የአውሮፓ ህብረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት ላቋቋመው ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሙሉ ትብብር እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠይቋል።

የአውሮፓ ህብረት ይህንን የጠየቀው በትናንትናው ዕለት ሚያዝያ 1፣ 2014 ዓ.ም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ አምነስቲና ሂውማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ ተፈፅሟል ባሉት የዘር ማፅዳት ወንጀልን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ነው። በምዕራብ ትግራይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣና ግፎችን አስመልክቶ ተቋሟቱ ያወጡት ሪፖርት የአውሮፓ ህብረትን አስደንግጦታል ብሏል- መግለጫው ገለልተኛ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪ ኮሚሽን መረጃዎችን ይፋ በማድረግ ኃላፊነትንና ተጠያቂነት በማስፈን ለተጎጂዎች ፍትህን ለማምጣት በአፋጣኝ ያስፈልጋል ብሏል።

ይህ ኮሚሽን በአገሪቱ ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥረትን የሚያጠናክርም ነው ብሏል። ” እነዚህ ምርመራዎች በአስቸኳይ እንዲጀመሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኮሚሽኑ ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲተባበር የአውሮፓ ህብረት ጥሪውን በድጋሜ ያቀርባል” ብሏል መግለጫው። ከአውሮፓ ህብረት በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥትም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ በምዕራብ ትግራይ ላይ ተፈጸሙ ያሏቸውን ጥሰቶችን አስመልክቶ ባወገዘበት መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት በተመድ የተቋቋመውን ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲተባበር ጠይቋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጡት 207 ገጽ የጋራ ምርመራ ሪፖርት በምዕራብ ትግራይ ያሉ ጊዜያዊ አስተዳደሮች፣ የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና እንደ ጦር ወንጀሎች ሊቆጠር የሚችል የዘር ማፅዳት ዘመቻ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከጦርነቱ መባቻ ጀምሮ ፈፅመዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በምላሹ ባወጣው መግለጫ ሪፖርቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል። የፌደራሉ መንግሥት ሁለቱ ተቋማት ጉዳዩን ለመመርመር የተጠቀሟቸውን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ አቅርቧል። የአውሮፓ ህብረት በአምስተኛው የተባባሩት መንግሥት ኮሚቴ ተይዞ የነበረው የአለም አቀፉ ኮሚሽን በጀት ውይይት መዘግየት እንዳሳዘነው ገልጾ ኢትዮጵያን ወደ ሰላም እርቅ እንዲመራ ለተቋቋመው ለዚህ አለም አቀፍ ሰብኣዊ ኮሚሽንም ሁሉም አገራት ገንቢ በሆነ መልኩ መሳተፍ እንዳለባቸውም በዚህ መግለጫ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ላቋቋመው አዲሱ የተመድ መርማሪ ኮሚሽን በጀት እንዳይመደብ ለጠቅላላ ጉባኤው ሃባብ አቅርባ የነበረ ቢሆንም የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ውሳኔው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ ዋጋ የሚያሳጣና ጉባኤው ያቋቋመው ሌላኛው መርማሪ ኮሚሽን ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምረው የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን አይችሉም በሚል የተዛባ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው ስትል ተችታለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በትግራይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ተቀስቅሶ በአጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልልሎች በተዛመተው የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የስደተኛ ሕጎችና ሌሎች ጥሰቶችን የሚያጣራና ገለልተኛ ምርመራ የሚያካሂድ መርማሪ ቡድን ለማቋቋም የውሳኔ ሃሳብ ያሳለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ነበር።

በአውሮፓ ሕብረት ጠያቂነት በተካሄደው በዚህ የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ በሰብዓዊ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት የሚሾሙ አባላትን የያዘ ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ለማቋቋም ውሳኔ ላይ ደርሷል። በወቀቱም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለውና አንዳንዶች የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት ሲጠቀሙበት በድጋሚ ማየቷ እንዳሳዘናት በመግለፅ በውስጥ ጉዳይዋ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን እንደማትቀበል፤ እንደማትተባበርም ገልጻ ነበር።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) በበኩሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በጦርነቱ ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች አዲስ የመርማሪ ቡድን ለማቋቋም ማቀዱ እንዳሳሰበው ለድርጅቱ በላከው ደብዳቤ ላይ መግለጹ ይታወሳል። ለዚህ ዓለም ዓቀፍ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽንም የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ፋቱ ፋቱ ቤንሱዳ ሊቀ መንበር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

ከሳቸውም በተጨማሪ ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ እና በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር በጦርነቱ ተፈፅመዋል ለተባሉ ዓለማቀፍ ወንጀሎች መርማሪ ቡድን አባላት ሆነው ተሾመዋል። የአውሮፓ ህብረት ጦርነቱ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙትን ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚያወግዝ በዚሁ መግለጫ አካትቷል።

በተጨማሪም ህብረቱ ሁሉም የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች እና የመብት ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እና የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች የተሟላ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ፣ ፈጣን እና ያልተደናቀፈ ሰብዓዊ እርዳታ በችግር ላይ ላሉ ዜጎች እንዲያመቻቹ ጠይቋል። በትናነትናውም ዕለም የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የጦርነቱ ተሳታፊዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲያቆሙ እንዲሁም ሁሉም የውጭ ሃይሎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡና እንዲሁም ክልሎች የጸጥታ ኃይሎቻቸውን ከአጎራባች ክልሎሎች እንዲያስወጡ ጠይቋል።

በዚሁ በአሜሪካ መግለጫ ጦርነቱ እንዲቆም፣ ያልተቋረጠ እና ቀጣይነት ያለው ሰብዓዊ አገልግሎት፣ በሁሉም አካላት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችና ጥሰቶች ላይ ግልጽ ምርመራ እና ለግጭቱም በውይይት ላይ እልባት እንዲያገኙለትም አሳስቧል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል። አስራ ሰባት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት መሄድ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *