የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ማረሚያ ቤት ተወካይን ጨምሮ ሶስት የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ በታጣቂዎች መታገታቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። እገታውን የፈጸሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው የሚል ግምት እንዳለ የኮሚሽኑ ምክትል ኃላፊ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በማረሚያ ቤት ፖሊሶቹ ላይ እገታው የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ አካባቢ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መጋቢት 22፤ 2014 መሆኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ምስጋናው እንጅፋታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ፖሊሶቹ በታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱት፤ ከአሶሳ ከተማ ወደ ካማሺ ዞን በህዝብ ማመለሻ አውቶብስ ተሳፍረው በመመለስ ላይ እንዳሉ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ምስጋናው አስታውቀዋል።

እገታው በተፈጸመበት ዕለት እኩለ ቀን ገደማ፤ ታጣቂዎች የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሱን በመንገድ ላይ ካስቆሙ በኋላ በተሸከርካሪው ውስጥ ከነበሩ ተሳፋሪዎች መካከል ሶስቱን የማረሚያ ቤት ሰራተኞች ብቻ ለይተው መውሰዳቸውን ከዓይን እማኞች መረዳታቸውን የፖሊስ ኃላፊው ተናግረዋል። በታጣቂዎቹ ተመርጠው ወዳልታወቀ ቦታ የተወሰዱት ፖሊሶች፤ የካማሺ ዞን ማረሚያ ቤቱ አዛዥ ተወካይ ኮማንደር ጉተማ ደላላ እንዲሁም የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች ኮማንደር አብዱራሂም ዑመር እና ኢንስፔክተር በካ ጊቼሌ መሆናቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ሶስቱ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ በተጓዙበት ወቅት በጸጥታ ኃይሎች ታጅበው እንደነበር የሚያስታውሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በመልስ ጉዟቸው ግን “ለማንም ሳያሳውቁ በራሳቸው ጊዜ” የህዝብ ትራንስፖርት መጠቀማቸውን አስረድተዋል። “ያለ እጀባ መሄዳቸውን እኛም እንደ ስህተት ነው የምንወስደው” ሲሉም የፖሊሶቹ የመልስ ጉዞ በተለመደው መልኩ በጸጥታ ኃይሎች አጀብ መከናወን እንደነበረበት አብራርተዋል።

የአጋቾቹን ማንነት በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ኮሚሽነር ምስጋናው፤ “እሱን እርግጠኛ መሆን አንችልም። [ነገር ግን] እዚያ አካባቢ በስፋት የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ ነው። እርሱ ይሆናል የሚል ግምት አለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሁለት የካማሺ ዞን ነዋሪዎችም፤ በአካባቢው የ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል። የኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ ያለውን ሁኔታም “በጣም ስጋት ያለበት” ሲሉ ገልጸውታል።

ሶስቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፖሊሶች ያገቷቸው “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” የሚለውን ግምት ታሳቢ በማድረግ፤ የክልሉ መንግስት ታጋቾቹን በሽምግልና ለማስለቀቅ ጥረት እያደረገ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ምስጋናው ተናግረዋል። “እስከ ትላንት ማታ ድረስ ታጋቾቹ ደህና መሆናቸውን አረጋግጠናል” የሚሉት ኮሚሽነር ምስጋናው፤ ታጋቾቹ ለቤተሰቦቻቸው ስልክ ደውለው “በህይወት አለን አትስጉ” ማለታቸውን እንደሰሙም አመልክተዋል። “የት እንዳሉ፣ ለምን ምክንያት እንደታገቱ ግልጽ የሆነ ነገር የለም። በህይወት እንዳሉ ብቻ ነው መረጃ ያለን” ሲሉም አክለዋል።

ሶስቱ ፖሊሶች ታግተው የሚገኙበት ቦታ በትክክል የት እንደሆነ ባይታወቅም፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን” እገታው ወደ ተፈጸመበት የምዕራብ ወለጋ ዞን ለመላክ ጥረት እያደረገ መሆኑን የፖሊስ ኃላፊው አስታውቀዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ የሚመረጡት እገታው ከተፈጸመበት ምዕራብ ወለጋ ጋር ከሚዋሰነው የካማሺ ዞን እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከኃይል ይልቅ ሽምግልናን መጠቀም የመረጠው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በካማሺ ዞን ከታጣቂዎች ጋር የፈጸመውን እርቅ ላለማሰናከል ነው። “ጉዳት ከደረሰ ሰላሙ እንዳይቀጥል ለሚፈልጉ አካላት ምቹ ሁኔታ ነው የሚፈጥረው” ሲሉ ኮሚሽነር ምስጋናው ከውሳኔው ጀርባ ያለውን ምክንያት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

የካማሺ ዞን፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግድያ፣ መፈናቀል፣ እና የታጣቂዎች ጥቃት በተደጋጋሚ ከሚከሰቱባቸው አካባቢዎች መካከል አንደኛው ነው። በዞኑ ለሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና ግጭቶች፤ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ታጣቂዎችን ተጠያቂ ሲያደርግ ሲያደርግ የቆየው የክልሉ መንግስት ከአንድ ሁለት ጊዜ ከአማጽያኑ ጋር እርቅ አድርጓል። የክልሉ መንግስት ከጉህዴን ታጣቂዎች ጋር የፈጸመው የመጨረሻው እርቅ የተካሄደው ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት መጋቢት 10፤ 2014 ነው።

ምንጭ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *