በአማራ ክልል በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች ትላንት ማክሰኞ ባደረሱት ጥቃት ለጊዜው ቁጥራቸው በወል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦሰት እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ከትላንትና ከሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪዎች ዝግ ሆኖ የነበረው ከመተሐራ ወደ ወለንጪቲ የሚወስደው መንገድ ዛሬ ረፋዱን አገልግሎት መስጠት መቀጠሉን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

የትላንትናው ጥቃት የተፈጸመው ከፈንታሌ ወረዳ ጋር በሚዋሰነው የአሞራ ቤት ቀበሌ እንደሆነ የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አስተዳዳሪ አስረድተዋል። አቶ ታደሰ “በቡድን የተደራጁ እና በከባድ መሳሪያ የታገዙ” ሲሉ በጠሯቸው ታጣቂዎች ሰነዘሩት ባሉት ጥቃት የሰው ህይወት እንዳለፈ እና ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦችም እንዳሉ ተናግረዋል።

በጥቃቱ ከተጎዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ውስጥ የተወሰኑት በምንጃር አረርቲ ከተማ በአረርቲ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አመልክተዋል። ቀሪዎቹ ተጎጂዎቹ ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልከው ህክምና እንዲያገኙ መደረጉንም አክለዋል።

የምንጃር ሸንኮራ ወረዳን በሚጎራበተው ፈንታሌ ወረዳ ያሉ ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ በትላንትናው ዕለት ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ “ቆርኬ” ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች እንደተገደሉ መስማታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የተኩስ ልውውጡ “ከባድ እና ለሁለት ሰዓታት የቆየ” እንደነበርም ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ከመተሐራ ወደ ወለንጪቲ ከተማ የሚወስደው አውራ ጎዳና ተዘግቶ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ትላንት ምሽት 12 ሰዓት ገደማ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ሰራዊት አባላት በአካባቢው ላይ ደርሰው ሁኔታውን ለማረጋጋት መሞከራቸውን የሚያስረዱት ነዋሪዎቹ፤ ሆኖም ወደ ጅቡቲ የሚወስደው ዋና አውራ ጎዳና እስከ ዛሬ ረፋድ አራት ሰዓት ገደማ ድረስ ወደ ለተሽከርካሪ ዝግ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በምንጃር ሸንኮራ አካባቢ የነበረው ተኩስ ወደ አምስት ሰዓታት የፈጀ ነበር የሚሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ የጥቃቱ መንስኤ ግን ገና በመጣራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አስተዳዳሪ የጥቃቱ መነሻ አልታወቀም ቢሉም፤ ድርጊቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ግን “ከፈንታሌ ወረዳ አካባቢ የመጡ ናቸው” ሲሉ ወንጅለዋል። የድርጊቱ ፈጻሚዎች “አካባቢውን ለመውረስ የረጅም ጊዜ እቅድ ያላቸው ናቸው” ሲሉም ከስሰዋል።

በወረዳቸው ስር ያለው “አውራ ጎዳና” ተብሎ የሚጠራው መንደር “ከዚህም በፊት ችግር ያለበት” እንደነበር የሚገልጹት አቶ ታደሰ፤ የፌደራል ፖሊስ በቦታው ተገኝቶ የማረጋጋት ስራ ከሰራ በኋላ ጥቃቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አሁን በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ “አስተማማኝ የሚባል ደረጃ ላይ አይደለም” ብለዋል።

ከሁሉም ወገን የአካባቢውን ሰላም ለማወክ የሚፈልጉ የጸረ ሰላም ኃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቆሙት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በአካባቢው በዘላቂነት ሰላም ለማስፈን የጋራ ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የትላንትናው ጥቃት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የፈንታሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፍሬዘር አበራን ለማነጋገር ብንሞከርም ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *