በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ህዳጣን ብሔረሰቦችን ‹‹መብት የሚጥሱና ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረኑ›› የተባሉ በስምንት ክልሎች ሕገ መንግሥቶች ውስጥ የሚገኙ አንቀጽና ንዑስ አንቀጾች እንዲሻሩ፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጥያቄ ቀረበ፡፡ ጥያቄ የተነሳባቸው በሶማሌ፣ በአፋር፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በጋምቤላ ክልሎች ሕገ መንግሥቶች ውስጥ የሚገኙ አንቀጾችና ንዑስ አንቀጾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከሱማሌ፣ ከደቡብና ከጋምቤላ ክልሎች ውጪ ያሉት ሌሎች የተጠቀሱ ክልሎች ሕገ መንግሥት መግቢያም አቤቱታ ቀርቦበታል፡፡

ጥያቄውን ያቀረበው የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘ አገር በቀል የሲቪል ማኅበር፣ በአቤቱታው ላይ የተጠቀሱ የሕገ መንግሥቶቹ ክፍሎች በክልሎቹ ውስጥ የሚኖሩ ህዳጣን ማኅበረሰቦችን የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶች የሚገድቡ ስለመሆናቸው በጥር ወር ለጉባዔው ባስገባው የ15 ገጽ ማመልከቻ አብራርቷል፡፡ የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አንድ የሚጠቅሰው አቤቱታው፣ ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሕግ መሆኑንና ማናቸውም ሕጎች፣ ልማዳዊ አሠራሮችና ውሳኔዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው መደንገጉን ያስረዳል፡፡ ይሁንና ማመልከቻው፣ አብዛኛዎቹ የክልል ሕገ መንግሥታት በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ጥበቃ የተደረገላቸውን ሰብዓዊ መብቶች “እንዲሸራርፉ” እና “እንዲጣሱ” ምክንያት ሆነዋል የሚል ወቀሳውን አቅርቧል፡፡

ወቀሳው ከቀረበባቸው የሕገ መንግሥታቱ ክፍሎች ውስጥ አንዱ የሆነው የክልሎቹ ሕገ መንግሥት መግቢያዎች አግላይ እንደሆኑና የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 25፣ 32፣ 38፣ እና 40ን እንደሚቃረኑ እንደሆኑ አቤቱታው አስረድቷል፡፡ ‹‹መግቢያዎቹ የክልሉን ባለቤትነት ጭምር በስም ለተጠቀሰው/ሱት ብሔርና ብሔረሰቦች ብቻ የሚሰጡና ሌሎች በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችን (ብሔር ብሔረሰቦችን) ዕውቅና የማይሰጡ፣ የሚያገሉና እንደ ሌላ አገር ዜጋ የሚቆጥሩ ናቸው፤›› የሚል ገለጻ በአቤቱታው ተገልጿል፡፡

በዚህም ምክንያት የሕገ መንግሥቶቹ መግቢያዎች በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የተደነገጉትን የእኩልነት፣ የመዘዋወርና በመረጡት የአገሪቱ ክፍል የመኖር፣ የመምረጥና የመመረጥ እንዲሁም የንብረት መብቶች “የሚቃረኑ” በመሆናቸው፣ ጉባዔው “ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም” በማለት የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲልክ ተጠይቋል፡፡ የትግራይ፣ የአማራና የደቡብ ክልሎች ሕገ መንግሥቶች “ኢሕገ መንግሥታዊ” ተብለው ከተጠቀሱት ክልሎች በተቃራኒ አግላይ የሆነ አገላለጽን የማይጠቀሙና በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ሁሉ የሕገ መንግሥቱ መሥራቾች አድርገው የሚቆጥሩ ስለመሆናቸው በማመልከቻው ላይ ተጠቅሷል፡፡

በሕገ መንግሥቶቹ ላይ የተነሳው ሌላው ቅሬታ፣ ‹‹የሕዝብ ወሳኝነትን ሥልጣን የየክልሉ ባለቤት ሆነው ለተጠቀሱ ብሔር ብሔረሰቦች ብቻ የሚሰጡ፣ በየክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ዜጎችን ወይም ብሔር ብሔረሰቦችን ፖለቲካዊ መብቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ሰብዓዊ መብቶቻቸውን የሚገድቡና የሚጥሱ ናቸው፤›› የሚል ነው፡፡ የክልል ሕገ መንግሥታት ለሁሉም በክልላቸው ለሚኖሩ ዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚሰጡ ድንጋጌዎች ቢኖሯቸውም፣ የክልል የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ በስም የተጠቀሱት ብሔርና ብሔረሰቦች ብቻ በመሆኑ በክልሎቹ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች ትክክለኛ (Genuine) የፖለቲካ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደማይችሉ በአቤቱታው ውስጥ ተካቷል፡፡

የክልል ሕገ መንግሥታቱ በክልላቸው ላለው ብዝኃነት “ዕውቅና አይሰጡም” የሚለው አቤቱታው የክልል ነዋሪዎችን “ባለቤት” እና “ባለቤት ያልሆኑ” ተብለው መከፋፈላቸውን ያስረዳል፡፡ ‹‹አሁን በየዕለቱ ለምናየው የዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ መደፈር፣ መፈናቀል፣ የንብረት መውደም፣ ብሎም በአጠቃላይ የሰላም ዕጦትና የሰብዓዊ መብት ቀውስ ምክንያት ሆኗል ብለን እናምናለን፤›› የሚል ሐሳብ ለአጣሪ ጉባዔው በቀረበው አቤቱታ ላይ ሠፍሯል፡፡

እነዚህንና ሌሎች ምክንያቶችን ያቀረበው አቤቱታው ጉባዔው የተጠቀሱት የሕገ መንግሥቶች መግቢያዎችና አንቀጾች ሕገ መንግሥታዊነት ተጣርተው ኢሕገ መንግሥታዊ እንዲባሉ ጠይቋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጉባዔው፣ ‹‹የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት ኢሕገ መንግሥታዊ የተባሉትን ድንጋጌዎች በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ መሠረት ማስተካከያ እንዲያደርጉባቸው እንዲታዘዝ የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲልክልን፤›› የሚል ሐሳብ በአቤቱታው ተመልክቷ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኢ ሕገ መንግሥታዊ እንዲባሉ የተጠየቁ የክልል ሕገ መንግሥታትን መሠረት አድርገው የወጡ ሌሎች የክልል ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና አሠራሮች ሕገ መንግሥታዊነትን መርምሮ ውጤቱን በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርብ የባለሙያዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም እንዲታዘዝ፣ አጣሪ ጉባዔው የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲልክ ተጠይቋል፡፡

ክልሎች ሕገ መንግሥት በሚያወጡበት ወቅት ከግምት ሊያስገቧቸው የሚገባቸውን ሕገ መንግሥታዊ መርሆች በግልጽ አለመቀመጣቸው ያስረዳው አቤቱታው፣ በዚህም የተነሳ የክልል ሕግ መንግሥታት አረቃቅ ‹‹ግልጽነት የጎደለውና ለተለያዩ ፖለቲካዊ ጫናዎች የተጋለጠ›› እንደሆነ ገልጿል፡፡ ስለዚህም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሎች ሕገ መንግሥት በሚያወጡበት ወይም በሚያሻሽሉበት ወቅት፣ ከግምት ሊያስገቡት የሚገባ ግልጽ የሆኑ ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን እንዲቀመጡ ተጠይቋል፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቢነት የሚመራው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን ለመተርጎም ሥልጣን ለተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን እያጣራ የሚያቀርብ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አዋጅ አንቀጽ አምስት ንዑስ አንቀጽ ሦስት በፌዴራሉም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ወይም ባለጉዳይ ለአጣሪ ጉባዔው ሊያቀርብ እንደሚችል ደንግጓል፡፡

አሥራ አንድ አባላት ያሉት ጉባዔው የሕግ ባለሙያ የሆኑ ስድስት አባላቱን ታኅሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሾመ በኋላ፣ አዲስ የተሾሙት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላት የተገኙበት የመጀመርያው ጉባዔ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ በዕለቱም አጣሪ ጉባዔው በሦስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጉባዔው ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ተጠባባቂ ዳይሬክተር ይርጋለም ጥላሁን ጉዳዮች ወረፋ ይዘው በቅደም ተከተላቸው እንደሚታዩ ገልጸው፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች በተሰኘ የሲቪል ማኅበር የቀረበ ጥያቄ ለጉባዔው አለመቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *