ቅዳሜ መጋቢት 10/2014 ዓ.ም በአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ቡልቡላ ከተማ በተካሄደ የሚሊሻ ምርቃት ላይ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ የ12 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልፁ።

ከሞቱት ሰዎች መካከል ሦስቱ ለ20 ቀናት ሥልጠና ላይ ቆይተው በዕለቱ ይመረቁ የነበሩ የሚሊሻ አባላት መሆናቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሙሐመድ በሪሶ ገልፀዋል። አቶ ሙሐመድ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 10/2014 ዓ.ም በቡልቡላ ከተማ ስታዲየም በርካታ ነዋሪዎች በተገኙበት ከ200 በላይ የሚሊሻ አባላት መመረቃቸውን ተናግረዋል። ይሁንና የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቅቆ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከመድረኩ ከተሸኙ በኋላ ሕዝቡና የሚሊሻ አባላት በደስታ እየጨፈሩ እያለ የቦንብ ፍንዳታው መድረሱን ተናግረዋል።

በፍንዳታው የ12 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ሦስት ሚሊሻዎች ሲገደሉ 35 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን ባለሥልጣኑ ገልፀዋል። አቶ ሙሐመድ አክለውም ፍንዳታውን በማድረስ የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል። የቡልቡላ ከተማ ተወላጅ የሆኑት እና አሁን በባቱ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ዶ/ር ገቦ ቲቤሶ ባለፈው ቅዳሜ ቤተሰባቸውን ለማግኘት ወደ ቡልቡላ ሄደው እንደነበር ገልፀው፣ እየተመለሱ ባለበት ወቅት ፍንዳታ ሰምተው መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዕለቱም በርካቶች የተጎዱ ሰዎችን ወደ ዋናው መንገድ ሲያወጡ መመልከታቸውን ጠቅሰው እርሳቸውም ሰባት የተጎዱ ሰዎችን ይዘው ባቱ ከተማ ወደሚገኝ የሕክምና ተቋም ማድረሳቸውን ገልፀዋል። የቡልቡላ ጤና ጣቢያ እንዲሁም የባቱ ሆስፒታል በተጎዱ ሰዎች ስለሞላ ተጎጂዎች ሼር ወደተባለ የግል ሆስፒታል እንዲሁም ወደ መቂ ሆስፒታል ሲወሰዱ እነደነበርም አክለው ገልፀዋል።

ዶ/ር ገቦ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ከ62 በላይ መጎዳታቸውን እንደሰሙ ለቢቢሲ ጨምረው ገልፀዋል። አክለውም አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች እድሜያቸው ከስምንት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት መሆናቸውንም ተናግረዋል። ከምረቃ ፕሮግራሙ በፊት አነስተኛ ፕሮግራሞች እንደነበሩ ያስታወሱት ኃላፊው፣ ዋናው የምረቃ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ጥብቅ ፍተሻ እንደነበር በመግለጽ፣ የቦንብ ፍንዳታው የደረሰው ተቀብሮ ይሆን ተወርውሮ እየተጣራ ነው ብለዋል።

በፍንዳታው ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና እርዳታ ያገኙ ተጎጂዎች አብዛኛዎቹ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ገልፀው፣ ስድስት ሰዎች ግን እስካሁን ድረስ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል። “ይህንን ቦንብ ያፈነዳው ጠላት” ነው ሲሉ የገለፁት ባለሥልጣኑ ፍንዳታውን ያደረሰው ማን እንደሆነ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል። ለቦንብ ፍንዳታው እስካሁን ድረስ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።

በዚህ ቦንብ ፍንዳታ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች በትናንትናው ዕለት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው መፈፀሙን ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በወረዳ ደረጃ የሚሊሻዎች ሥልጠና እንደሚካሄድ በገለፀው መሰረት የአብዛኛው የኦሮሚያ ዞን ወረዳዎች የራሳቸውን ሚሊሻ አሰልጠንው እያስመረቁ ይገኛሉ።