ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ላለፉት 16 ወራት ግጭት ውስጥ የቆየው ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ ግጭት ለማቆም እንደሚስማማ ገለጸ።

ህወሓት ይህን ያለው ትናንት ሐሙስ መጋቢት 15/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲደርስ ለማስቻል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ካስታወቀ በኋላ ነው። የፌደራሉ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ “በእጅጉ ሊያሻሽል” ስለሚችል እና “በቀጣይ ያለተጨማሪ ደም መፋሰስ ለግጭቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል” ተስፋ በማድረግ መሆኑን ገልጿል።

መንግሥት ይህ ውሳኔ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ “በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ” ጠይቋል። ይህን ተከትሎ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ላይ በበቂ መጠን እና ተቀባይነት ባለው ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ ጥሪውን እንደሚቀበል ገልጿል። በትግራይ ካለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እና ተቀባይነት ባለው ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታው የሚደርስ ከሆነ “የትግራይ መንግሥት ግጭት ለማቆም ቁርጠኛ ነው” ብሏል።

በህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በኩል የተጋራ እና ከትግራይ የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት የተሰጠው ነው በተባለው መግለጫ ላይ፤ ፖለቲካዊ እና የሰብዓዊ ጉዳዮች ማገናኘት ተቀባይነት አይኖራቸውም ካለ በኋላ “የትግራይ መንግሥት እና ሕዝብ ለሰላም እድል ለመስጠት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን” ብሏል። የፌደራሉ መንግሥት ከዚህ ቀደም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በክልሉ ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በትናንቱ መግለጫው አስታውሷል።

ነገር ግን ይህ አቅርቦት በክልሉ ያለውንችግር ለመፍታት ባለማስቻሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ሰብዓዊ እርዳታ ፍለጋ ወደአጎራባች ክልሎች እየገቡ መሆናቸውን አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔን ይፋ መድረጉን ተከትሎ አውነታዊ ምላሽ ከሰጡት መካከል የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ መንግሥታት ይገኙበታል። ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን ግጭት የማቆም እርምጃ አድንቃ አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች።

አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ መንግሥት በአስቸኳይ ተግባራዊ የሚሆን ግጭት የማቆም እና ሰብአዊ እርዳታ ያለችግር እንዲደርስ ለማድረግ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ያሳለፈውን ውሳኔ አድንቃለች። ይህ ውሳኔ ድጋፍ ለሚሹ ኢትዮጵያውያን በፍጥነት ለማቅረብ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ለአገሪቱ ደኅንነትና ብልጽግና ሁሉን አካታች የሆነ ፖለቲካዊ ሂደት ለማስጀመር መሠረት እንደሚሆንም ጠቅሷል። ጨምሮም በሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙና ከዚህ በፊት ለተፈጸሙ በደሎችና ጭፍጨፋዎች ተጠያቂነት እንዲኖር ጠይቋል።

ይህንን ግጭት የማቆም ውሳኔን በመከተልም ተፋላሚ ወገኖቹ አስፈላጊ የደኅንነት ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ጨምሮ በድርድር ላይ ወደተመሠረተ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደርሱ መክሯል። ይህ የመንግሥት ውሳኔ ይፋ የሆነው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ጉብኝት አድርገው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ዋነኛ ትኩረት በጦርነት ብዙ ምስቅልቅል ባጋጠመው ትግራይ ክልል እና በሌሎችም አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

ይህንን በተመለከተም ሳተርፊልድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር የተወያዩ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተቋረጠ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ቁርጠኛ ቢሆንም፣ በህወሓት ታጣቂዎች ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ እክል እየገጠመው መሆኑን ለልዩ መልዕክተኛው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። ካለፈው ታኅሣሥ ወር ወዲህ ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ አቅርቦት በየብስ አለመድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ ምግብ ለማግኘት ከፌደራል መንግሥቱና ከክልል ባለሥልጣንት ፈቃድ ማግኘቱን ከቀናት በፊት አስታውቋል።

በ2013 ዓ. ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት ከፍ ያለ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል። ጦርነቱ እስካሁን መቋጫ ስላላገኘ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ለመመለስና እርዳታ ለማቅረብ አስቻጋሪ በመሆኑ በአስቸኳይ እርዳታ ማቅረብ ካልተቻለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የእርዳታ ድርጅቶች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

ህወሓት የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ እገዳ ጥሏል በማለት ሲከስ መንግሥት ደግሞ በእርዳታ አቅርቦት መስመሮች ላይ ጥቃት በመክፈት የእርዳታ አቅርቦትን ያስተጓጎለው አማጺው ኃይል ነው ሲል ይወቅሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ