የጋምቤላ ክልልን ከሚያዋስነው ደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻግረው በመጡ የሙርሌ ታጣቂዎችና የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መካከል፣ ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ውጊያ መካሄዱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

ከ20 እስከ 30 ይደርሳሉ የተባሉት የሙርሌ ታጣቂዎች በትናንትናው ዕለት በክልሉ ወደሚገኘው ኢታም ልዩ ወረዳ ኤልያ ቀበሌ የገቡት በተደጋጋሚ እንደሚያደርጉት፣ የገበሬዎችን ከብቶች ለመዝረፍ መሆኑን፣ የክልሉ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ አዲንግ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ድንበር አቋርጠው ሲገቡ የክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ የቀበሌ ሚሊሻዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ቀድመው ማወቃቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ ታጣቂዎቹ ግን ቀድመው ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎቹ መካከል ውጊያ ተደርጓል፡፡

አቶ ኡጌቱ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች የተሰነዘረው መልሶ ማጥቃት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተው፣ ታጣቂዎቹ ተኩስ ሲበረታባቸው መገልገያ ዕቃዎቻቸውን ትተው ወደ መጡበት መሸሻቸውን ገልጸዋል፡፡ ጥለው ከሄዷቸው ዕቃዎች ውስጥም ለምግብነት ሊጠቀሙበት የነበረ ዱቄት መገኘቱን አክለዋል፡፡ በየዓመቱ በጋምቤላ ክልል በኩል የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ጥቃት የሚፈጽሙት የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች፣ ከ2008 ዓ.ም. አንስቶ እስካሁን ከ740 በላይ ሰዎችን መግደላቸውን የክልሉ መንግሥት መረጃ ያስረዳል፡፡ ታጣቂዎቹ 2014 ዓ.ም. ከገባ ወዲህ 18 ሰዎችን ገድለው ስምንት ሕፃናትን መውሰዳቸውና ከ300 በላይ ከብቶችን መዝረፋቸውም ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ታጣቂዎቹ በከፈቱት ጥቃት ሳቢያ 20 ሺሕ የክልሉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል ተብሏል፡፡

የሙርሌ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም በጥር ወር ላይ በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ ካንካን ቀበሌ በጉዞ ላይ የነበረ አምቡላንስ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ስምንት ሰዎችን ገድለው፣ በአምስት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት አድርሰው ነበር፡፡ ጥቃቱ ከመፈጸሙ ከቀናት በፊትም ከ70 በላይ የቀንድ ከብቶችን ከዘረፉ በኋላ፣ ዘረፋውን ለመከላከል የሞከረ አንድ የፖሊስ ባልደረባ ገድለው ሄደዋል፡፡ የሙርሌ ታጣቂዎቹ በየዓመቱ ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ይህንን ዓይነቱን ጥቃት በክልሉ ነዋሪዎች ላይ በመክፈት ግድያ፣ የሕፃናትና የከብቶች ዝርፊያ ያካሂዳሉ፡፡ ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚጋራው ድንበር ሰፊና ክፍት መሆኑም ታጣቂዎቹ በቀላሉ ድንበር አቋርጠው እንዲገቡ እንዳገዘ ይነገራል፡፡

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ታጣቂዎቹ ቀን በቀን ድንበር ተሻግረው በመምጣት የሚያደርሱትን ጥቃት ቀጥለዋል፡፡ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና ሚሊሻዎች ታጣቂዎቹ የሚከፍቱትን ጥቃት በመከላከል ላይ መሆናቸውን አስረድተው፣ ያላቸው አቅም ግን አነስተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ታጣቂዎቹ በጥር ወር አሥር ገደማ ሰዎችን ከገደሉ በኋላ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳዳር አቶ ኡመድ ኡጅሉ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር፣ የመከላከያ ሠራዊት በክልሉ ገብቶ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን እንዲከላከል ጠይቀው ነበር፡፡ ይሁንና ‹‹ዝግጅት እያደረግን ነው›› በመባሉ የመከላከያ ሠራዊት እስካሁን ወደ ክልሉ እንዳልገባ አቶ ቡን ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው፣ ‹‹እኛ ያለን ልዩ ኃይል በመሆኑ አቅሙ አነስተኛ ነው፣ እንደ መከላከያ ሠራዊት አይሆንም፣ ያጋጠመን ችግር ደግሞ በአገር ደረጃ የሚታይ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በጥር ወር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢጋድ አገሮች ጉዳይ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ፍስሀ ሻውልና በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲን ያካተተ ልዑክ ወደ ደቡብ ሱዳን አቅንቶ ነበር፡፡ ልዑኩ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዳት ጋር በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ተወያይቶ የነበረ ሲሆን፣ የሙርሌ ታጣቂዎች በኢትዮጵያ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጾ ነበር፡፡

ከአንድ ወር በፊት የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የሙርሌ ታጣቂዎች ጥቃትን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት ጉዳዩን በውይይት መፍታት የሚል አቋም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ፣ የጋምቤላ መንግሥት ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት እንዲገባ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥቃት እየፈጸመ ያለው የተደራጀ ኃይል አይደለም፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ምክንያት መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ እንዲገባ ማድረግ አዋጭ ላይሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ አቶ ኡጌቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ታጣዊዎቹ ያሉበት ካምፕ አለመኖሩን ካስረዱ በኋላ፣ መከላከያ ሠራዊት ታጣቂዎቹን ጫካ ውስጥ እንዲፈልግ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን አክለዋል፡፡ ስለዚህም  የክልል መንግሥት የፀጥታ ኃይሉን የማጠናከርና ማኅበራሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ የማንቃት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበርን የሚጋራ በመሆኑ፣ ነዋሪዎች በሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከሚደርሰው ጥቃት ባሻገር፣ በደቡብ ሱዳን ለሚከሰት የእርስ በርስ ግጭት ተጠቂ ሆኗል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የደቡብ ሱዳን መንግሥትን በሚዋጉት የሱዳን ሕዝብ ነፃነት ሠራዊት (Sudan People’s Liberation Army-in-Opposition) እና የአገሪቱ መንግሥት ወታደሮች ባደረጉት ግጭት፣ ተኩሱ ወደ ጋምቤላ ክልል በመዝለቁ አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ ስድስት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ግጭቱ ሥጋት ያሳደረባቸው ዘጠኝ ሺሕ ነዋሪዎች በክልሉ ኑዌር ዞን፣ ላሬና ጂካዎ ወረዳዎች ሥር ከሚገኙ የአራት ቀበሌ ሕዝቦች ተፈናቅለዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *