በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ሪፖርት የቀጠለ. . .

ወሲባዊ እና ፆታዊ ጥቃቶች

የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ጊዜ መጠነ ሰፊ፣ ጭካኔ የተሞላበትና እና ስልታዊ የሆነ በተናጠል እና በቡድን የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሴቶች፣ በሕፃናት ሴቶችና አረጋዊያን ሴቶች ላይ አድርሰዋል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ ንፋስ መውጫ ከተማ ሁለት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች አስገድደው ደፍረዋት ብዙ ደም የፈሰሳት ሴት በጓደኛዋ ቤት ስታገግም ቆይታ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ አክስቷ ቤት ስትሄድ በመንገድ ያገኟት ሌሎች የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በድጋሚ አስገድደው ሊደፍሯት ሲወስዷት ስለነበረው ሁኔታ ስታስረዳ፡

“አንደኛው ታጣቂ ሊደፍረኝ ሱሪዬን ሲያወልቅ ደም ሲመለከት አስጠላሁት እና ተፋብኝ፤ ሰደበኝ እኔም ተስፋ ቆርጨ ራሴን ላጠፋ እያሰብኩ ስለነበር አልፈራሁትም፤ መልሼ ስሰድበው ተናዶ የጠመንጃውን አፈ ሙዝ በማህፀኔ ውስጥ ከተተው። ሕመሙ ከአቅም በላይ ስለነበር ራሴን ሳትኩ፡፡ አሁን ለፊስቱላ በሽታ ሕክምና እየተከታተልኩ ነው፡፡” ብላለች።

በሸዋ ሮቢት ከተማ በትግራይ ኃይሎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ከደረሰባቸው ተጎጂዎች መካከል የ34 ዓመት ሴት ጥቃቱ በተፈጸመባት ማግስት በገመድ ታንቃ ሞታ የተገነች ሲሆን፤ በደረሰባት ጥቃት የተነሳ ሕይወቷን አጥፍታ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በአማራ ክልል ሀይቅ ከተማ ነዋሪ የሆነች ተጎጂ አራት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች እየተፈራረቁ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ፈጽመውባት መንግሥት ቦታውን ከተቆጣጠረ በኋላ ሕክምና ስታደርግ በተላላፊ በሽታ መያዟ የተነገራት መሆኑን አስረድታለች፡፡ በመሀል ሜዳ መንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ቀበሌ 03 የቡድን አስገድዶ መድፈር ጥቃት የደረሰባት የ20 ዓመት ተጎጂ ቀኑን በማታስታውሰው ዕለት ሻይና ቡና ንግድ በምትሰራበትና በምትኖርበት የኮንቴይነር ቤት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በመምጣት አብረዋት የነበሩትን የ80 ዓመት አባቷን አውጥተው ውጪ ግንድ ላይ አስረው የ2 ዓመት ሕፃን ልጇ ባለበት ለ3 እንደደፈሯት አስረድታለች። በደባርቅ ወረዳ ድብባህር በትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በተደጋጋሚ አስገድዶ መድፈር ተጎጂ የሆነች ሴት ስታስረዳ

“በየተራ እየመጡ ይደፍሩኝ ነበር፡፡ ሲደፍሩኝ፣ የእናንተ ሰዎች የእኛን ሴቶች ለ10 ሆነው ነበር የሚደፍሩት ይሉኝ ነበር፡፡ እኛ እነሱን ለመበቀል ነው የመጣነው እንጂ በአክሊል ነበር የምንዳረው ይላሉ፡፡ እየተመላለሱ 15 ታጣቂዎች ደፍረውኛል” በማለት አስረድታለች፡፡

በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን ያሎ ወረዳ ነዋሪ የሆነች ተጎጂ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂ ቤቷ መጥቶ የባሏን መሳሪያ እንድትሰጠው ሲጠይቃት ባለቤቷ ምንም አይነት መሳሪያ እንደሌለው በመግለጿ ካራ አውጥቶ ሊወጋት ሲል ይተወኛል በሚል ብር እንደሰጠችውና ብሩን ከወሰደ በኋላ ግን በልጆቿ ፊት አስገድዶ እንደደፈራት አስረድታለች። በአማራ ክልል ከሚሴ ከተማ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፍተሻ በገቡበት መኖሪያ ቤት የነበረችን ሴት ብሔሯ አማራ መሆኑን ጠይቀው ከተረዱ በኋላ ደብድበው በቡድን በመሆን አስገድደው ደፍረዋታል፤ ቤቷ ውስጥ የነበረ ገንዘብም ወስደውባታል። የትግራይ ኃይሎች በሁለቱም ክልሎች ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ስፍራዎች የቤት ለቤት ብርበራ ሲፈጽሙ እንደነበር እና ሴቶችን የመከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና የፋኖ ሚስት ናችሁ በማለት የማንገላታት፣ ምግብ እንዲያበስሉ የማስገደድ እና በተናጠልና በቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ይፈጽሙባቸው እንደነበር ኮሚሽኑ በርካታ ማስረጃዎች የሰበሰበ ሲሆን ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ሆኖም ተጎጂዎች የደረሰባቸው ወሲባዊ ጥቃት በማኅበረሰቡ ከታወቀ ሊደርስባቸው የሚችለውን መድሎ እና መገለል በመፍራት ብዙውን ጊዜ ጉዳታቸውን ለመናገር የማይፈልጉ በመሆኑ ኮሚሽኑ ብዙ ተጎጂዎችን ለማነጋገር ባለመቻሉ የጥቃቱ ስፋት በዚህ ሪፖርት ከተመለከተው በእጅጉ ከፍ ያለ እንደሚሆን ኮሚሽኑ ያምናል።

በትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በአፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍተው የተፈጸሙ ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃቶች የተጎጂዎችን እና የጥቃቱ ዒላማ የተደረጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ሰብአዊ ክብር ለመጉዳት እና ለማዋረድ፣ በአብዛኛው በሴቶች ላይ በሙሉ ያለልዩነት፣ አልፎ አልፎም አጥቂዎቹ ሆነ ብለው ለጥቃቱ ዒላማነት በመረጧቸው ሴቶች ላይ ሆነ ተብሎ ታቅዶ በግፍና በጭካኔ፣ በግልጽ የበቀል ስሜት፣ በቡድን አስገድዶ በመድፈር፣ ድርጊቱን ሆነ ተብሎ በቤተሰብ ፊት በመፈጸምና፣ ባዕድ ነገር (የጠብ መንጃ አፈ ሙዝ) በማህፀን በመክተት ጭምር፣ በታጣቂዎቹ ኃላፊዎች ይሁንታ እና ዝምታ የተፈጸመ በመሆኑ፤ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በሴቶች ላይ የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለጦርነት አላማ እንዳዋሉት የሚያስረዳ ነው፡፡ እነዚህ የመብት ጥሰቶችም በጦርነት ዐውድ ውስጥ የተፈጸሙ በመሆናቸው የጦር ወንጀልም ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። 

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች

በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ በተለይም የትግራይ ኃይሎች በአማራ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ወራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከቤታቸውና መኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ጉዳቶች ተዳርገዋል። በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረው የፀጥታ ስጋት እና በትግራይ ኃይሎች በተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና የንብረት ዝርፊያዎች ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ተፈናቃዮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከመለያየት በተጨማሪ፤ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመኝታ፣ የጤና አገልግሎቶች የመሳሰሉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች የተሟሉላቸው ባለመሆኑ፤ በተለይም የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ፣ ለሕፃናት፣ ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች የተለየ እና የተሟላ አቅርቦት ባለመኖሩ ልዩ ድጋፍ የሚሹትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግር ይበልጥ አባብሶታል፡፡ በርካታ ተፈናቃዮች ወደመኖሪያ አካባቢያቸው በተመለሱበት ወቅትም፤ የመኖሪያ ቤቶቻቸው እና ልዩ ልዩ ንብረታቸው፣ የእርሻ ማሳዎች እንዲሁም የአካባቢያቸው መሰረታዊ አገልግሎት ተቋማት በመዘረፋቸው እና በመውደማቸው ምክንያት ተመላሽ ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት፣ የሕክምና አገልግሎት ማጣትን ጨምሮ ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠዋል፡፡

በንብረት ላይ የተፈጸመ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና ውድመት

በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩ እና ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በተደራጀ መልኩ የትግራይ ኃይሎች በመንግሥት አስተዳደር ተቋማት፣ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (በተለይ የጤና ተቋማት እና የትምህርት ተቋማት) ፣ በግል ንብረቶች እና በንግድ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና የንብረት ውድመት ፈጽመዋል። በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ሕግና ሥርአት መፍረሱን ተከትሎ የተወሰኑ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የሆኑ ሰዎችም በዝርፊያው ተግባር ተሳትፈዋል። በአብዛኛዎቹ ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ሆነ ተብሎ በታቀደ፣ በተጠና፣ በተደራጀ መንገድ ስልታዊ የዘረፋና ገፈፋ ተግባር በተለይ የሕክምና መሳሪያ ቁሳቁስ፣ ማሽኖችን እና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመዝረፍና በመግፈፍ፣ በመኪና በመጫን ወስደዋል፡፡ በተለይም ከሆስፒታሎች እና የሕክምና መስጫ ተቋማት መድኃኒቶችን፣ እንደ ኤክስ ሬይ፤ አልትራ ሳውንድ፤ የደም መመርመሪያ፣ የላቦራቶሪ ማሽነሪዎች፣ አምቡላንሶች እና ሌሎችም የሕክምና መሳሪያዎች ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡ በተለይ በሕክምና መሳሪያዎች እና ማሽኖች ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ በባለሙያ እየታገዘና ማሽኖቹ በጥንቃቄ እየተፈቱና እየተነቀሉ ተወስደዋል፡፡ በአማራ ክልል 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎች፣ እና 1850 የጤና ኬላዎች (በድምሩ በአማራ ክልል ብቻ 2343 የጤና ተቋማት) ፤ እንዲሁም በአፋር ክልል 2 ሆስፒታሎች፣ 19 ጤና ጣቢያዎች እና 45 የጤና ኬላዎች (በድምሩ በአፋር ክልል 66 የጤና ተቋማት) ፤ በአጠቃላይ በሁለቱ ክልሎች በ 2409 የጤና ተቋማት ላይ ጥቃት፣ ጉዳትና ዝርፊያ በመድረሱ አገልግሎታቸው ተቋርጧል፡፡(ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ) በአማራ ክልል 1025 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ፤ 3082 ደግሞ በከፊል ወድመዋል። በአፋር ክልል 65 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ 138 ደግሞ በከፊል ወድመዋል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ ክልሎች 1090 ት/ቤቶች ሙሉ በሙሉ 3,220 ደግሞ በከፊል ወድመዋል። (ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ) በፋይናንስ ተቋማት በተለይም በ18 የንግድ ባንኮች 346 ቅርንጫፎች ላይ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ዘረፋ እና ውድመት ደርሷል። (ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘ መረጃ) የትግራይ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው አንዳንድ አካባቢዎች የዘረፋ እና የንብረት ውድመት በፈጸሙባቸው የሕዝብ አስተዳደር ተቋማትና የግለሰብ ንብረቶች እንዲሁም ለወታደራዊ ካምፕ እና ሌሎች አገልግሎቶች የተጠቀሟቸው ትምህርት ቤቶች፣ ታሪካዊ ስፍራዎች እና ጤና ተቋማት ግድግዳዎች ላይ የስድብ መልዕክቶችን በመፃፍ እና በሕንጻዎች ወለል ላይ፣ ጠረጴዛና መሳቢያዎች እንዲሁም ወንበሮች ላይ ሆነ ተብሎ በመጸዳዳት ጭምር አበላሽተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የደሴ ንጉስ ሚካኤል ቤተመንግሥት (አይጠየፍ አዳራሽ) የንጉስ ኢያሱ እልፍኝ አዳራሽ በሚል በሚጠራው ቤት ላይ እና በአጣዬ ከተማ ጤና ጣቢያ ላይ የደረሱት ብልሽቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህ ምርመራ በተመለከታቸው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የበርካታ ሰዎች የንግድ መደብሮች እና የመኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ከዕለት የምግብ ፍጆታና አልባሳት ጀምሮ እስከ ንግድ እቃዎች እና ሸቀጦች፤ አላቂ የምግብ ፍጆታዎች፣ እህሎች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ የቤት እንስሳትና ሰብሎች እንዲሁም ገንዘብ በትግራይ ኃይሎች ተዘርፈው ተወስደዋል፣ የቀንድ እና የጋማ ከብቶችን በጥይት መትተው ገድለዋል።

ሌላ በኩል በተለይም በአማራ ክልል የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩ ስፍራዎች ከለቀቁ በኋላ በአንዳንድ አካባቢዎች ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተባብረዋል የተባሉ ሰዎች እና ለደኅነታቸው በመስጋት ከተሞቹን ጥለው በሸሹ የትግራይ ተወላጆች ንብረቶች በልዩ ልዩ የመንግሥት ታጣቂዎችና በተወሰኑ የየአካባቢው ነዋሪ ሰዎች ተዘርፈዋል፡፡ በወቅቱ በስፍራው የነበሩ የፌደራል መንግሥት እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በቂ ጥበቃና የመከላከል እርምጃ አልወሰዱም። ለምሳሌ በሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ድርጅቶች በተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪ ሰዎች ተዘርፈዋል። እንዲሁም በሰንበቴ ከተማ ጃራ ዋታ የገጠር ቀበሌ የፋኖ አባላት የሆኑ ሰዎች አንዳንድ መኖሪያ ቤቶችን እየሰበሩ መዝረፋቸውን፤ በአጣዬ ከተማም የግለሰቦች ቤቶች ተሰብረው ዘረፋ መፈጸሙን ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ክልከላ

በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ውስጥ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ የተከሰተ ሲሆን፣ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ በተለይ በአፋር ክልል ጦርነቱ አሁንም በመቀጠሉ ምክንያት በአፋር እና ትግራይ ክልሎች ሰብአዊ እርዳታን ለማድረስ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኗል፡፡ የጦርነቱ እና የጸጥታ መደፍረስ ሁኔታ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የፈጠረው እንቅፋት የሚታወቅ ቢሆንም፤ በተለይ ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብአዊ እርዳታ ላይ በፌደራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት የሚደረጉ አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ መስፈርቶችና የስራ ሂደቶች አስፈላጊው እርዳታ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል። የፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለኢሰመኮ በሰጠው መረጃ እስከ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የመንግሥትና የአጋር ድርጅቶችን የእርዳታ ስራ በማስተባበር ከ 8 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ በጦርነቱ ምክንያት እርዳታ ላስፈለጋቸው ሰዎች የምግብና ሌሎች አይነት አስፈላጊ እርዳታዎች መቅረቡን፤ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥት እርዳታ እንዳይደርስ የተደረገ ክልከላ አለመኖሩንና ሆኖም በጸጥታ መደፍረስና በጦርነቱ ምክንያት የእርዳታ አቅርቦት መስተጓጎል እንደሚያጋጥም ገልጿል። የአፋርና አማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት ወደ ስፍራዎቹ መድረስ አስቸጋሪ የነበረ እና በተወሰነ መጠን ሲደርስ የነበረው ሰብአዊ እርዳታ በጣም ዝቅተኛ የነበረ ሲሆን፤ ለዚህም ዋነኛው ምክንያቶች የጦርነት ሁኔታው፣ የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች ያስቀመጧቸው ኬላዎች እና በእርዳታ አቅርቦቱ እና ሰራተኞች ደኅንነት ላይ የነበረው ስጋት መሆኑ ይገለጻል። የአፋርና አማራ ክልል አብዛኛዎቹ ስፍራዎች በፌደራል እና በክልሎቹ መንግሥታት ቁጥጥር ስር ከገቡ በኋላ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የተሻሻለ ቢሆንም ካለው ፍላጎት አንፃር በቂ እንዳልሆነ ኮሚሽኑ ተገንዝቧል።

ኢኮኖሚያዊ፡ ማኅበራዊና የባሕል መብቶች

ለዓመታት የተገነቡ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት በመድረሱ ምክንያት የሰዎች የጤና መብት፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ እና የንጽሕና ሁኔታ የማግኘት እና የትምህርት መብቶች ላይ እንዲሁም እንደ የኤሌትሪክ ኃይል፣ ባንክ እና ስልክ የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ጉዳት ደርሷል። የትግራይ ኃይሎች ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የአማራ እና አፋር ክልሎችን የተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ጊዜያት በመንግሥት ተቋማት እና በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። በነዋሪዎች የመኖርያ ቤቶች፤ እርሻዎች እና የቤት እንስሳት ላይ ባደረሱት ዝርፊያና ውድመት ነዋሪዎቹን ለመጠለያና ለምግብ ችግር አጋልጠዋል፡፡ በተለይም በጤና እና ትምህርት ተቋማት ላይ በደረሰው ዝርፊያ፤ ውድመት እና ቃጠሎ የየአካባቢው ነዋሪዎች የጤና እና ትምህርት አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ ያደረገ ሲሆን፣ በርካታ ነፍሰጡር እናቶች በሕክምና እጦት ሕይወታቸው አልፏል። ለአብነትም በአማራ ክልል መቄት ወረዳ ሸሆድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በወረዳው የሚገኝ ብቸኛ ሆስፒታል ሲሆን በደረሰበት ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት ምክንያት አገልግሎት መስጠት በማቆሙ በወረዳው 8 ነፍሰጡር እናቶች በሕክምና ማጣት ሕይወታቸው አልፏል።

በሕፃናት ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶች

በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳታፊ አካላት በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ሕፃናት ለሞት፣ ለአካል እና ለሥነ ልቦና ጉዳት እንዲሁም ለወሲባዊ ጥቃት ተጋልጠዋል፤ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው የጤና፣ የትምህርት እና በቂ የኑሮ ሁኔታ የማግኘት መብቶቻቸው ተጥሰዋል። ወላጆቻቸው እና ሌሎች የቤተሰብ አባላት ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የአካል ጉዳቶች፣ እንዲሁም በርካታ ሲቪል ሰዎች በጦርነቱን ምክንያት የተፈናቀሉ በመሆኑ ካስከተለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነልቦና ጉዳት በተጨማሪ፤ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ሊያገኙት ይገባ የነበረውን ጥበቃ እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል። የሕክምና ተቋማት በመውደማቸው እና በመዘረፋቸው በቂ ሕክምና ለማግኘት ሳይችሉ ሕይወታቸው ያለፈ ሕፃናትም አሉ። በጦርነቱ ተሳታፊ አካላት በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች በርካታ ሕፃናት ተገድለዋል፤ በአቅራቢያቸው ያሉ ሕክምና ተቋማት በመውደማቸው እና በመዘረፋቸው በቂ ሕክምና ለማግኘት ሳይችሉ ሕይወታቸው ያለፈ ሕፃናትም ነበሩ።

የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በአማራ ክልል ጭና ቀበሌ አንድን አባት ከገደሉ በኋላ የ7 ዓመት ሕፃን ልጃቸውንም “ይህ አድጎ ነው የሚወጋን” ብለው በእናቱ ፊት በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። በተዋጊ ኃይሎች በተፈጸሙ ሲቪል ሰዎችን ባልለዩ፣ ጥንቃቄ ባልታከለባቸው እና ተመጣጣኝ ባልሆኑ የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች በርካታ ሕፃናት ተገድለዋል፤ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሐሙሲት ከተማ በመከላከያ ሠራዊት የተተኮሰ ከባድ መሳሪያ አንድ የ2ሁለት ዓመት ሕፃን እና አባት ሲገደሉ ሌሎች ሁለት የቤተሰቡ አባላት ደግሞ ቆስለዋል። በዚሁ ከተማ አካባቢ በመኖሪያ ቤት ላይ ያረፈ ሌላ ከባድ መሳሪያ የ5 እና የ16 ዓመት እህትማማቾችን ገድሏል። በአማራ ክልል ዳባት ወረዳ በድብ ባሕር ንዑስ ወረዳ እንጨት ለመልቀም የወጣችን የ14 ዓመት ታዳጊ ሕፃን ሁለት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች “የእናንተ ወታደሮች የእኛን እናቶች አእና እህቶች ደፍረዋል፤ ስለዚህ እናንተም መደፈር አለባችሁ” ብለው በጥፊ ከመቷት በኋላ አንደኛው ታጣቂ አስገድዶ እንደደፈራት ተጎጂዋ አስረድታለች።

የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን

በጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎች በተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ምክንያት በርካታ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ተገድለዋል፤ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ እንዲሁም አረጋዊያን ሴቶች በትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል። በተጨማሪም ቤት ንብረታቸው ወድሟል እንዲሁም በሚጦሯቸው እና በሚደግፏቸው ቤተሰቦቻቸው ላይ በተፈጸሙ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች እና የንብረት ዘረፋ እና ውድመቶች ምክንያትም ያለጧሪ እና ደጋፊ ቀርተዋል፤ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል። በአማራ ክልል ሸዋ ሮቢት ከተማ ኅዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠዋት 3፡00 ሰዓት አካባቢ አንድ የ70
ዓመት አረጋዊ፤ ቀበሌ 05 ከሚገኘው ሱቃቸው በተቀመጡበት የትግራይ ታጣቂዎች ሲጋራ እንዲሰጧቸው ሲጠይቋቸው “ደሀ ዘርፈህ ብላ የሚል መንግሥት የለም” ብለው በመመለሳቸው ብቻ በሱቃቸው ውስጥ እንዳሉ በጥይት ደረታቸውን መትተው ገድለዋቸዋል፡፡ የወልዲያ ከተማ ቀበሌ 04 ነዋሪና የሆኑ የ60 ዓመት አረጋዊት ነሃሴ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ኃይሎች ታጣቂ አስገድዶ መድፈር ተፈጽሞባቸዋል።

የአዕምሮ ሕሙማን በተለይ በትግራይ ኃይሎች ከሌሎች ሲቪል ሰዎች በበለጠ የጥቃት ዒላማ ተደርገዋል። ሕሙማኑ የትግራይ ኃይሎች ወደ ተቆጣጠሯቸው ከተሞች ሲገቡ በመንገድ ላይ በመገኘታቸው፣ ወይም መንቀሳቀስ በተከለከለባቸው ሰዓታት ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው፣ ወይም የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ባለመቻላቸው፣ ወይም ለሚጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ባለመቻላቸው፣ ወይም የመንግሥት ሰላዮች ናቸው በሚል ጥርጣሬ መገደላቸውን ኮሚሽኑ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያሳያሉ። በርካታዎቹ የአዕምሮ ሕሙማን ለመገደላቸው ዋነኛው ምክንያት ለመንግሥት ኃይሎች መረጃ የሚያቀብሉ ሰዎች እንደ አዕምሮ ሕሙማን መስለው በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙ ቦታዎች ውስጥ ይሰልላሉ የሚል ጥርጣሬ ነው። የአዕምሮ ሕሙማንን በሰላይነት የመጠርጠር አመለካከት በመንግሥት ኃይሎች ዘንድም እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ። በሰንበቴ ከተማ ይኖር የነበረ አንድ የአዕምሮ ሕመምተኛን የመከላከያ ሠራዊት አባላት “የትግራይ ኃይሎች ተላላኪ ነው” በማለት ሁለት ጊዜ ወስደውት የአካባቢው ሰው ሕመምተኛ መሆኑን አስረድቶ ያስጣሉት ቢሆንም በመጨረሻ የመከላከያ ሠራዊት ምሽግ ሰርቶ የነበረበት ቦታ ተገሎ ተገኝቷል።

ምክረ ሃሳብ

ሪፖርቱ ለሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ዝርዝር ምክረ ሃሳቦችን አካቷል። ከነዚህም ምክረ-ሃሳቦች መካከል፣
1. የጦርነቱ ተሳታፊዎች በአባሎቻቸው ለተፈጸሙ ጥሰቶች ኃላፊነት በመውሰድና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ፤
2.
ፆታዊ ጥቃት የፈጸሙትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖች ሁሉ ተጠያቂ ለማድረግ ገለልተኛ፣ ተአማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃውን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር፣
3. ተጎጂዎችን፣ የተጎዱ አካባቢና ተቋሞችን መልሶ የማቋቋም ስራ በልዩ ትኩረት እንዲከናወን፤
4. ሀገራዊ፣ አሁጉራዊና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ለሰላማዊ መፍትሔ፣ ለፍትሕ እና ለመልሶ ማቋቋም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ የሚጠይቁት ይገኙበታል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *