የትግራይ ተወላጆች በብሔራችን ምክንያት በደቡብ ክልል ሾኔ ተብላ በምትጠራ ከተማ ለእስር ከተዳረግን ወራቶች አለፉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ። ቢቢሲ ለደኅንነታቸው ሲባል በዚህ ዘገባ ስማቸውን የቀየረው ታሳሪዎች እንደሚሉት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ወራቶች ቢያልፍም እስካሁን ክስ እንዳልተመሰረተባቸው እና ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ተናግረዋል። ታስረው በሚገኙበት ቦታ ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዞ መገኘት አይፈቀድም የሚሉት እነዚህ እስረኞች፣ ‘ደብቀን እየተጠቀምንበት ነው’ ባሉት ስልክ ቢቢሲ አግኝቶ አናግሯቸዋል።የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ሐጎስ*፣ ለሥራ ወደ ሰመራ ከተማ እየሄደ ሳለ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደዋለ እና ከሐምሌ 12 ጀምሮ እስካሁን ሾኔ በምትባል ከተማ ውስጥ ታስሮ እንደሚገኝ ይገልፃል።

”የኮንስትራክሽን ሰራተኛ ነኝ። የአመት ዕረፍት ወስጄ ለግል ስራ ወደ ሰመራ እየሄድኩ ሳለ አውቶቡስ ውስጥ አግኝተው ያዙኝ። የኮንስራክሽን ሰራተኛ እንደሆንኩ ማስረጃዎቼን አሳየኋቸው። ግን ከነበረው ህዝብ ጋር ሰብስበው ወደ ደቡብ ክልል አመጡን” ሲል በቁጥጥር ስር ስለዋለበት ሁኔታ ለቢቢሲ ገልጿል። ሐጎስ በደቡብ ክልል፣ ሃድያ ዞን ሾኔ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ነው በሚለው ‘የእርሻ ምርምር ማእከል’ ውስጥ ታስሮ እንዳለ ይናገራል።በደቡብ ኢትዮጵያ ሃድያ ዞን ሾኔ ከተማ ውስጥ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያለፍርድ ታስረናል የሚሉት 1300 የትግራይ ተወላጆች በከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የታሰሩበት ምክንያት እንደማያውቁ እንዲሁም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ የሚናገሩት እነዚህ እስረኞች፣ በቂ የምግብ፣ የውሃና የመድሃኒት አቅርቦት በሌለበት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ መታሰራቸውን ጨምረው ገልፀዋል። የደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን ግን የቀረበውን ክስ በማጣጣል በክልሉ ውስጥ በተገለፀው መጠን የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን እንደማያውቁ ተናግረዋል። ወ/ሮ ሰናይት ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው ሊታሰሩ እንደሚችሉ ተናግረው፤ በብሄራቸው ተለይተው የታሰሩ ሰዎች ሰለመኖራቸው ግን አላውቅም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ የሚናገሩት ለምለምና በሪሁ የተባሉ የትግራይ ተወላጆች በበኩላቸው ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱ በሳምንቱ መያዛቸውንና ላለፉት ዘጠኝ ወራት ታስረው እንደሚገኙ ገልፀዋል። ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት እንደነበር የሚገልፀው በሪሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ላለፉት 9 ወራት ሾኔ ከተማ ታስሮ እንደሚገኝ ይናገራል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ የተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ እነደነበር ይታወሳል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ወራት ላይ የትግራይ ኃይሎች ወደ ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ከተሞችን በተቆጣጠሩበት ወቅት ብሄራዊ ምክርቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በርካታ ሰዎች ‘ብሄር ላይ ለተመሰረተ’ እስራት መዳረጋቸውን የሚያመላክቱ ዘገባዎች አውጥተው ነበር። ሂውማን ራይትስ ዎች ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት በከባድ ስቃይ ውስጥ ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን አስሯል፤ በኃይልም ሰውሯል ሲል ከሷል።

ተቋሙ ከሳተላይት ምስሎችና ከአይን ምስክሮች ያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ሰመራ እና በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን ውስጥ በምትገኘው ሾኔ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ በርካታ የትግራይ ተወላጆች የታሰሩባቸው ከተሞች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስፍሯል። የኢትዮጵያ መንግሥት ብሄር ላይ የተመሰረተ እስር እየፈፀመ እንደሆነ የሚገልፁ ክሶችን ሲያጣጥል ቆይቷል። የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ሕዳር ወር ላይ ለኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን በሰጡት መግለጫ በሽብርተኝነት በተፈረጁት ህወሓት እና መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ቡድን ደጋፊዎች ላይ እንጂ በትግራይ ተወላጆች ላይ እስራት እንዳልተፈፀመ ገልፀው ነበር።

ከአምስት ወራት እስራት በኋላ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም. ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባች የምትገልፀው ለምለም፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢዋ ትግራይ እየተጓዘች ሳለ የአፋር ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ ውስጥ እንደተያዘች ትገልፃለች። ”ሐምሌ 5 ወደ ትግራይ ለመግባት ሰመራ ላይ ያረፍንበት ሆቴል ውስጥ መጥተው ያዙን። ወደቤታችሁ ትሄዳላችሁ ብለው ኋላ ግን ወደዚህ (ሾኔ ከተማ) አመጡን።”

በሪሁ በበኩሉ ”ሳዑዲ አረቢያ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በላይ ታሰርን። አዲስ አበባ ገብተን ሁለት ሌሊት እንዳደርን በቀጥታ ወደ ትግራይ ጉዞ ጀመርን። እኔ ሚሌ የሚባል ኬላ ላይ ታሰርኩኝ። ምክንያቱን ምንም አላውቀውም። የፌደራል ፖሊስ አባላት ናቸው የያዙን” ይላል። በማንነታቸው ምክንያት እንደታሰሩ የሚገልፁት ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ ግለሰቦች፤ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና የታሰሩበት ምክንያት የገለፀላቸው አካል እንደሌለ ይናገራሉ። በመላው አገሪቱ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ በኋላ፤ በተለያዩ አካባቢዎች ታስረው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ከየካቲት ወር ጀምሮ በብዛት የተፈቱ ቢሆንም በዚህ በደቡብ ክልል፣ ሃድያ ዞን ሾኔ ከተማ በእስር የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ግን አለመለቀቃቸውን ይገልጻሉ።

እስር ቤቱ ውስጥ ነፍሰ ጡሮችና ህፃናት እንደሚገኙ የሚናገሩት ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ ግለሰቦች፣ በቂ የመድሃኒት አቅርቦት እንደሌለና በእስር ቤቱ ውስጥ ህይወታችው ያለፈ ሰዎች መኖራቸውንም ይናገራሉ። ”130 የሚሆኑ ሴቶች አሉ። ነፍሰጡሮች፣ አራሶችና ታማሚዎች አሉ። አስከፊ ሁኔታ ነው ያለው። በቅርብ ቀን በተስፋ መቁረጥ ሊያመልጥ የሞከረ አንድ ሰው ተገድሏል። ሁለት ሰዎች ደግሞ በህመም ሞተዋል” ይላል ሐጎስ የተባለ ታሳሪ። ከነፍሰጡሮቹ መካከል ሶስቱ እዚያው እስር ቤት ውስጥ መውለዳቸውን ሐጎስ ይናገራል።

በመካከላቸው ሳዑዲ አረቢ ውስጥ ከአምስት አመት በላይ የታሰሩ እንዳሉ የሚገልፀው ሐጎስ ”ወደሃገራቸው ሲመጡ ደግሞ ያለምንም ወንጀል ታስረዋል” ሲል ያስረዳል። ”ሻወርም ይሁን ሽንት ቤት በሰአቱ አንጠቀምም። 24 ሰዓት ተዘግቶብን ነው የምንቀመጠው። ቁርስ፣ ምሳና እራት ሰዓት ብቻ ነው የሚከፍቱልን።” በማለት በሪሁ ያሉበትን ሁኔታ ይገልፃል። ”ህፃናት ያላቸው አሉ፤ ነፍሰ ጡሮችም አሉ።” የምትለው ለምለም በበኩሏ ግቢው ውስጥ በተለይ የሴቶች ህይወት ከባድ እንደሆነ ትገልፃለች።

ሶስት ጊዜ ትፈታላችሁ ተብለው ተዘጋጅተው እንደነበር የሚናገሩት እነዚህ ታሳሪዎች አሁንም ግን በእስር እንደሚገኙ ተናግረዋል። ”ቤተሰቦቻችን የት እንዳለን አያውቁም” ከሳዑዲ አረቢያ ተመልሰው ወደ ትግራይ እየተጓዙ እንዳሉ የተያዙት ለምለምና በሪሁ ቤተሰቦቻቸው ስለእነርሱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ጠቁመዋል። ”ሳዑዲ ከሚገኙ ዘመዶቻችን ጋር እየተገናኘን ነበር። አሁን ግን ስልካችን ተወስዷል። ትግራይ ውስጥ የሚገኙት ቤተሰቦቻችን ግን የት እንዳለን አያውቁም” ትላለች ለምለም።

ቢቢሲ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ከሆኑት ኣምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊዎች ማብራርያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ታስረው ስለሚገኙት ሰዎች ጉዳይ እየተከታተለ መሆኑን ቢቢሲ ከተቋሙ መረጃ አግኝቷል። ነገር ግን ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም። የደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን ክሱ ሐሰት ነው በማለት አጣጥለውታል።

“ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ሾኔ የሚባል ካምፓስ የለውም፤ ዱራሜ የሚባል ካምፓስ ነው ያለው። ሾኔ የምትባል የከተማ አስተዳደር ግን ሃድያ ዞን ውስጥ ትገኛለች። ስለዚህ ‘ሾኔ ካምፓስ የምንገኝ እስረኞች ነን’ የሚለው መረጃ ሲጀመር ስህተት ያለው ይመስለኛል።” ይላሉ። ”ከዚህ ውጭ የትም አከባቢ ህጋዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ያደረጉ ወይም ህግ የጣሱ ሊታሰሩ ይችላሉ። ሃድያ ዞን ውስጥ ግን በዚህ ቁጥር መጠን የታሰረ የለም። በዚህ መልክ የታሰሩ ወይም እንዳልከው በብሄራቸው ተለይተው የታሰሩ እንደሌሉ ነው የማውቀው።” ሲሉ ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *