የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ጉዳዮች አቤቱታ ያቀረቡ ፓርቲዎች የተካተቱበት አጣሪ ኮሚቴ ባደረገው ምርመራ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከቤታቸው እንዳይወጡ የቁም እስረኛ መሆናቸውን አረጋገጠ፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓርብ የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ኅዳር 23 እና ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ፣ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ አመራሮቻቸውና አባሎቻቸው እየታሰሩ መሆናቸውን በተመለከተ በተደጋጋሚ የደረሰውን አቤቱታ የሚያጣራ ኮሚቴ አቋቁሞ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
አቤቱታዎችን የሚያጣሩ ቡድኖች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማና በኦሮሚያ ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማቋቋሙን ቦርዱ ገልጿል፡፡ አባላቱ ከገዥው ፓርቲ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁለት ባለሙያዎችና አቤቱታውን ካቀረቡት ፓርቲዎች ደግሞ አንድ ሰው መካተታቸውን ጠቁሟል፡፡ የቡድኑ ሁለት አባላት አቤቱታውን ለማጣራት አቶ ዳውድ ቤት የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 10: 00 ሰዓት ላይ በመሄድ ሁኔታውን እንዲያጣሩ መደረጉን፣ በዚህም የቡድኑ አባላት የሊቀመንበሩ መኖሪያ ቤት ሲደርሱ አንኳኩተው ለመግባት በሞከሩበት ወቅት የፀጥታ ሠራተኛ መሆናቸውን በገለጹና ሲቪል በለበሱ ሰዎች ማንም ሰው መግባት እንደማይቻል ተከልለው እንደነበር ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ማንም ሰው መግባት እንደማይፈቀድለት ለአቤቱታ አጣሪዎቹ እንደተገለጸላቸውና ገብተው ለማየት ከየት እንደመጡ፣ ለምን እንደመጡ ተጠይቀው መጨረሻ ተፈቅዶላቸው አቶ ዳውድን መጎብኘት እንደቻሉ ተገልጿል፡፡ አቤቱታ አጣሪዎቹ ከአቶ ዳውድ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት የያዙት ቦርሳ እንደተፈተሸና ስልካቸውን ይዘው መግባት እንዳልቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ በመጨረሻም አቶ ዳውድ ከመጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቤት እንዳይወጡ የታጠቁ ኃይሎች ቤታቸው ውስጥ ተመድቦባቸው የቤት ውስጥ እስረኛ ሆነው የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ መቆየቱን መገንዘቡን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
የፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ዳውድ በየትኛውም የሕግ አግባብ ተቀባይነተ በሌለው ሁኔታ የሚገኙበት የቤት ውስጥ እስር በአፋጣኝ መቆም እንዳለበት ቦርዱ ጠይቋል፡፡ በመሆኑም በአቶ ዳውድ ግቢ የተመደበው ጥበቃ እንዲነሳና የሊቀመንበሩን የመንቀሳቀስ መብት አስከብረው በአስቸኳይ ለቦርዱ እንዲገልጹ፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ደብዳቤ ጽፏል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር