የኢትዮጵያ የመንግሥት እና ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በተቃራኒው በግል የሚንቀሳቀሱ ሚድያዎች የሚደግፉትን አካል ብቻ ማዕከል አድርገው ዘገባዎችን መስራታቸው የሚድያ መልክዓ ምድሩን እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሙያን ፈተና ውስጥ አስገብተዋል ይላሉ ባለሞያዎች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2010 ዓ.ም ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ መገናኛ ብዙኃን ላይ የነበረው መነቃቃት ተስፋ የሚሰጥ ነበር ይላል የሚድያ ባለሙያ ኤልያስ መሰረት። በዚያን ወቅት የመንግሥት ሚድያዎች የተቃዋሚዎችን ድምጽ ማስተናገድ ብቻም ሳይሆን መንግሥት ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች ጭምር ሽፋን መስጠት ጀምረው ነበር። በ2011 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በአዲስ አበባ ሲከበር ኢትዮጵያ ‘አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት አገር’ ተብላ ተወድሳ ነበር። ይህ ግን ረዥም ጊዜ መቆየት አልቻለም።

የአንድ ወገን ድምጽ

በአሁኑ ወቅት “የመንግሥት እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን የፕሮፓጋንዳ ማሽን ሆነው መንግሥት የሚለውን ብቻ ሲያንፀባርቁ በስፋት ይታያል” ይላል ጋዜጠኛ ኤልያስ። ከመንግሥት የሚመጣውን መረጃም ቢሆን ለማጣራት ምንም ሙከራ ሳይደረግ ወደ ሕዝብ ይደርሳሉ የሚለው ኤልያስ፣ ለዚህም ከወራት በፊት የተፈጠረውን የከረዩ አባገዳዎች ግድያ በአስረጅነት ይጠቅሳል። በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም የከረዩ አባገዳዎች ላይ የተፈፀመው ግድያን ተከትሎ የኦሮሚያ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች በፌስቡክ ገጹ ላይ ያወጣውን መግለጫ ብቻ በመጥቀስ፣ ግድያውን መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸው እና ሸኔ የሚላቸው የኦሮሞ ነጻነት ታጣቂዎች እንደፈፀሙት እነዚህ የመንግሥት እና ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበውት ነበር።

ከሁለት ወራት በኋላ ጥር ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ግድያውን የመንግሥት አካላት እንደፈፀሙት ባደረገው ምርመራ መረዳቱን ጠቅሶ ሪፖርት አውጥቷል። ይሁን እንጂ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ይህንን ሪፖርት በዝምታ አልፈውታል። ይህም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ይህንን ጉዳዩ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ መገናኛ ብዙኃኑ የሰሩትን አንስቶ እርምት እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።

ፓርቲው ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩ የመንግሥት ሚድያዎች “ይህንን እኩይ ተግባር በተሳሳተ መንግድ የዘገቡ ሚድያዎች ሁሉ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው የኮሚሽኑን ሪፖርት አልያም በራሳቸው መንገድ የተፈጠረውን ትክክለኛ ኩነት በድጋሚ ለሕዝብ እንዲያደርሱ እንጠይቃለን” ብሎ ነበር። በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው ኦቢኤን፣ የድርጅቱ ጋዜጠኛ ሠይፉ ጉርሙ ከአንድ ወር በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በእስር ላይ ሲቆይ መገናኛ ብዙኃኑ የራሱ ጋዜጠኛ መታሰሩን ሽፋን አለመስጠቱ በድርጅቱ ባልደረቦች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።

ጋዜጠኛ ሠይፉ ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ዘገባውን ከሰሩ በኋላ በስህተት መታሰሩ ተነግሮት ተለቅቋል። ከዚህ በተጨማሪ 16 ወራት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት እና በተለያዩ የኦሮምያ ክልል ዞኖች ያለውን ግጭት ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ፈፀሙት ስለሚባለው የመብት ጥሰት እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሲሰሩ አይስተዋልም ቢሰሩም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች ያለውን ድርቅ እና እያስከተለ ያለውን ጉዳት አስመልክቶ ተገቢ ሽፋን አልሰጡትም የሚሉ ቅሬታዎችም ይሰማሉ። ለመሆኑ የመንግሥት እና ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያላቸው ሚዲያዎች የኢዲቶሪያል ነጻነታቸው ምን ያህል ነው? ጋዜጠኞቻቸውስ ዜና የሚሆን ነገር በራሳቸው ውሳኔ ላይ ተመስርተው መስራት ይችላሉ?

‘መንግሥት ይቀየመናል’

የመንግሥት እና ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ውስጥ የሚሰሩ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች፣ ራሳቸው ያቀዱትን ሳይሆን ‘ከበላይ አካል’ በመጣ ጥቆማ ወይንም ደግሞ መንግሥት ይፈልገዋል ተብለው በሚሰጧቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንደሚሰሩ አንድ በመንግሥት ሚድያ ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግሯል። ሊደርስበት የሚችልን ጫና ፍራቻ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው ይህ ጋዜጠኛ “ጋዜጠኞች ራሳቸው ያሰቡትን ነገር እንዳይሰሩ መከልከል፣ ከሰሩም ደግሞ አየር ላይ እንዳይውል ማድረግ አለ” ይላል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ወቅታዊ ሁኔታ ይገድበናል፣ ወቅታዊ ሁኔታ ይህንን እንድንሰራ አይፈቅድልንም፣ ነገር ማባባስ ይሆናል፣ መንግሥት ይቀየመናል እና ይህንን የመሳሰሉ ምክንያቶች መሆናቸውን ይናገራል።

“አንድ የመንግሥት ባለሥልጣንን ቅሬታ ወይንም ደግሞ ቅያሜ ለማስቀረት ጋዜጠኞች መሰራት ያለባቸውን ወይንም ደግሞ አንድ ጋዜጠኛ ሊሰራ ያቀደው ይቀይራል።” “ጋዜጠኞች ይህ ለምን አይሰራም ብለው ጥያቄ ካነሱ እንደ መንግሥት ተቃዋሚ ይታያሉ፤ የሚሰጣቸውም መልስ ዝም ለማስባል እና እንደዚህ አይነት ጥያቄ ደግመው እንዳያነሱ ማድረግ ላይ ትኩረት ያደርጋል” ይላል። ጋዜጠኞች ይህን ስሩ ተብለው ከኢዲቶሪያው ውሳኔ ውጪ ባሉ ሰዎች፣ ምናልባት የመንግሥት ባለሥልጣናት ርዕስ ወይንም አጀንዳ እንደሚሰጣቸው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ከሚሰሩ ጋዜጠኞች መረጃ ይደርሰው እንደነበር ጋዜጠኛ ኤልያስ ያስታውሳል።

“ጋዜጠኞች ይህ ዜና መሆን ይችላል ብለው ያሰቡት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማጣራት አድርገው ሳይሆን የሚዘግቡት፣ ከበላይ አካል የተሰጣቸውን ነገር መልሰው ማስተጋባት ብቻ ነው በስፋት የሚስተዋለው” ይላል ኤልያስ። እናም የመንግሥት ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት ሚድያውን እያቀጨጨው ነው። ይህም ሕዝቡ የተጣራ መረጃ እንዳያገኝ ያደርጋል ሲል ያክላል።

ጋዜጠና እና መጽሔት የሚያነቡ ሰዎች

‘እውነት አደጋ ላይ ወድቃለች’

ይህ በአንድ ወገን በኩል ያለን ሃሳብ ብቻ የማራገብ ሁኔታ በሌሎችም ላይ እንደሚስተዋል ኤልያስ ይጠቅሳል። ለዚህም በግል የሚንቀሳቀሱ እና በተለይ ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚድያዎችም ለሚደግፉት አካል ማዳላት እና መንግሥትን በጭፍን መቃወም ይታያል። ጋዜጠኞች የመጡበትን ብሔር፣ ሃይማኖት እንዲሁም ለፖለቲካ አመለካከታቸው በማድላት የአክቲቪዝም ሥራ ሲሰሩ ይስተዋላል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ብንሰራ መንግሥት ይቆጣል በሚል ራሳቸውን ሳንሱር የሚያደርጉ እና አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮችን ከመስራት የሚቆጠቡ ጋዜጠኞች እንዳሉም ይናገራል።

ለዚህም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣው የጋዜጠኞች እስር አስተዋጽኦ ማድረጉን ይጠቅሳል። “የታሰሩ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት መቅረብ ይቅርና የት እንደታሰሩ እንኳ ማወቅ አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ እኔም ላይ ሊደርስ ይችላል የሚል ፍራቻ ጋዜጠኞች ጋር አለ።” “በአጠቃላይ በጭፍን በመደገፍ፣ በጭፍን መቃወም እና ፈርቶ መተው” ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን የሚገልጸው ኤልያስ፣ የሚድያ ምኅዳሩ እና የጋዜጠኝነት ሙያ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ይናገራል። የሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን መምህር የሆኑት አብዲሳ ዘርዓይ (ዶ/ር) አገሪቷ በጦርነት እና በግጭት ውስጥ ያለች ከመሆኑ አንጻር እና ፖለቲካው ዋልታ ረገጥ በመሆኑ እውነት አደጋ ላይ ወድቋል ይላሉ።

የመንግሥት ሚድያዎች ነጻ እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን በጠበቀ ሁኔታ ሳይሆን እንደ ፕሮፓጋንዳ ማሽን በመንግሥት በኩል የሚነገረውን ብቻ ከፍ አድርጎ ማሰማት በስፋት ይታያል ሲሉ ያክላሉ። በግል የሚንቀሳቀሱትም ቢሆኑ፣ የሚደግፉትን ወይንም የቆሙለትን አካል በጭፍን ደግፈው ስለሚሰሩ እውነት እና ሐቀኝነት (Objectice and Truth) አደጋ ላይ ወድቀዋል ይላሉ አብዲሳ (ዶ/ር)። የመንግሥት ሚድያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ መንግሥት በሚሾማቸው ሰዎች ስለሚተዳደሩ መንግሥት እንደሚፈልገው ብቻ እንደሚዘግቡ ያስረዳሉ።

“ነጻ የሆነ ጋዜጠኛ ቢኖር እንኳ ራሱ ያየውን እና ያረጋገጠውን ነገር አምጥቶ ለመስራት ያለው እድል ጠባብ ነው፤ ቢሰራ አየር ላይ እንደሚውል ዋስትና የለውም። ስለዚህም የተሰጠውን አቅጣጫ ብቻ ጠብቆ እንዲሰራ ይገደዳል።” ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒነት እና ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ከዚህም አልፎ ኅብረተሰቡ እውነትን በትክክል ተረድቶ ትክክለኛ አቋም እንዳይዝ፣ ትክክለኛ ውሳኔ እንዳይወስን እንዲሁም ተጠያቂነት ማስፈን እንዳይችል ያደርጋ ይላሉ አብዲሳ ዘርዓይ (ዶ/ር)።

‘ፖለቲካው መስተካከል አለበት’

መገናኛ ብዙኃን በአንድ አገር ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ የሚበቅል ነው የሚሉት የሚድያና ኮምዩኒኬሽን ምሁሩ፣ ይህ ሁኔታ እስካልተቀየረ ድረስ ሚድያውን መቀየር እንደማይቻል ያስረዳሉ። የሚድያው ምኅዳር ውስጥ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ዋልታ ረገጥ የሆነው ፖለቲካ ወደ መካከል መምጣት እና መስተካከል መቻል አለበት ሲሉም ያክላሉ። “አንድ ሚድያ ወይንም ደግሞ አንድ ጋዜጠኛ ታዳሚ ለማግኘት ጆሮን የሚስብ ነገር ማቅረብ አለበት። አሁን ባለው የአገሪቱ ሁኔታ ደግሞ ታዳሚው ዋልታ ረገጥ የሆነ ፖለቲካ ሰለባ ስለሆነ ጋዜጠኛው ወይንም ደግሞ ሚድያው የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባር ተከትሎ ለመስራት ይቸገራል። ስለዚህም ከጋዜጠኛ ብዙም የምንጠብቀው ነገር ላይኖር ይችላል” ይላሉ አብዲሳ (ዶ/ር)።

የሚድያ ባለሙያው ኤልያስ በበኩሉ፣ በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙኃን የኢዲቶሪያል ነጻነታቸውን ጠብቅው እንዲሰሩ መፈቀድ አለበት ይላል። የሚድያ ማኅበራት ደግሞ የሚድያ ነጻነት እንዲኖር ጫና ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም ሚድያዎች ራሳቸው እና የሚድያ ልማት ላይ የሚሰሩ ተቋማት የጋዜጠኞች የሙያ ብቃት ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ሌላው አስፈላጊ ነገር መሆኑን ይጠቅሳል። በዚህ ዘገባ ላይ የተለያዩ የመንግሥት እና ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያላቸው የመገናኛ ብዙኃንን ሐሳብ ለማካተት ብንሞክርም ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። ለኢትዮጵያ መገናና ብዙኃን ባለሥልጣን ኃላፊዎችም በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም አግኝተን ሐሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *