘሮ አስቴር እንደሚሉት የህወሓት ወታደሮች የመኖሪያ በሩን ቤት እንዲከፍቱ የሚጠይቋቸው እነዚህን አስተናጋጆች ለመድፈር ነው። ወይዘሮ አስቴር ግን በእምቢታቸው ጸኑ።
“እተኩሳለሁ ሲለኝ ተኩስ እንጅ አልከፍትም” አልኩኝ ይላሉ ወይዘሮ አስቴር። ወታደሮቹ ግን አስፈራርተው ዝም አላሉም። “አከታትለው ተኮሱ። ያኔ ተመትቼ ልጄን አደራ ብዬ ወደቅኩ” የሚሉት ወይዘሮ አስቴር፣ ከእዚያ በኋላ የሆነውን አያስታውሱም። የተተኮሰው ጥይት ወ/ሮ አስቴር ላይ ብቻ አላረፈም። ሊያትርፏት ‘በር አልከፍትም’ ያሉላት የ11 ዓመት ልጃቸውም እግሯ ላይ ተመታች።

አብረው የነበሩት ባለቤታቸው አቶ ገሰሰ ጥይቱ አላገኛቸውም። የህወሓት ወታደሮች ወይዘሮ አስቴርን ከመቱ በኋላ ወደ ሆቴሉ በማምራት በሩን ገንጥለው ገቡ ይላሉ አቶ ገሰሰ*። በዚህ ጊዜ አቶ ገሰሰ በር ከፍተው ተከትለው በመሄድ ልጆቹ [የሆቴሉ አስተናጋጆች] እንዳይደፈሩ ተማጸኑ። ተማጽኗቸው አዎንታዊ መልስ አላገኘም። “እንኳን ልጆቹን ላተርፍ እኔንም በብረት ራሴን ቀጠቀጡኝ” በማለት ሁኔታውን ያስረዳሉ። “ልጆቹን ልታደጋቸው ስላልቻልኩ ባለቤቴን ለማትረፍ አማራጭ መፈለግ ነበረብኝ” በማለት ባጃጅ አስነስተው የህወሓት ወታደሮች የሕክምና ክፍል ወደ ሚገኝበት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ካምፓስ አመሩ። በባለቤታቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት ሲያስረዱ “ይዘሃት ና” የሚል መልስ አገኙ። ባጃጃቸውን ይዘው በፍጥነት ወደ ቤታቸው በመመለስ ባለቤታቸውን ለማትረፍ ተጣደፉ። ነገር ግን ቤት አልደረሱም። መንገድ ላይ ባጃጁ ተገለበጠ። እርሳቸው አልተጎዱም።
ድሮውንም ከባጃጅ ይልቅ መኪና መያዝ ይችሉ ነበር። ነገር ግን መኪናቸው ቀደም ብሎ ተወስዷል። ብቸኛ ማሳለጫ ሆና የቀረችው ባጃጃቸውም ከዳች። ቀጣዩና የመጨረሻው አማራጭ በእግር መጓዝ ነው። በእግር ወደ ጓደኛቸው ቤት በማምራት መኪና ለምነው ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ኮምቦልቻ ካምፓስ ሄዱ። አልቀናቸውም። “አሁን ባቲ አካባቢ ችግር ገጥሞን ሐኪሞቹ ወደ እዚያ ስለሄዱ ልንረዳህ አንችልም” መባላቸውን የሚገልጹት አቶ ገሰሰ፣ የባለቤታቸውን ቁስል በእጅ እና በጨርቅ ደግፈው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። አቶ ገሰሰ ከእዚህ በኋላ ነው አስቸጋሪ ውሳኔ ለመወሰን የተገደዱት።
በጦርነቱ የተነሳ ኮምቦልቻ ከተማ የሕክምና ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት አስተናግደዋል። ሰራተኞቹም የሉም። ወደ ሌላ ቦታ ሂዶ መታከምም የማይታሰብ ነው። እናም ባለቤታቸውን ለማትረፍ አቶ ገሰሰ እድላቸውን መሞከር ነበረባቸው። በሦስት ጥይት ተመትቶ የተንጠለጠለውን የባለቤታቸውን ሰውነት ያለምንም ማደንዘዣ ለመስፋት ወሰኑ። የሕክምና እውቀት ኖሯቸው ሳይሆን የመጨረሻ አማራጫቸው በመሆኑ የተንጠለጠለውን ስጋ ወደ አንድ ሰብስበው በመስፋት ቢያንስ የሚፈሰውን ደም ማስቆም እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል። አደረጉት።
ያኔ ፎቶ አንስተው በአልበም መልክ ያስቀመጡትን ፎቶ ነበር ለእኛ ያሳዩን። አቶ ገሰሰ ያለሙያዊ እገዛና በማይሆን ክር የሰፉት የባለቤታቸው ሰውነት አመረቀዘ። ወደ ሆስፒታል ወሰዷቸ፤ የህወሓት ወታደሮች ወይዘሮ አስቴርን አከሟቸው። ለአምስት ተከታታይ ቀናትም አልጋ አስይዘው ተከታተሏቸው። ነገር ግን ወይዘሮ አስቴር ጉዳታቸው ከፍተኛ ስለነበር ወደ መቀለ ሄደው ተጨማሪ ሕክምና እንዲደረግላቸው ሐኪሞቹ ነገሯቸው።
ወይዘሮ አስቴር “መትረፍ እፈልግ ስለነበር ተስማማሁ” ይላሉ። ባለቤታቸው ግን “እዚሁ ዘመድ ጋር አልቅሼ እቀብርሻለሁ እንጅ መቀለ አትሄጅም” አሉ። ባልና ሚስት በሃሳብ ባይስማሙም የአቶ ገሰሰ ሃሳብ አሸንፎ ወይዘሮ አስቴር ከአምስት ቀናት በኋላ የመቀለውን ጉዞ ሰርዘው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ የፌደራል ሠራዊት ድጋሜ ኮምቦልቻን ተቆጣጠረ። “እንዴት እንደተነሳሁ አላውቅም። ‘ጨለማው ነጋ’ ብዬ በቅጽበት ከአልጋዬ ተነስቼ ቆምኩ” በማለት “ሁለተኛ ተፈጠርኩበት” የሚሉትን ቀን ያስታውሳሉ።
ወይዘሮ አስቴር በወር 80 ሺህ ብር ይከራይ የነበረው መኪናቸው ተወስዶባቸዋል። ሆቴላቸው ወድሟል። የእርሳቸው እና የባለቤታቸው ማጌጫ 80 ግራም ወርቅም እንደተወሰደባቸው ይናገራሉ። ወይዘሮ አስቴር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኮምቦልቻን ከተቆጣጠረ በኋላ ድጋሚ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸዋል። ሕይወት እንደበፊቱ ባይሆንም ወይዘሮ አስቴር ጤናቸውን ከማስመለስ ጎን ለጎን መተዳደሪያቸው የነበረውን ሆቴላቸውንም ለማንቀሳቀስ ደፋ ቀና እያሉ ነው።
“የሄደው ሃብት ነው፣ የደረሰብን ጉዳትም አካላዊ ጉዳት ስለሆነ ይድናል፣ አዕምሯዊ ጉዳት ስላልደረሰብኝ ተመስገን እላለሁ” ይላሉ ወይዘሮ አስቴር። *የወ/ሮ አስቴር እና የባለቤታቸው ስም ለደህንነታቸው ሲባል ተቀይሯል።
ምንጭ – ቢቢሲ