በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ በሚገኘው የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ በታጣቂዎች ጥቃት እንደደረሰበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለፀ።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በምስራቅ አፍሪካ እና በግሬት ሌክስ የስደተኞች ተጠሪ ቃል አቀባይ ፌይዝ ኪሲንጋ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት ታጣቂዎቹ አዲስ በተከፈተው መጠለያ በመግባት በፈፀሙት ጥቃት ስምንት ስደተኞች በጥይት እንደተመቱ እና እንደቆሰሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች ሕክምና እንደተደረገላቸው እና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ኃላፊዋ ጨምረው ገልፀዋል። ታጣቂዎቹ በቁጥር ስድስት እንደነበሩ የገለፁት ኃላፊዋ ዓላማቸው ምን እነደነበር ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በትግራይ መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ የሚገኙትን ስደተኞች የተሻለ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ለማዘዋወር በሚል ነበር ይህንን መጠለያ ጣብያ ያቋቋመው። ከዚህ ቀደም በማይጸብሪ በሚገኙት ማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ ወደተገነባው አዲስ ጣቢያ እንደሚዘዋወሩ ተቋሙ ገልፀ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) እና የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ባለሥልጣናት ጥቃቱ በደረሰ ማግሥት በጋራ ወደ ማቆያው መሄዳቸውን እና የስደተኞቹን ደህንነት በተመለከተ ከመንግሥት ጋር መነጋገራቸውን አክለው ገልፀዋል። ጥቃቱን የፈፀሙ ታጣቂዎች ማንነት እስካሁን ድረስ ያልታወቀ ሲሆን የአካባቢው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ኃላፊዋ ጨምረው አስረድተዋል።
በትግራይ ክልል ማይጸብሪ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን ጉዳያቸውም አሳሳቢ መሆኑን ከስፍራው ወደ ዳባት መጠለያ ጣብያ የመጡ ስደተኞች ለቢቢሲ ገልፀዋል። ቃል አቀባይዋ በበኩላቸው በትግራይ ማይጸብሪ በሚገኙት ሁለት የስደተኞች መጠለያ 22 ሺህ 500 ስደተኞች መኖራቸውን ይናገራሉ። በማይጸብሪ በሚገኙት ማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን በተመለከተ ሲናገሩም “በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት። ሁኔታቸው ከጊዜ ወደጊዜ ደግሞ እየከፋ መጥቷል” ብለዋል።
አክለውም በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሰብዓዊ ረድኤት ሲባል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል። በማይ አይኒ እና አዲ ሀሩሽ መጠለያ ካምፖቹ ውስጥ የንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የምግብ እህል እጥረት መኖሩን የተጠየቁት ኃላፊዋ፣ የካቲት ወር መጨረሻ ከአካባቢው ባለስልጣናት በመነጋገር 290 ሜትሪክ ቶን እህል ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ወደ ሽረ እንዲሄድ ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።
ስደተኞቹ በጦርነት ምክንያት ለተለያዩ ጥቃቶች በመጋለጣቸው የደህንነት ዋስትና ወዳለው አካባቢ እንዲዘዋወሩ ሲጠይቁ እነደነበር ይናገራሉ። ስደተኞቹን ወደ ሌላ ስፍራ ለማጓጓዝ ደህንነቱ ተጠበቀ መስመር ሊኖር እነደሚገባ የሚናገሩት ኃላፊዋ፣ “ስደተኞቹ የሚገኙበት አካባቢ ደህንነቱ የተጠበቀ ስላልሆነ ወደሌላ ቦታ ማዘዋወር አልቻልንም፤ ስደተኞቹን ለማሸገገር ደህንነቱ የተጠበቀ መስመር እንዲኖር ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለዋል።
ጦርነቱ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሌሊት ከመቀስቀሱ በፊት 100 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያዎ፣ዓዲ ሐሩሽ፣ ማይ ዓይኒ፣ ሽመልባ እና ህጻጽ ይኖሩ ነበር። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ግን ለስደተኞቹ ጥበቃ የሚሰጣቸው አካል ስላልነበረ ከተዋጊ ኃይሎች በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች የሞትና የመቁሰል አደጋ እንዲሁም የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው የሰብአዊ ድርጅቶች ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል በኤርትራ ወታደሮች በግድ ወደ ኤርትራ የተወሰዱ መኖራቸውን በሪፖርቶቹ ላይ አመልክቷል። በትግራይ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በተለይ ከ21 ሺህ በላይ ስደተኞች ሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያ ካምፖች የነበሩ ስደተኞች የመገደል፣ ታፍኖ የመወሰድና መበታተን አደጋ እንደገጠማቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርቶች ይገልጻሉ።
ኤርትራውያኑ የአገራቸውን አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት እና አፋኝ አገዛዝን በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጥር ይሸሻሉ። በፌደራሉ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት ሲቀሰቀስ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከፍሎች ሸሽተዋል። በጠቅላላ በኢትዮጵያ ከ200 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይነገራል።
ምንጭ – ቢቢሲ