አንኳር ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን በትግራይ ክልል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ በተለይ በትግራይ ክልል እና በተወሰነ መጠን በሌሎች አካባቢዎችም ስለነበረው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ያወጡት የጣምራ ምርመራ ሪፖርት ይታወሳል፡፡ የጣምራ ምርመራ ሪፖርቱ በጊዜ ረገድ በወቅቱ ለመሸፈን የቻለው ጦርነቱ ከተነሳበት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ የፌዴራሉ መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከትግራይ ክልል መውጣቱን እስካስታወቀበት ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ነበር፡፡ በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎም ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተከስተዋል፡፡

ኢሰመኮ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ ባሰማራው የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ቡድንና ተከታታይ የምርመራ ስልቶች በአፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መርምሯል፡፡ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት ወገኖች በአንድ በኩል የትግራይ ኃይሎችና ተባባሪ ሚሊሺያዎች (በአንዳንድ አካባቢዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም በተለምዶ ኦነግ ሸኔ በመባል የሚጠሩትን ታጣቂ ኃይሎችን ጨምሮ) እና በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች (የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካሎች፣ የአማራ እና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎችንና ተባባሪ ሚሊሺያሚሊሺያን ጨምሮ) ሲሆኑ፤ ምርመራው በጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖችና ተባባሪ ተዋጊዎች ተፈጸሙ የተባሉ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን ይመለከታል።

በተጨማሪም የዚህ ምርመራ ዋነኛ ትኩረት በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ቢሆንም፤ በተወሰነ መጠን በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን በሚመለከትም ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ አድርጓል። የምርመራው ዋና ዓላማ በጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን ከነፆታዊ እንድምታው መለየት ነው። የምርመራውን ግኝቶች መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ የሚሰጣቸው ምክረ ሃሳቦች የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ማገዝ፤ ተጎጂዎች ፍትሕ እና ተገቢውን የካሳ እና መልሶ መቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻል እና ወደፊት ተመሳሳይ ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ማስቻል ነው። በአጠቃላይ 29 አባሎች የነበሩት የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች በጦርነቱ በተጎዱ በርካታ ቦታዎች በአካል በመገኘት ምርመራ አድርጓል፡፡ እንዲሁም በትግራይ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን እንደርታ ወረዳ ደብረናዝሬት ጣብያ ቶጎጓ ጎጥ እና መቀሌ አካባቢዎች የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን በሚመለከት እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን በሚመለከት በተለያዩ ጊዜያት ከተጎጂዎች፣ ከምስክሮች እና ከሚመለከታቸው ምንጮች መረጃዎችና ማስረጃዎችን ሰብስቧል፡፡

በምርመራው የተሸፈኑ አካባቢዎች

ኮሚሽኑ በዚህ የምርመራ ሂደት በአጠቃላይ 427 ሚስጥራዊ ቃለ መጠይቆችን፣ ከልዩ ልዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች ጋር 136 ስብሰባዎችን እና ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 12 የቡድን ውይይቶችን ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ የየአካባቢው ነዋሪዎችና የዓይን ምሰክሮችን፣ የሆስፒታልና ጤና ተቋም ባለሙያዎች፣ የእርዳታ ድርጅቶችና፣ ሲቪል ማኅበራትን ይጨምራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ለምርመራው ስራ የሚያስፈልጉትን መረጃዎችና የሰነድ ማስረጃዎች ጭምር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ልዩ ልዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ምንጮች ሰብስቧል፡፡ ኮሚሽኑ ምርመራውን ያካሄደው አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በተለይም በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች፣ በሰብአዊነት ሕጎች ወይም ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎች፣ በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ፣ በሌሎችም ዓለም አቀፍ መርሆዎች እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሕግጋት መሰረት ነው፡፡ ኢሰመኮ በሰበሰባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች መነሻነት ግኝቶች ወይም ድምዳሜዎች ላይ ለመድረስ የተጠቀመው የማስረጃ ምዘና ስልት፤ በተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራዎች ጥቅም ላይ የሚለውን “ምክንያታዊ አሳማኝነት” (reasonable grounds to believe) የተሰኘውን የማስረጃ ምዘና ስልት ነው። ይህ ሪፖርት ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተፈጸሙ ሁሉንም ጥሰቶችን የሚሸፍን አይደለም። ሆኖም ምርመራው በተከናወነባቸው ስፍራዎች የተፈጸሙ ዋና ዋና የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ዋነኛ ጠባዮችና ሁኔታዎችን እና አጠቃላይ የጥሰት ዓይነቶችን ወካይ በሆነ መልኩ አካትቷል፡፡ 

የምርመራው ግኝቶች

ከጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ኃይሎችና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የተጀመረው የትጥቅ ግጭት ለወራት ከቀጠለ በኋላ፤ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራሉ መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም ማድረጉን አሳውቆ ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌና አብዛኛው የትግራይ አካባቢዎች ለቅቆ ወጣ፡፡ የትግራይ ኃይሎችም በተከታይ ቀኖች የመቀሌን ከተማና ሌሎችም የተለቀቁ የትግራይ ክልል ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን አሳወቁ፡፡ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች በአጎራባች የአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች ላይ በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠር ጀመሩ፡፡ እስከ ጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የትግራይ ኃይሎች ከኦነግ ሸኔ ጋር ትብብር የፈጠሩ መሆኑንም በማሳወቅ ጭምር በአፋርና አማራ ክልሎች በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ቆይተው ነበር፡፡ ከኅዳር ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የፌደራሉ መንግሥት ከክልሎቹ መስተዳደሮች ጋር በመቀናጀት በከፈቱት መጠነ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ፤ የትግራይ ኃይሎችና ኦነግ ሸኔ በአፋርና አማራ ክልል ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩ ቦታዎች ወጥተው በፌዴራሉ መንግሥትና የክልሉ መስተዳድሮች ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የትግራይ ኃይሎች በጥር ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአፋር ክልል ዳግም በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት 5 ወረዳዎችንና የአብአላ ከተማን ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡ ጦርነቱ በአብዛኛው ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው የከተማ እና ገጠራማ አካባቢዎች በመካሄዱ በጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፤ ለአካል እና ለሥነልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፤ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችም ተፈጽመውባቸዋል። እንዲሁም በንብረት ላይ በተለይም በትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት እና በመሰረተ ልማቶች ላይ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት ተከስቷል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለዘርፈ ብዙ ችግር ተጋልጠዋል። የኮሚሽኑ ምርመራ ግኝቶች በጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች በተለያየ ደረጃ የተፈጸሙ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን ያሳያሉ።

በሲቪል ሰዎች፣ ሲቪል ተቋማት እና ሌሎች ጥበቃ በሚደረግላቸው ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች

በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው በሲቪል ሰዎች ላይ በተለይም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጭምር እንዲሁም በሲቪል ሰዎች ቁሶች ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ያልተደረገበት፣ የመለየት መርህን ያልተከተለና ያልተመጣጠነ ጥቃት ፈጽመዋል። ሲቪል ሰዎችን እንደከለላ በመጠቀም በመኖሪያ ቤቶች እና በከተሞች ውስጥ ጦርነት በማካሄድ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ አካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት እንዲከሰት አድርገዋል። በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግን በሚጥስ መልኩ ከባድ መሳሪያዎችን ተኩሰዋል፤ የአየር እና የድሮን ድብደባዎችን ፈጽመዋል። ኮሚሽኑ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ምርመራ ባደረገባቸው ሥፍራዎች ሆነ ተብለው የተፈጸሙ ሕገወጥ ግድያዎችን ሳይጨምር፤ በጦርነት ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ በደረሰ የሕይወትና የአካል ጉዳት ብቻ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት እንዲሁም 309 ሲቪል ሰዎች ለቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል።

ለምሳሌ የትግራይ ኃይሎች ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9 00 ሰዓት አካባቢ በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ የጋሊኮማ ተራራ ላይ ሰፍረው የነበሩ የአፋር ልዩ ኃይሎችን በሚያጠቁበት ወቅት ሲቪል ሰዎችን ሳይለዩ በፈጸሙት ጥቃት 27 ሕፃናትን ጨምሮ 107 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፤ 35 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል የሚገኙ በርካታ ከተሞችን ከመቆጣጠራቸው አስቀድሞ ከተሞች ላይ በተኮሷቸው ከባድ መሳሪያዎች ሲቪል ሰዎች እንዲሞቱ እና እንዲቆስሉ አድርገዋል፤ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ የሲቪል ሰዎችን መኖሪያ ቤቶችን፣ የትምህርት፣ ጤና እና የሕዝብ አስተዳደር ተቋማትን እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትን አውድመዋል። የትግራይ ኃይሎች ከነሃሴ 12 እስከ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በደባርቅ ወረዳ የአዲጋግራ፣ የአብርሃም እና የአዳጋት ቀበሌዎችን በመያዝ፤ የአርሶ አደሮችን ቤት እንደ ምሽግ አድርገው በመዋጋታቸው በመከላከያ ሠራዊት በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች 6 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።

የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል በወረባቡ ወረዳ በቆዩባቸው ቀናት የተለያዩ ፈንጂዎችን ቀብረው እና በሜዳ ጥለው በመሄዳቸው 5 ሕፃናት ሲሞቱ፣ 1 ሕፃን አካል ጉዳት ደርሶባታል። በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ ታኅሣሥ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ በግምት 9፡00 ሰዓት ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው የነበሩ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች ላይ በፈጸመው የድሮን ጥቃት በአንድ ሕንፃ በረንዳ ላይ ሻይ ቡና፣ ምግብ፣ ውሃ የሚሸጡ በተለምዶ ‘ሱቅ በደረቴ’ በመባል የሚጠሩ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች እና አገልግሎት በመጠቀም ላይ የነበሩ 6 ሲቪል ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 4 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በሪፖርቱ ላይ በዝርዝር እንደተመለከተው የትግራይ ኃይሎች ሲቪል ሰዎችንና አካባቢዎችን እንደከለላ በመጠቀም፣ ፈንጂዎችን ያለልዩነትና ጉዳት በሚያደርስ መልክ በመጠቀም እንዲሁም ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ሲቪል ሰዎችንና ተቋሞችን ከጉዳት ለመከላከል ተገቢውንና የተሟላ ጥንቃቄ ባለማድረግ ባካሄዱት ጦርነት ለብዙ ሲቪል ሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት እና መሰረተ ልማት ውድመት እና መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል፡፡ 

ሕገወጥና ከዳኝነት ውጪ የተፈጸመ ግድያ

ኢሰመኮ ምርመራ ባደረገባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች በተለይም እና በዋነኝነት በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ተገድለዋል። የትግራይ ኃይሎች ይህን መሰሉን ሕገወጥ ግድያ ሲፈጽሙ ምክንያት ሲያደርጉ የነበረው ተጠቂዎቹን “ለመንግሥት ኃይሎች ሰላይ ናችሁ፤ የግላችሁን የጦር መሳሪያ አምጡ፤ ንብረት እንዳይወሰድ ተከላክላችኋል፤ የመከላከያ፣ የልዩ ኃይል ወይም የፋኖ ታጣቂዎችን አግዛችኋል” ወይም “የት እንዳሉ ታውቃላችሁ” ወይም “የነዚሁ አባላት የሆኑ ሰዎች ቤተሰብ ናችሁ” በሚል ምክንያትና፣ እንዲሁም አካባቢዎቹን በሚቆጣጣሩበት ወቅት በትግራይ ኃይሎች ላይ ለደረሰባቸው ጥቃት ወይም የትግራይ ታጣቂዎች እና ትግራይ ላይ ለደረሰ ሞት እና ጉዳት የበቀል/አጸፋ እርምጃ መሆኑን ጭምር በግልጽ እየተናገሩ ብዙ ሲቪል ሰዎችን በጅምላ እና በነጠላ ገድለዋል። በተመሳሳይ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ ያሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን ፈጽመዋል። በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዎችም የትግራይ ኃይሎች እና ኦነግ ሸኔ አባላት ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ሕገወጥና ከዳኝነት ውጪ የሆኑ ግድያዎችን ፈጽመዋል፤ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል።

ከሕገወጥ ግድያዎች ውስጥ ለምሳሌ፤ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ከነሃሴ 24 እስከ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በቀበሌው በቆዩበት ወቅት ቢያንስ 47 ሲቪል ሰዎችን (41 ወንዶች እና 6 ሴቶች) ገድለዋል። ሟቾች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የተረሸኑ፣ እንዲሁም ተይዘው እጆቻቸውን ወደኃላ ታስረው የተገደሉ ሲሆን በተለይም የመንግሥት ኃይሎች ወደ ቀበሌው እየተቃረቡ በመምጣታቸው የትግራይ ኃይሎች ከአካባቢው ሲያፈገፍጉ በየቤቱ እና በየሰፈሩ ያገኟቸውን ነዋሪዎች እየገደሉ ሄደዋል። በተጨማሪም በሰሜን ሸዋ ዞን በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ አሰለሌ ቀለበት ወንበር ቀበሌ አምቦውሃ ጎጥ ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ለቀብር የተሰበሰቡ ሲቪል ሰዎች ላይ በመተኮስ እና ቤት ለቤት በመግባት 40 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል። ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ አትኮማ አካባቢ የ9 ዓመት ሕፃን እና የ18 ዓመት ወጣት ሴት በትግራይ ኃይሎች ደረት እና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመትተው ተገድለዋል። በአጣዬ ከተማ የ01 ቀበሌ ኅዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም. የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የቀበሌው አመራር የነበሩ ግለሰብን አባት እና ወንድም ልጃችሁን አምጡ በሚል ከያዟቸው በኃላ ልዩ ስሙ ቆሮ ከሚባል ቦታ ላይ ገድለዋቸዋል።

በሌላ በኩል በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ ልዩ ቦታው እንቶሊ አካባቢ በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ቁጥራቸው ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎችን በጅምላ በጥይት ደብድበው ገድለዋል። ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በላስታ ወረዳ 024 ቀበሌ ዳቦ ከተማ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት የትግራይ ኃይሎችን ቀልባችኋል በሚል የተዘጋ መኖሪያ ቤት ላይ ተኩሰው አንድ እናትን ግራ እግሯ ላይ፤ ሕጻን ልጇን ደግሞ ግራ እጇ ላይ በጥይት የመቷት ሲሆን፤ ሕጻኗ ሕክምና በማጣቷ ደም ፈሷት ሞታለች። በሸዋ ሮቢት ከተማ ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎችን ደግፋችኋል በሚል አራት ወንድ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሲቪል ሰዎች በፋኖና በአርሶ አደር ታጣቂዎች ተገድለዋል።

የጭካኔ፤ ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት

የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ የአፋር እና አማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎችን ገንዘብ አምጡ፣ መረጃ አምጡ፣ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ፣ በሚሉና የመሳሰሉ ምክንያቶች በሲቪል ሰዎች ላይ በጭካኔ የመደብደብ፣ የማዋረድ እና የማሰቃየት ተግባር ፈጽመዋል። ለምሳሌ በጋሸና ከተማ ኅዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች አንድ ግለሰብን ገንዘብ እንዲሰጣቸው ለማስገደድ ከደበደቡት በኋላ በወንዝ ውሃ ውስጥ በመድፈቅ አሰቃይተዋል፤ እግሩ ላይ ሚስማር መትተው አሰቃይተዋል እንዲሁም ብልቱን በካራ ተልትለዋል። ወደ ተጎጂው ቤት በመሄድ ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላም ሚስቱን በመደብደብ አሰቃይተዋል፡፡ ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በአማራ ክልል ወረባቡ ወረዳ ቀበሌ 020 የትግራይ ኃይሎች የ20 ዓመት ወጣት እንስሳትን በመጠበቅ ላይ እያለ “የሶዶማ አካባቢ ተዋጊዎችን ትመስላለህ” በሚል ድብደባ እና ማሰቃየት ካደረሱበት በኋላ በጥይት ተኩሰው ገድለውታል፡፡ የትግራይ ኃይሎች በወረዳው 6 ቀበሌዎች ውስጥ በ10 ሰዎች (8 ወንዶች እና 2 ሴቶች) ላይ ድብደባ እና የአካል ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በቀበሌ 018 ነዋሪ የሆነ የ30 ዓመት ወጣት ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች ከቤቱ በመውሰድ እግሩን እና እጁን ገልብጠው በማሰር እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ታስሮ በቆየበት ወቅት በተለያየ ጊዜ ድብደባ የፈጸሙበት ሲሆን በድብደባውም ጉዳት እንደደረሰበት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር

የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን ድንጋጌ በሚጥስ መልኩ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር ፈጽመዋል። የትግራይ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀልን ሊያቋቁም በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን የፈጸሙ ሲሆን፣ የፌዴራል፣ አማራ እና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዐውድ ውስጥም ቢሆን የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ መሆን መርሆዎች ከሚፈቅዱት ውጪ መጠነ ሰፊ የዘፈቀደ እስር ፈጽመዋል፡፡ በአማራ ክልል ዳቦ ከተማ ኅዳር 4 ቀን 2014 ዓ.ም. “የአመራርና የሚሊሺያ ስምና ቤት ጠቁም” በማለት በትግራይ ኃይሎች የተያዘ አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ በገመድ ከዛፍ ጋር እንደታሰረ፣ ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ተፈቶ ባዶ ቤት ያለምግብ አሳድረውት፤ በነጋታው ከሌላ ታሳሪ ጋር በግዳጅ ተወስደው ታጣቂዎቹ በሚሄዱበት ሁሉ የጦር መሳሪያና ጥይት ሲያሸክሟቸው እና ውሃ ሲያስቀዷቸው ቆይተው ከሦስት ሳምንት በኋላ እንደተለቀቁ ለኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡

በአፋር ክልል ቡርቃ ቀበሌ ሙዴና አካባቢ ለገበያ የመጡ 8 ሰዎች በትግራይ ኃይሎች በግዳጅ የተወሰዱ ሲሆን ኮሚሽኑ ምርመራውን እስካከናወነበት ጊዜ ድረስ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን አያውቁም። ከታገቱ በኋላ ኢሰብአዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው እና የተገደሉም ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ኃይሎች አጣዬ ከተማን ኅዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም ሲቆጣጠሩ 01 ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አንድ ነጋዴ ቤት በመግባት እና ግለሰቡን በማገት ለ5 ቀናት ከቆዩ በኋላ አጣዬ ከተማ ቀበሌ 01 ልዩ ስሙ ኤፌሶን ቁጥር 2 ትምህርት ቤት ውስጥ ‹‹ፋኖ ትቀልባለህ፣ ወታደር ታበላለህ፣ ቤትህ የወታደር ካምፕ ነው›› በሚል ምክንያት ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች አሳልፈው ሰጥተዋቸው ኅዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጃራ ዎታ በሚባል ቦታ ላይ ተገድለዋል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ሊተባበሩ ይችላሉ፤ የፀጥታ ስጋት ናቸው በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ በተለይ የትግራይ ተወላጆችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ተፈጻሚነት ካላቸው የሰብአዊ መብቶች መርሆዎች ውጪ አስረው አቆይተዋል፤ በርካቶችም ያሉበት ሳይታወቅ፤ የቤተሰብ እና የሕግ ባለሙያ ጉብኝት ተነፍገው ለወራት ቆይተው ነበር። 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *