አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ጠየቁ።

ሁለቱ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ይህን የጠየቁት ዛሬ በምዕራብ ትግራይ የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ባሉበት የጋራ ሪፖርታቸው ነው። ሁለቱ ተቋማት ላለፉት 15 ወራት ያካሄዱትን ምርመራ ውጤት ተከትሎ በአካባቢው ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም በአፍሪካ ሕብረት የሚመራ ሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ተቋማቱ ረቡዕ መጋቢት 27 ይፋ ባደረጉት ሪፖርታቸው በሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶችም የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ምዕራብ ትግራይ በአስቸኳይ ማሰማራትን ያጠቃለለ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል። እንደ መብት ተሟጋቾቹ ከሆነ የሰላም አስከባሪ ኃይል በስፍራው መሰማራት፤ የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ፣ የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ እና በትግራይ አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመድረስ ቁልፍ እርምጃ ይሆናል ብለዋል። በአካባቢው ያለው ችግር ውስብስብ እና በቀላሉ የማይፈታ ስለሆነ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በሁለቱም ወገን ያሉ ሲቪሎችን ሊከላከል ይችላል ብለዋል።

“ይህ የተለመደ ወይም በቀላሉ የምንሰጠው ምክረ ሃሳብ አይደለም። ነገር ግን የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የጸጥታ ኮሚሽን የኢትዮጵያን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ተወያይቶ አያውቅም። የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም ተጨባጭ እርምጃ አልወሰደም። ይህንን ምክረ ሃሳብ የምንሰጠው የጉዳዩን አሳሳቢነት እንዲረዱት መነሻ ሃሳብ ለመስጠት ነው” ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሸናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ ተናግረዋል።

ይህ የሁለቱ ተቋማት ሪፖርት የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ወደ 60 የሚጠጉ የትግራይ ተወላጅ ወንዶችን የተከዜ ድልድይ ጋር ወስደው ረሽነዋል ይላል።

በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ፣ የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብለዋል። ሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሉት ከሆነ ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ የአማራ ኃይሎች እና ባለስልጣናት በምዕራብ ትግራይ ባሉ የትግራይ ተወላጆች ላይ ከጦር እና በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ መጠነ ሰፊ ወንጀሎች ፈጽመዋል።

የአምነስቲና የሂውማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ ላይ የዘር ማፅዳት ተፈፅሟል የሚለውን ሪፖረት በተመለከተ መግሥት ምን ይላል ሲል ቢቢሲ ለመንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የጠየቃቸው ሲሆን ሪፖርቱን እየመረመሩት እንደሆና ሲያጠናቅቁም መግለጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ ተቀሩት አጎራባች ክልሎች በተስፋፋው የእርስ በእስር ጦርነት ሁሉም ተሳታፊ አካላት በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲጠየቁ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት፣ የትግራይ ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች በሲቪሎች ላይ የመብት ጥሰት በመፈጸም ተጠያቂ ሲደረጉ ቆይተዋል። አምነስቲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባወጣው ሪፖርት ላይ የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ገብተው በቆዩባቸው ጊዜያት ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ በሲቪሎች ላይ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ይፋ አደርጎ ነበር።

ሁለቱ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ዛሬ ይፋ ያደረጉት እና ” ‘ከዚህ ምድር እናስወግዳችኋለን’፡ በሰብዓዊነት የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት በኢትዮጵያዋ ምዕራብ ትግራይ ዞን” የተሰኘው ሪፖርት የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ምዕራብ ትግራይ የሚንቀሳቀሱ የአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም ሚሊሻዎች “የዘር ማጽዳት እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን” መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ግኝቶችን ይዟል።

“የኢትዮጵያ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች በምዕራብ ትግራይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችን ክብደት ለማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል” ሲሉ የአምነስቲ ዋና ጸሃፊ አግነስ ካላማርድ ወቅሰዋል። “የሚመለከታቸው መንግሥታት እየተካሄደ ያለው የዘር ማጽዳት ዘመቻን ማስቆም ብሎም ከአካባቢው የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን በፈቃዳቸው እና ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ማስቻል አለባቸው” ሲሉ ዋና ጸሃፊዋ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ፍትህ ለተበዳዮች እንዲሰጥ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ሪፖርቱ በጦርነቱ የመጀመሪያ ጥቂት ወራት ውስጥ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ጭምር የዳሰሰ ሲሆን የትግራይ ሚሊሻዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪ ሲቪሎች በማይካድራ ከተማ አካባቢው ነዋሪ በሆኑ እና ለቀን ስራ በመጡ የአማራ ተወላጆች ላይ “የጦር ወንጀሎችን” መፈጸማቸውን አስታውሷል። ተቋማቱ በዝርዝር ካጠኗቸው ልዩ ክስተቶች መካከል በተከዜ ድልድይ አካባቢ በጥር ወር 2013 ፋኖ በመባል በሚጠራው ሚሊሻ ተፈጽሟል ሲሉ የገለጹት ጭፍጨፋ ይገኝበታል።

ጥር 9 አዲ ጎሹ ተብላ በምትጠራው አነስተኛ ከተማ የፋኖ ሚሊሻዎች ነዋሪዎችን ከሰበሰቡ በኋላ ወንዶቹን በመምረጥ አስረዋል ያለው ሪፖርቱ፤ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በበኩላቸው 60 የሚጠጉ የትግራይ ተወላጅ ወንዶችን የተከዜ ድልድይ ጋር ወስደው ረሽነዋል ይላል። “መንግሥት በምዕራብ ትግራይ ጥቃት የሚፈጽሙ የሚሊሺያ አደረጃጀቶችን ሊያፈርስ እንዲሁም ጥቃት የፈጸሙ አማራ ልዩ ኃይል እና የፌደራል ሃይሎች አባላትን ሊያስወጣ ይገባል” ሲሉ ተቋማቱ በሪፖርታቸው አሳስበዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *