በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ሪፖርት የቀጠለ. . .

የምርመራው አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ

17.ይህ ምርመራ የተከናወነው አግባብነት ያላቸውን የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች፣ ሰብአዊነትና ወንጀል ሕግጋት እና መርሆዎችን እንዲሁም ብሔራዊ/ሀገራዊ ሕግጋትን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ የተለዩ ጥሰቶችን የሚመለከቱ ዝርዝር የሕግ ትንታኔዎች በሚመለከተው ክፍል ስር ቀርበዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት

18.ኢትዮጵያ ዋና ዋና ከሚባሉት ዘጠኝ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ውስጥ ሰባቱን አጽድቃለች። እነዚህም፡-

  • ማሰቃየትን እና ሌሎች ዓይነት ኢሰብአዊ ወይም አዋራጅ አያያዝን እና ቅጣትን ለማስወገድ የተደረገ ስምምነት፤
  • ዓለም አቀፍ የሰቪል እና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት፣
  • በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማንኛውንም ዓይነት መድሎዎች ለማስወገድ የተደረገ ስምምነት፤
  • ማንኛውንም ዓይነት ዘርን መሰረት ያደረገ መድሎ ለማስወገድ የተደረገ ስምምነት፤
  • ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባሕል መብቶች ስምምነት፤
  • የሕፃናት መብቶች ቃልኪዳን፣ ሕፃናትን በጦርነት ስለማሳተፍ የተደረገ ተጨማሪ ፕሮቶኮል፣ ሕፃናትን መሸጥን፣ ለሴተኛአዳሪነት እና ወሲብ ቀስቃሽ ለሆኑ ተግባራት መጠቀምን ለማስወገድ የተደረገ ተጨማሪ ፕሮቶኮል፤
  • የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ናቸው።

19. ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሚከተሉት አህጉራዊ ስምምነቶች ፈራሚ አገር ነች፡፡

  • የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር፤
  • የአፍሪካ ሴቶች መብቶች የሚመለከት የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር ተጨማሪ ስምምነት /ማፑቶ ፕሮቶኮል/፤
  • የአፍሪካ ሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተር፤
  • የአፍሪካ አረጋውያን መብቶች የሚመለከት የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር ተጨማሪ ስምምነት፤
  • የአፍሪካ ሕብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት) ናቸው።

ከእነዚህ ስምምነቶች በተጨማሪም ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ልማዳዊ ሕጎች በኢትዮጵያ ተፈጻሚነት አላቸው፡፡

20.ኢትዮጵያ ከላይ በተመለከቱት ስምምነቶች እና በልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕጎች እውቅና ያገኙ መብቶችን በአገሪቱ ድንበር ወሰን ወይንም ስልጣን ስር ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ያለ አድልኦ የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ግዴታ ተጥሎባታል፡፡ ይህ ግዴታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎችን ለፍርድ ማቅረብን እንዲሁም መብታቸው የተጣሰባቸው ሰዎች ፍትሕና ካሳ ማስገኘትን እና ወደፊት የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ማስቆምን ጨምሮ ፈጣን፣ በቂ እና ውጤታማ የሆነ መፍትሔ የማስገኘትን ግዴታ ይጨምራል፡፡ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ እና ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊነት ስምምነቶች በጦርነት ወቅት የጣምራ ተፈጻሚነት ያላቸው በመሆኑ በጋራ እና በተጣጣመ መልኩ ሊተረጎሙ ይገባል።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ

21. የሰብአዊነት ሕግ በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎችን ባሕሪያት እና ተግባራት የሚመለከት ሕግ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ስምምነቶች በጦርነቱ ተሳታፊ ያልሆኑ፣ ተሳታፊ መሆን ያቆሙ ወይም በግጭቱ/ጦርነቱ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ማጥቃትን ይከለክላሉ፤ ሰብአዊነት ያለው አያያዝ /እንክብካቤ የማግኘት መብታቸውን ያረጋግጣሉ እንዲሁም በጦርነቱ የሚሳተፉ አካላት የጦር ኃይልን/መሳርያን የግጭቱን ዓላማ ለማሳካት በሚያስችል መጠን ብቻ ማለትም፤ የግጭቱ የመጨረሻ ዓላማ ምንም ይሁን ምን የጦር ኃይል አጠቃቀሙ የጠላትን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም በሚያስችል መጠን ብቻ እንዲሆን ያስገድዳሉ16፡፡በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሀይሎች ሁሉ ተፈጻሚነት ላላቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ስምምነት ድንጋጌዎች ተገዢ የመሆን ግዴታ አለባቸው።

22. ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው እና የሌላቸው ጦርነቶች መካከል ልዩነት ያደርጋል። ዓለም አቀፍ ግጭቶች ሁለት ወይም ከዛ በላይ ቁጥር ያላቸው አገራት የጦር ኃይላቸውን ወይም እነርሱን በሚወክል ሌላ አካል አማካኝነት የሚያደርጉት ጦርነትን የሚመለከት ነው፡፡ዓለም አቀፋዊ ያልሆኑ ግጭቶች ደግሞ በአንድ አገር ድንበር ውስጥ በሀገሪቱ መንግሥት እና አንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ መንግሰታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ኃይሎች መካከል ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ኃይሎች እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ጦርነት/ግጭት ያመለክታል

23. ዓለም አቀፋዊ ያልሆኑ ግጭቶችን የሚመለከቱት ሕግጋት በዋነኛነት የጄኔቫ ስምምነቶች የጋራ አንቀጽ 3 እና የጄኔቫ ስምምነቶች ተጨማሪ ፕሮቶኮል ሁለት ናቸው፡፡ ዓለም አቀፋዊ ያልሆኑ ግጭቶችን በተመለከተ ተፈጻሚነት ያላቸው ተጨማሪ ድንጋጌዎች የተወሰኑ ዓይነት የጦር መሳርያዎችን አጠቃቀም ለመከላከል፣ ለመወሰን ወይንም ለመቆጣጠር የተደረገ ስምምነት (Convention on Certain Conventional Weapons) እና በልማዳዊ የሰብአዊነት ድንጋጌዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 

24. በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ መሰረት አንድ ግጭት ወይም ጦርነት ዓለም አቀፋዊ ያልሆነ ጦርነት ነው ተብሎ እንዲመደብ ሦስት መመዘኛዎች መሟላት አለባቸው። የመጀመሪያው በመደበኛ የሕግ ማስከበር እርምጃዎች ምላሽ ሊያገኝ ያልቻለ እና ከፍ ያለ መጠን ያለው ጦርነት/ግጭት መኖር ሲሆን፣ ይህም በግጭቱ የቆየበትን ጊዜ፣ በጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሳሪያዎችን እና ሌሎች ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚወሰን ነው። ሁለተኛው ግጭቱ በአንድ ሀገር ግዛት ወስጥ በአንድ በኩል በመንግሥት እና በሌላ በኩል አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ቡድኖች መካከል ወይም ሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ የታጠቁ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት መካከል መከናወኑ ነው። ሦስተኛው ታጣቂ ቡድኖቹ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግጋት መሰረት እንደ አንድ ተካፋይ ወገን ለመቆጠር ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለማከናወን እንዲሁም ዓለምአቀፍ ሰብአዊነት ሕግጋትን ለማክበር በሚያስችል መልኩ በቂ አደረጃጀት እና ቁጥጥር ያላቸው መሆኑ ነው።

25. የዚህ ምርምራ ትኩረት የሆነው ጦርነት በመንግሥት ኃይሎች በአንድ ወገን እንዲሁም የትግራይ ኃይሎችና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በሌላ ወገን በመሆን በሀገሪቱ ወሰን ክልል ውስጥ የሚያከናውኑትን በጦር መሳርያ የታገዘ ግጭት በመሆኑ እንደ ዓለም አቀፋዊ ያልሆነ ጦርነት የሚመደብ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ግጭት ተካፋይ የሆኑት ኃይሎች ላይ፣ እንዲሁም በእነዚህ ኃይሎች ትዕዛዝ፣ አመራር እና ቁጥጥር ስር ያሉ ታጣቂዎች እና አጋዥ ኃይሎች ላይ በሙሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ እና አግባብነት ያላቸው ልማዳዊ ሕግጋት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

26. ኢትዮጵያ የሚከተሉትን አጠቃላይ እና ልዩ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ስምምነቶች ፈራሚ ሀገር ናት፦

  • የጄኔቫ ስምምነቶች (1949) እና ተጨማሪ ስምምነት 1፣2 እና 3
  • አፋኝ እና መርዛማ ጋዞች እንዲሁም ባክቴሮሎጂካል ዘዴዎችን ለመከልከል የተደረገ የጄኔቫ ስምምነት /1925
  • ባዮሎጂካል ጦር መሳርያዎችን ለመከልከል የተደረገ ስምምነት /1972/
  • የኬሚካል ጦር መሳርያዎችን ለመከልከል የተደረገ ስምምነት /1993/
  • ፀረ ሰው ፈንጂን ለማገድ የተደረገ ስምምት /1997/
  • ባህላዊ ንብረቶችን /ቁሶችን ለመጠበቅ የተደረገው የሄግ ስምምነት እና የ1945 ተጨማሪ ስምምነት

27.የሁሉም ጄኔቫ ስምምነቶች የጋራ አንቀጽ 3 እና ተጨማሪ ፕሮቶኮል 2 በዚህ ጦርነት ላይ ተፈጻሚነት አላቸው። እነዚህ ስምምነቶች ሲቪል ሰዎች፣ በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸው ሌሎች ሰዎችን የሚመለከቱ ጥበቃዎችን የያዙ ናቸው፡፡ የጋራ አንቀጽ ሶስት የጦርነቱ ተካፋይ ኃይሎች ሁሉ በጦርነቱ ተካፋይነት የሌላቸው ወይም ተካፋይ መሆን ያቆሙ ሰዎች ጎጂ/አሉታዊ/ የሆነ ልዩነት ሳይደረግባቸው ሰብአዊነት በተሞላበት ሁኔታ እንዲያዙ ያስገድዳሉ። ጦርነትን በማካሄድ ወቅት ተዋጊ ኃይሎችን ከሲቪል ሰዎች መለየት፤ ተመጣጣኝነት እና ጥንቃቄ ለሚሉት መርሆዎች ተገዢ መሆን አለባቸው።

28. መንግሥታት ሴቶች እና ሕፃናትን የሚመለከቱ አግባብነት ያላቸው የሰብአዊነት እና የሰብአዊ መብቶች ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ሴቶችና እና ሕፃናት ሴቶችን ጨምሮ በጦርነት ሂደት ውስጥ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው የሚከላከሉ ልዩ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለባቸው፡፡ 

ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ

29. ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ በዓለም አቀፍ ወንጀልነት የተፈረጁ ከፍ ያሉ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግጋት ጥሰቶች ፈጻሚዎች በግለሰብ ደረጃ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ መንግሥታት ይህን መሰል ወንጀሎችን በተመለከተ ተጠያቂነት እንዲኖር የማድረግ ተቀዳሚ ግዴታ አለባቸው፡፡ ለዚህም የወንጀል ድርጊቶቹ እና መርሆዎቹ በአገራዊ ሕጎች ውስጥ በበቂ ጥልቀት እንዲካተቱ በማድረግ የሀገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በተከተለ መልኩ ውሳኔ ለመስጠት በቂ ስልጣን እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

30. ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የጦር ወንጀል፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጥፋትን ወንጀልን ያካትታሉ፡፡ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል (crimes against humanity) በሰላማዊ ወቅትም ሆነ በጦርነት ወቅት በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸም መጠነ ሰፊ እና ከፍ ያለ የመብት ጥሰት ሲሆን እንደ ግድያ፣ ባርነት እና ሌሎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን የሚያካትት እና ፖለቲካዊ አቋምን፣ ዘርን፣ ሃይማኖትን ወይም መሰል ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ሊፈጸም የሚችል ነው።

31. የዘር ማጥፋት ወንጀል አንድን ማኅበረሰብ፣ ብሔር፣ ዘር እና የሃይማኖት ቡድን በሙሉ ወይንም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የሚተገበሩ የተከለከሉ ተግባራትን ያመለክታል፡፡ በሕግ ጥበቃ የተደረገለትን የቡድኑን አባላት አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ደኅንነት ወይንም የቡድኑን ህልውና እና ሥነ- ህይወታዊ ቀጣይነት ላይ ያነጣጠሩ ተግባራትን ያካትታል፡፡

32. የጦር ወንጀል ማለት በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት/የጦርነት ሕግ የተመለከቱ ድንጋጌዎች እና ልማዳዊ ሕጎች ከባድ ጥሰት ሲሆን፣ በዓለም አቀፋዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ባልሆኑ ጦርነቶች ውስጥ ሊፈጸም የሚችል ነው። የሕግ ጥሰቱ ከባድ ነው ተብሎ የሚወሰደው በሕግ ማዕቀፉ ጥበቃ የተደረገላቸውን ሰዎች ወይም ንብረቶች አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ እና የሕጉን መሰረታዊ መርሆዎች የሚጥስ ከሆነ ነው።

33. ግለሰቦች ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎችን ፈጽመው፣ ለመፈጸም ተዘጋጅተው፣ አቅደው፣ እንዲፈጸም ትዕዛዝ ሰጥተው ወይንም እንዲፈጸሙ አነሳስተው የተገኙ እንደሆነ ለዚሁ ተግባራቸው ተጠያቂ ይሆናሉ። ከዚህም በተጨማሪ የጦር ወንጀለኞችን መርዳት እና ማበረታታት እንዲሁም እነዚህን መሰል ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ድጋፍ መስጠት እና ማመቻቸትም ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡

34. የጦር አዛዦች እና ሌሎች ባለሥልጣኖች እንደየሁኔታው ራሳቸው በግል ለፈጸሙዋቸው፣ እንዲፈጸሙ ትእዛዝ ለሰጡባቸው ወይንም ላነሳሷቸው ወንጀሎች እንዲሁም በእነርሱ ሙሉ ሥልጣን ወይም ዕዝ ወይም ቁጥጥር ስር ባሉ አካላት አማካኝነት ይህን መሰል ወንጀሎች እየተፈጸሙ መሆኑን ወይንም ሊፈጸሙ መሆኑን እያወቁ ድርጊቱ እንዳይፈጸም ለማድረግ የሚያስችል አስፈላጊ እና ምክንያታዊ እርምጃዎችን ሁሉ ያልወሰዱ እንደሆነ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡

35. ኢትዮጵያ የሮሙ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት ስምምነት አባል ባትሆንም አብዛኞቹ የስምምነቱ ድንጋጌዎች የዓለምአቀፍ ልማዳዊ ሕግ ደረጃ ያላቸው በመሆኑ እነዚህ ድንጋጌዎች በሀገሪቱም ላይ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡

36. ኢሰመኮ በዚህ የሰብአዊ መብቶች ምርመራው በጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን የለየ ቢሆንም፣ የምርመራው ግኝቶች በራሳቸው ግለሰባዊ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በቂ ባለመሆናቸው፤ ይህን ምርመራ መሰረት አደርጎ የተሟላ የወንጀል ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። 

ብሔራዊ ሕግጋት

37. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ) ሕገ-መንግሥት በምዕራፍ 3 ከዘረዘራቸው የሰብአዊ መብቶች በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል እንደሆኑና23 በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተካተቱ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ከሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ መርሆዎች እንዲሁም አገሪቱ ከተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም እንዳለባቸውም ይደነግጋል፡፡

38. ሕገ-መንግስቱ የተወሰኑ ሰብአዊ መብቶች በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት እገዳ የሚደረግባቸው መሆኑን ገልጾ፣ ሆኖም ከኢ ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ፣ የእኩልነት እና ከአድልኦ የመጠበቅ መብቶችን እና ሌሎች የተወሰኑ ሰብአዊ መብቶች በአስቸኳይ ጊዜ ወቅትም እገዳ የማይጣልባቸው እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች (ዘር ማጥፋትን፣ ያለፍርድ የሚደረጉ ግድያዎችን እና በግዳጅ መሰወርንና ማሰቃየትን በሚያካትት መልኩ አስቀምጦታል) በይርጋ እንደማይታገዱ፤ ይቅርታ እና ምህረትም ተፈጻሚ እንደማይሆንባቸው ይደነግጋል።

39. በ1996 ዓ.ም. የወጣው የወንጀል ሕግ እንደየደረጃው ሰው መግደል፣ አካል ጉዳት ማድረስ፣ በሕገወጥ መንገድ ነጻነትን ማሳጣት፣ ጠለፋ፣ ፖለቲካዊ ጠለፋ፣ ሰውን በባርነት መያዝ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች፣ውንብድና፣ ዘረፋ እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስን ክልከላ የሚያደርጉ እና ቅጣቶችን የሚያስቀምጡ ድንጋጌዎችን ይዟል። የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 269 የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚከለክል እና ቅጣት የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ የወንጀል ድርጊቱን የትርጓሜ መሰረት ከዓለም አቀፍ ስምምነቶችም በላይ በማስፋት የፖለቲካ ቡድኖች ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን እንዲጨምር ያደርጋል። ሕጉ በአንቀጽ 270 ስር ግድያ፣ ማሰቃየት እና ኢሰብአዊ አያያዝ፣ አስቦ ሕዝብን ለረሃብ መዳረግ፣ ማደህየት ወይም ኑሮውን ማናጋት፤ በኃይል ማፈናቀል፣ መበተን፣ ማጋዝ፣ አስገድዶ ስራ ማሰራት፤ ለስለላ ማስገደድ፤ ዜግነት ማሳጣት ሃይማኖት ማስለወጥ፤ በግዳጅ የወሲብ ንግድ ስራ ማሰማራት፤ አስገድድ መድፈር፣ በወጆ /በመያዣነት/ መያዝ፣ ማስፈራራት፣ ማሸበር፣ የጅምላ ቅጣት፣ የበቀል ድርጊት፣ ንብረት መውረስ፣ ማውደምና ለራስ ማድረግ፣ የቤት እንስሳት መውረስ፣ የታሪካዊ እና ሥነጥበባዊ ቁሶችን ማጥፋት ማፍረስ ከጥቅም ውጭ ማድረግ፣ ታሪካዊ እና የሥነ ጥበብ ቦታዎችን፣ ቤተእምነቶችን ለወታደራዊ ዓላማ ማዋል፣ በተቆጣጠረው ስፍራ አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ግልጋሎቶችን አለማቅረብ/እንዳይቀርቡ ማድረግ፣ ስደተኞችን ማጥቃት፣ ከ18 ኣመት በታች የሆኑ ልጆችን በጦርነት ማሳተፍ ለወታደርነት መመልመል፣ ዘላቂ ወይንም መጠነ ሰፊ ጉዳትን የሚያደርስ መሳርያ እና የውግያ ዘዴ መጠቀም፣ ኃይል ማመንጫዎች እና ግድቦችን መምታት እና ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ውጪ ቅጣት መወሰን እና ማስፈጸም የመሳሰሉ ወንጀሎችን ይዟል።

ከአንቀጽ 273 – 274 በጦርነት ወቅት የሚከናወን ዝርፊያ፣ ገፈፋ እና የባህር ውንብድና የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን እንዲሁም ከአንቀጽ 281 – 283 የሰብአዊ ድርጅቶች ሰራተኞች፣ ንብረት እና ምልክቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የወንጀል ድርጊት ያደርጋል፤ ቅጣትም ያስቀምጣል።

የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት የመመርመር ፣ ክስ የማቅረብ እና ተገቢውን መፍትሔ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ

40. ከዚህ በላይ እንደተገለጸው መንግሥት በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና ሰብአዊነት ሕግጋት ላይ የሚፈጸሙ ከፍ ያሉ ጥሰቶችን የመመርመር እና አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡ ፡ ይህን በመሰሉ ጥሰቶች ላይ የሚደረግ ምርመራ ገለልተኛ በሆነ አካል መደረግ እንዲሁም ፈጣን፣ ጥልቅ፣ ግልጽ እና ውጤታማ መሆን አለበት፡፡በተጨማሪም ለተጎጂዎች መፍትሔ ለማስገኘት ጥረት የማድረግና ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ መገኘቱን ማረጋገጥ እንዲሁም ጥሰቶቹ ዳግም እንዳይከሰቱ አስፈላጊ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታም አለበት፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ኃይሎች

41. መንግስታዊ ያልሆኑ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ማለት በአንድ ግዛት/አካባቢ ላይ ቁጥጥር ያላቸው እና መንግሥት መሰል ተግባራትን የሚከውኑ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች በስራቸው ያሉ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች የማክበር ግዴታ አለባቸው። በውግያ ተሳትፎ የሚያደርጉ የታጠቁ መንግስታዊ ያልሆኑ ኃይሎች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ለተቀመጡ መርሆዎች እና ድንጋጌዎች ተገዢ መሆን እና ማክበር አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ተዛማጅነት ያላቸው ልማዳዊ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት በሁሉም ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *