በደቡብ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ አካባቢ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ በሚጠራው ቡድን መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበረ ተገለጸ።

ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሃገር ኬንያ በምታዋስነው የንግድ መዳረሻዋ ሞያሌ ከተማ ግጭት ተከስቶ እንደነበር አንድ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልፀዋል። ባለሥልጣኑ ግጭቱ ከቅዳሜ ምሽት እስከ እሑድ አጥቢያ ድረስ ዘልቆ እንደነበርም ተናግረዋል። እኚህ ባለሥልጣን እንደገለፁት ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ያደረጉት ታጣቂዎች መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራቸው የኦሮሞ ነፃነት ጦር አባላት ናቸው ብለዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣን የሆኑት ግለሰብ የደረሰውን ጉዳት ከመናገር ተቆጥበዋል። የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ በትዊተር ገፃቸው በደቡባዊ ኦሮሚያ መልካ ለሚ በሚባል ሥፍራ የመንግሥት ኃይሎች “ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ላይ ፅፈዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቀናት በፊት “በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ ነው” ሲል በፌስቡክ ገፁ ፅፏል።

የመከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮሎኔል ግርማ አየለን ዋቢ አድርጎ “የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎች እና ተተኳሽችን ጨምሮ ለሽብር ቡድኑ አመራሮች ሲጓጓዝ የነበረ መድሃኒት በቁጥጥር ስር ውለዋል” ብሏል።

ኮሎኔሉ “የአከባቢው ማሕበረሰብ የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ በማጋለጥ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመስጠት በኩል የተወጡት ሚና ከፍተኛ ነው” ማለታቸውንም ዘግቧል። በኦነግና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተለይ በደቡብና ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎች ግጭት ሲቀሰቀስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት አሸባሪ ሲል በፈረጀው ‘ኦነግ ሸኔ’ እና በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም በመከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭት ይነሳል።

መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ ከፍተኛ ድል እየተቀዳጀሁ ነው ሲል በተለያዩ ጊዜያት ቢገልጥም ታጣቂውም ቡድን በበኩሉ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ላይ ኪሳራ እያስከተልኩ ነው ይላል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ለሚደርስ ጥቃት ተጠያቂው ‘ኦነግ ሸኔ’ ነው ሲል መንግሥት ይኮንናል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *