ኢትዮጵያ ዘንድሮም በከባድ የድርቅ አደጋ ተጠቅታለች፡፡ በኢትዮጵያ ዘንድሮም ስለረሃብ አደጋ ይወራል፡፡ ዘንድሮም እንስሳት በውኃና በምግብ እጥረት ይረግፋሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ የካቲት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ከመሸ ባወጡት መግለጫ እንዳስረዱት ከሆነ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ዘንድሮም ሕፃናትና አረጋዊያን በድርቅና በረሃብ አደጋ እየረገፉ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በረሃብ አለንጋ የዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈ ነው ካሉ በኋላም ቢሆን ድርቁ ረሃብ አስከትሎ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ አልጠፋም የሚለውን ጉዳይ የማይቀበሉ ወገኖች ቢኖሩም ነገር ግን ድግግሞሹ እየበዛ በመጣው ድርቅ የደረሰው ውድመት ቀላል አለመሆኑን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

ሌላውን ቀርቶ የመንግሥት ተቋም የሆነውን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር  ኮሚሽንን መረጃ ብቻ እንኳ ቢገላበጥ ዘንድሮ የደረሰው የድርቅ አደጋ ያመጣው ጉዳት እጅግ ሰፊ ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ ኮሚሽኑ እንደሚለው ድርቁ በሁለት ክልሎች በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአምስት ዞኖች ማለትም በቦረና፣ በጉጂ፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በምሥራቅ ሐረርጌና በባሌ ድርቁ ተከስቷል፡፡ በክልሉ 40 ወረዳዎች በደረሰው ድርቅም 8,469,213 ከብቶች በድርቁ ተጠቅተዋል፡፡ ከ173,55 በላይ ሞተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 257,563 ከብቶች ደግሞ አቅም አጥተው በሰው ድጋፍ ለመንቀሳቀስ ተዳርገዋል፡፡

ከከብቶች በተጨማሪም በ70 ወረዳዎችና በ605 ቀበሌዎች ውስጥ በውኃ እጥረት የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በምዕራብ አርሲና አርሲ፣ በጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ በበባሌና ቦረና የድርቅ ተጎጂዎች ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ 2.8 ሚሊዮን ሕዝብ የውኃ አቅርቦት ይፈልጋል በማለት ያስረዳል የኮሚሽኑ ሰሞነኛ መግለጫ፡፡

በቦረናና በምሥራቅ ባሌ ዞኖች 61 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ በዚህ የተነሳም 9,938 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተለያይተዋል፡፡ ድርቁ ባስከተለው ተፅዕኖ የተነሳ በአጠቃላይ በቦረና፣ በጉጂ፣ በባሌ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ከ3.1 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይሻል ይላል ኮሚሽኑ በመረጃው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 800,244 አዲስ የድርቅ ተጠቂዎች መሆናቸውን ነው የተቋሙ መረጃ ያመለከተው፡፡

ኮሚሽኑ የሶማሌ ክልል የድርቅ ጉዳትን አድማስ ሲያመላክት ከ11 ዞኖች ዘጠኙ በድርቅ ተጠቅተዋል ነው የሚለው፡፡ በዚህም ወደ 3.15 ሚሊዮን ሕዝብ ለውኃ እጥረት ተጋልጧል ይላል፡፡ በ83 ወረዳዎች 1,767 ቦታዎች አፋጣኝ ውኃ የማቅረብ ሥራ ይጠይቃል ሲልም ያክላል፡፡

በሶማሌ ክልል ያጋጠመው ድርቅ ከሐምሌ እስከ የካቲት ባለው ጊዜ ብቻ 864 ሺሕ 43 ከብቶች ሞተዋል ሲልም አስደንጋጭ መረጃ ኮሚሽኑ ይሰጣል፡፡ በዳዋ፣ በሸበሌ፣ በአፍዴር፣ በቆራሄ፣ በሊበን፣ በኤረር፣ በጆሎ፣ በጀረር፣ በፋፈንና በኖጎብ በከባድ ሁኔታ የድርቁ ተጠቂ አካባቢዎች ሲሆኑ፣ በርካታ ከብቶች የሞቱት ደግሞ ከዳዋ ዞን ነው በማለትም ያስረዳል፡፡ በዳዋ ዞን ብቻ 447,597 ከብቶች ሞተዋል በማለት ነው መረጃው የአደጋውን ክብደት የሚያስቀምጠው፡፡

በሶማሌ ክልል በቅርብ በተገኘ መረጃ 58 ሺሕ 305 ቤተሰብ በድርቅ መጠቃቱ እንደተረጋገጠ መረጃው ይጠቁማል፡፡ እነዚህ የድርቅ ተጎጂዎች ደግሞ መኖሪያ ቀዬአቸውን ጥለው ወደ ባቢሌ፣ ጉርሱም፣ ቱሉ ጉሌድና ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሰደዳቸውን ይጠቁማል፡፡ በድርቁ የተነሳ የ915 ትምህርት ቤቶች ትምህርት የተስተጓጎለ ሲሆን 316 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ፣ 599 በከፊል ተዘግተዋል በማለት የኮሚሽኑ መረጃ ያስታውቃል፡፡ ከ152 ሺሕ 652 በላይ ተማሪዎች በድርቁ በዚህ ሳቢያ ተጎድተዋልም ይላል፡፡

በአጠቃላይ ደግሞ ድርቁ በሶማሌ ክልል ወደ 2.4 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት አጋልጧል፡፡ ድርቁ ከመከሰቱ በፊት በመደበኛነት የዕርዳታ ጥገኛ ሆኖ የሚኖረው ሕዝብ በክልሉ ከፍተኛ መሆኑን የሚያስረዳው ኮሚሽኑ፣ አሁን ደግሞ ድርቁ በዘጠኙ ዞኖች 960 ሺሕ ተጨማሪ ሕዝብ ለችግር መዳረጉን ነው የተናገረው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ደግሞ በክልሉ ያለውን የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂ ሕዝብ ቁጥር ወደ 3,360,000 እንዲያሻቅብ አድርጎታል ይላል የኮሚሽኑ ሰሞነኛ መረጃ፡፡

ለዚህ ሁሉ የድርቅ ተጎጂ ማኅበረሰብ እየቀረበ ስላለው ዕርዳታና ድጋፍ ኮሚሽኑ እንደሚዘረዝረው ከሆነ በቂ ባይሆንም፣ በመንግሥትና በለጋሾች የተለያዩ ርብርቦች እየተደረገ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡ ለቦረናና ለምሥራቅ ባሌ ዞኖች 254 ሺሕ ኩንታል እህል ለ853,791 ተረጂዎች በመንግሥት በኩል እንዲሠራጭ ተደርጓል ይላል ኮሚሽኑ፡፡ ለተቀሩት 1.8 ሚሊዮን የድርቅ ተጠቂዎች መደበኛ የዕርዳታ ሥርጭት አለን የሚለው ተቋሙ፣ በዚህ መደበኛ ዕርዳታ ማሠራጫ መንገድ በኩል ዕርዳታው እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የድርቅ ተጎጂ ለሆኑ አካባቢዎች የውኃ አቅርቦት እየተደረገ ሲሆን፣ በ100 የውኃ ማመላለሻ ቦቴዎች ለተጎጂዎች ውኃ እንዲቀርብ በመደረግ ላይ ይገኛል በማለት መረጃው ያትታል፡፡

በሶማሌ ክልል ስለሚደረገው የዕርዳታ አቅርቦት ርብርብ በሚመለከት ሙሉ ለሙሉ በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል እየተሸፈነ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ ያመለከተው፡፡ በኢትዮጵያ አደጋ ሲከሰት የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኅብረትና የኢትዮጵያ መንግሥት ናቸው ዕርዳታ የሚሰጡት ይላል ኮሚሽኑ፡፡ በዚህም መሠረት በሶማሌ ክልል የዕርዳታ አቅርቦት ሥራው አሁን  እየተሠራ ያለው ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ነው ይላል፡፡

‹‹እንደ መንግሥት እኛም ስንጠየቅ ዕርዳታ እንሰጣለን፤›› የሚለው ኮሚሽኑ፣ ከዚህ አንፃር ለክልሉ ከመስከረም እስከ ጥር 550 ሺሕ ኩንታል እህል ተመድቦ 530 ሺሕ ኩንታሉ ለ1.7 ሚሊዮን ሕዝብ በመዳረስ ላይ ይገኛል ሲል አስታውቋል፡፡ በ15 ወረዳዎች ለ311 ሺሕ ተጠቃሚዎች 215 ሚሊዮን ብር እንዲከፋፈል ተደርጓል በማለትም ኮሚሽኑ ያክላል፡፡ በሶማሌ ክልል በአሁኑ ጊዜ 159 የውኃ ቦቴዎች ተመድበው ለ81 ወረዳዎች ውኃ እያቀረቡ መሆናቸውን፣ በሌላ በኩል ለ40 ተጨማሪ ወረዳዎች 26 ሺሕ ኩንታል ምግብ መሠራጨቱን የሚገልጸው ኮሚሽኑ፣ ለ36 ወረዳዎች ደግሞ 36,900 ቤል (የሳር ክምር) ተሠራጭቷል ሲልም ይገልጻል፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነት የተጠቃች አገር ናት፡፡ ባለው ግምት መሠረት የድርቁ ተፅዕኖ የሚቀጥል ነው የሚሆነው የሚለው የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ይህን ከባድ አደጋ ደግሞ በመንግሥት ምላሽ ብቻ መቋቋም የሚቻል ባለመሆኑ፣ ‹‹መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ለጋሽ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው የምንጠይቀው፤›› ሲል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡

በድርቁ የተነሳ ረሃብ ተከስቷል እንዲሁም ሰው በረሃብ እየሞተ ነው የሚለውን ሪፖርት እንደማይቀበለው ያስታወቀው የአደጋ ሥጋት ዝግጁነት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ነገር ግን የእንስሳት ሞት ከፍተኛ መሆኑን ነው በቁጥር በማስደገፍ የዕርዳታ ጥሪ ያቀረበው፡፡ ተቋሙ አሁን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ለሁሉም ተጎጂዎች በመቅረብ ላይ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ይህ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሩት፣ እንዲሁም ድርቁ ያጠቃቸው ክልሎች ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከሚያወጡት መረጃ የሚቃረን ቢሆንም፣ የድርቁን አሳሳቢነት በተመለከተ ለመጠቆም የማያንስ መረጃ ነው፡፡ ሰው ሞቷል/አልሞተም የሚለውን ክርክር ለፖለቲከኞቹ ተወት በማድረግ ሁኔታው ሲታይ፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር አሳሳቢ የሆነ የድርቅ ችግር ዘንድሮም ገጥሟታል የሚለውን ጉዳይ መረዳትም ሆነ አጉልቶ ማንሳት ይቻላል፡፡

ይህን ተከትሎ ደግሞ ድርቅን መቋቋም ያቃተን ለምንድነው? ከዝናብ ጥገኝነት ግብርናና ከብት ዕርባታ ያልተወጣው በምን ምክንያት ነው? እንዲሁም ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት ለ30 ዓመታት ሲሠራ የቆየው የግብርና መር ኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ኢትዮጵያዊያንን አጥግቦ ማሳደር እንዴት ተሳነው? የሚሉ ወሳኝ አገራዊ ጥያቄዎችን ለማንሳት ጉዳዩ መንደርደሪያ መሆን የሚችል ነው፡፡

የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ጥያቄ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሦስቴ በልቶ ማደር የሚችልበትን ጊዜ ቅርብ አድርገው የተመኙ ብዙ ነበሩ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን ሕዝባቸው በቀን ሦስቴ በልቶ ለማደር እንደሚበቃ ተመኝተው ነበር፡፡ ‹‹ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን›› ብለው በመናገራቸው የሚታወሱት ከእሳቸው በፊት የነበሩት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም (ኮሎኔል) ሕዝባቸው ጠግቦ ሲያድር ለማየት ይመኙ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከሁለቱም በኋላ የመጡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም እ.ኤ.አ. በ2014 በኢትዮጵያ ድርቅ ቢከሰትም፣ ሕዝቧ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ለሞት እንደማይዳረግና በቂ የምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት አገሪቱ መገንባቷን አስታውቀው ነበር፡፡

ሆኖም የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥት ኢትዮጵያ ድርቅን የመቋቋም አቅሟ ማደጉንና በራሷ ለሚገጥማት ችግር ምላሽ የመስጠት ችሎታዋ መጠናከሩን ከተናገረ ሁለት ዓመት ሳይቆጠር ግን፣ አገሪቱ ከባድ የድርቅ አደጋ ደረሰባት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 የደረሰው ከባድ ድርቅ ወደ አሥር ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት ዳረገ፡፡ በ50 ዓመታት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የተባለው ይህ ድርቅ ኤልኒኖ በተባለ የአየር ፀባይ ለውጥ መከሰቱ ተነገረ፡፡ ይህን ጊዜ ተገነባ የተባለው የመንግሥት ምላሽ አሰጣጥ አቅምና የድርቅ ተፅዕኖ መከላከል ሥራ በከባዱ ተፈተነ፡፡

በመደበኛነት ለምግብ እጥረት ከሚዳረገው ሕዝብ ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ እስከ 14 ሚሊዮን ሕዝብ ተራበ የሚል ዘገባን የፈጠረው የያን ጊዜው ችግር መልሶ ጋብ አለ ሲባል ደግሞ፣ በሁለት ዓመቱ የተከሰተ ሌላ ድርቅ ወደ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ ማጥቃቱ ተነገረ፡፡ ይህን ጊዜ ላኒና የተባለ የአየር ፀባይ ለውጥ ለድርቁ ሰበብ ሆኖ ቢቀርብም፣ ነገር ግን የአገሪቱን የድርቅ አደጋ የመቋቋም አቅምን ጉዳዩ ፈተና ውስጥ መክተቱ አልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ የታሪክ ሒደት ታልፎም ዘንድሮ ከባድ የድርቅ አደጋ አገሪቱ ያጋጠማት ሲሆን፣ አሁን የተከሰተውም ቢሆን እንደ ቀደምቶቹ ሁሉ የመንግሥትን አቅም የፈተነ ሆኗል፡፡

ድርቅ የተፈጥሮ ችግር ቢሆንም ኢትዮጵያ ይህን የመሰለ አደጋ ለመቋቋም ያላት ዝግጅት ዘንድሮም ማጠያየቁ ቀጥሏል፡፡ ድርቅን ለመቋቋም አገሪቱ የፈጠረችው አቅም ብቻ ሳይሆን፣ ድርቅን ተከትሎ ከሚመጣ ችግር በዘላቂነት ለመውጣት የዘረጋችው ሥርዓት ዘንድሮም ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ አገሪቱ ካለፉ አደጋዎች ያካበተችው ልምድና ተሞክሮም ማነጋገር የቀጠለ ሲሆን፣ ከዚህ በላይ ደግሞ ልክ እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያዊያን ጠግበው ማደር የሚችሉት መቼ ነው የሚሉ ተለምዷዊ የሚመስሉ ጥያቄዎችም የወቅቱን አደጋ ተንተርሰው በመነሳት ላይ ይገኛሉ፡፡

በቅርቡ በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  ድርቁን በጊዜያዊነትና በዘላቂነት ለመቋቋም ያስችላሉ ያሏቸውን ሥራዎች ገልጸው  ነበር፡፡ ለድርቁ የአጭር ጊዜ መፍትሔው የዕለት ደራሽ ምግብ፣ አልሚ ምግብ፣ ክትባትና መሠረታዊ አቅርቦቶችን ለተጎጂዎች ማቅረብ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በዘላቂነት ድርቁን ለመከላከል ያስችላል የሚሉትን በተመለከተ ደግሞ ውኃ አያያዝና አጠቃቀም ላይ መሥራት፣ የግብርና ምርቶችን የገበያ ትስስር ማጠናከር፣ እንዲሁም ደመናን በማጎልበት ሰው ሠራሽ ዝናብን ማሳደግ መሆኑን አብራርተው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተ ቁጥር ዘላቂ መፍትሔ እየተባሉ ከሚቀመጡ ጉዳዮች ብዙዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነካክተዋቸዋል፡፡ በየጊዜው ድርቅና ረሃብ አጋጠመ በተባለ ቁጥር የውኃ አያያዝና የመስኖ ልማት መፍትሔ ነው ሲባል መስማቱ አዲስ አልነበረም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ ምርትና ምርታማነት የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን ተከትሎ ማደግ እንዳለበት ሲጠቆም ይሰማል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች ሲንፀባረቅ እንደሚደመጠውም ኢትዮጵያ የምታመርተው ምርት ሕዝቧን አጥግቦ ማደር የማይችል ነው የሚለው ጉልህ ነጥብ ነው፡፡ ምርትና የሕዝብ ቁጥር አልመጣጣን ስላለ ነው አገሪቱ የምግብ እጥረት እየገጠማት ያለው የሚለው ጉዳይ፣ የድርቅ አደጋ በገጠማት ቁጥር በብዙዎች ተደጋግሞ የሚቀርብ አመክንዮ ሆኗል፡፡

እነዚህን የድርቅ አደጋውን የተንተራሱ ጥያቄዎች በማቅረብ ሪፖርተር ከተለያዩ ባለሙያዎች ምላሽ ያሰባሰበ ሲሆን፣ አስተያየታቸውን ያጋሩ ሰዎችም የተለያዩ ምልከታዎችን አስቀምጠዋል፡፡

አንጋፋው የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የምታመርተው ሕዝቧን መቀለብ የማይችል ነው የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉትም፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ እንናገራለን በዚህ ጉዳይ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የአገሪቱን ሁሉንም ሕዝብ ለመቀለብ በሚል ማምረት የለብንም፡፡ ይህን ለማድረግ ግዴታ እንደሌለብን ነው ሳይንሱም የሚመክረው፤›› በማለት ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ በእሳቸው እምነት መግዛት እስከተቻለ ድረስ በቂ ምርት ባይመረት ችግር የለውም፡፡ ደምስ (ዶ/ር) እንደሚሉት ያደጉና የበለፀጉ አገሮችም በሕዝባቸው ልክ አያመርቱም፡፡

‹‹እነሱም አፍሪካ ውስጥ የሚተራመሱት የሚመገቡትን ለማግኘት ነው፡፡ በማምረት ይለካ ከተባለ የኢትዮጵያ ምርት (ግሬን ኢኩዊቫለንስ) ቢለካ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የሚተናነስ ሆኖ አይገኝም፡፡ ነገር ግን ማምረት ብቻ ሳይሆን የተመረተው እኔና አንተ ቤት በአግባቡ በሚፈለገው ልክ መድረስ አለበት፡፡ አሁን በዚህ ጊዜ አርባምንጭ ሆኜ ነው የምታነጋግረኝ፡፡ እዚህ እስክደርስ በመንገድ ላይም ብዙ ነገር እያየሁ ነው የመጣሁት፡፡ ከዚህ በፊትም ተሞክሮ የሆነ ነገር ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ቤንች ማጂ አካባቢ ምርታማነት ለማሳደግ ተባለና ማዳበሪያና ልዩ ልዩ የምርት ግብዓት ቀረበ፡፡ ገበሬዎቹ ካመረቱ በኋላ በኬሻ ጭነው በቆሎውን ቢወስዱም ገበያ አጡ፡፡ ገበሬው አህያዬ ለምን ትደክማለች እያለ ምርቱን ሜዳ ላይ አራግፎ ኬሻውን ይዞ ተመለሰ፤›› ሲሉ ደምስ (ዶ/ር) የውጭና የቀደሙ ልምዶችን አጣቅሰው አስረድተዋል፡፡

አዲስ አበባ በኪሎ ከ30 ብር በላይ የሚሸጠው ሙዝ እሳቸው ያሉበት አርባምንጭ በአሥር ብር እየተሸጠ መሆኑን በአብነት ያወሳሉ፡፡ ‹‹እኛ ከላይ ሆነን ስናየው ምርትና ምርታማነት ብለን ሐሳብ እንሰጣለን፤››  የሚሉት ባለሙያው፣ ነገር ግን ለአንድ ገበሬ ምርትን ማሳደግ ግቡ ሊሆን አይችልም ይላሉ፡፡ ‹‹ገበሬው ባመረተው ምርት ገበያ አግኝቶ ገቢው እንዲያድግና ኑሮው እንዲሻሻል ነው በመሠረታዊነት የሚፈልገው፡፡ ገበያው ለገበሬው ምላሽ ካልሰጠው ምርታማነትን በእጥፍ ብትጨምር ብክነት ነው የሚሆነው፤›› በማለትም ደምስ (ዶ/ር) ሐሳባቸውን ያክላሉ፡፡

‹‹እኛ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ‹ዌስት ሳይክል› እንለዋለን ይህንን፡፡ በዚህ አግባብ ካየነው አምራቹ የሚቀጥለውን ምርት የሚወስነው ገበያውን ዓይቶ ነው፡፡ ገበያው ምላሽ ካልሰጠው በሚቀጥለው አያመርትም፡፡ በሚቀጥለው ካላመረተ ደግሞ እጥረት ይፈጠራል፡፡ እጥረት ከተፈጠረ ደግሞ ዋጋው ስለሚያድግ ደግሞ ለማምረት ይሞክራል፡፡ ሲያመርት ደግሞ ሌላ የገበያ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ይህን እሽክርክሪት ነው እንግዲህ የብክነት አቁሪት ብለን የምንጠራው፤›› ሲሉ ነው የግብርና ኢኮኖሚ ምሁሩ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ምርታማነትና ገበያ መተሳሰር እንደሚኖርባቸው ያሳሰቡት፡፡ በእሳቸው እምነት ምርትና ምርትን መጨመር በግብርናው ግብ መሆን የለበትም፣ ላመረቱት ምርት ገበያ የማግኘት ጉዳይ እንጂ፡፡

ሁለት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በመታጣታቸው ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ በሶማሌና በኦሮሚያ አርብቶ አደር አካባቢዎች የድርቅ አደጋ መድረሱ አይዘነጋም፡፡ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ወይም ሳምንታት የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ ለእነዚህ አካባቢዎች መድረስ ካልቻለ፣ ያጋጠመው የድርቅ አደጋ ጉዳቱም ሆነ አድማሱ ይሰፋል መባሉ ከሁሉ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የወቅቱ አሳሳቢ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ የድርቅና የረሃብ አደጋ የሚያጠላባት ለምንድነው? በዘላቂነት ከድርቅ አደጋ የምትወጣው መቼ ነው? ሕዝቧን መግባ ማደር ያቃታት በምን ምክንያት ነው? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ምላሽ ማፈላለግ ብቻ ሳይሆን አደጋው ከመከሰቱ በፊት ችግሮችን ለመከላከል የሚደረጉ የትንበያና ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ጉዳይም ማጠያየቅ አስፈላጊ መሆኑ ይታመንበታል፡፡

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት  ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ እንደሚናገሩት፣ በአገሪቱ የአደጋ ቅድመ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እጅግ ኋላቀር በሚባል ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ ‹‹አንድ ብር በአደጋ ሥጋት ቅድመ ትንበያ ላይ ኢንቨስት ብናደርግ ኖሮ በአደጋ ልናጣ ከምንችለው እስከ ሰባት ብር ለማዳን እንችላለን፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ደበበ፣ ነገር ግን ቅድመ ማስጠንቀቂያም ሆነ ቅድመ ትንበያው ደካማ በመሆኑ ችግሩ ተደጋግሞ እንደሚከሰት ያስረዳሉ፡፡

አቶ ደበበ እንደሚሉት የእሳቸው ተቋም ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚያገኘውን ሪፖርት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ብሎ ከማስታወቅ በዘለለ የሚያደርገው ብዙም ሥራ የለም፡፡ የአደጋ ቅድመ ትንበያ ሥራው ብዙ መሥሪያ ቤቶችን ከሚቲዎሮሎጂ ጀምሮ የግብርና ተቋማትንና ሚዲያዎችን ያሳተፈ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ያስተባበረ ሊሆን ይገባል፡፡ በሌሎች አገሮች ይህ ዘርፍ ውጤታማ መሆኑን ኬንያና ቻይናን አጣቅሰው የሚናገሩት አቶ ደበበ፣ ኢትዮጵያ በዚህ በኩል የዘመነ ሥርዓት ባለመከተሏ ድርቅ መሰል አደጋዎች ጉዳት መስፋቱን አስረድተዋል፡፡

ከአደጋ ማስጠንቀቂያና ትንበያ ዝመና በተጨማሪ በግብርናው ዘርፍ የተሻሻለ የአስተራረስ ዘዴን መከተልና እንደ መስኖ ያሉ ሥራዎችን ማስፋፋት፣ በኢትዮጵያ ለምግብ ዋስትና አማራጭ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሰሞኑ በቀረበ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዳጉ የውይይት ፕሮግራም ላይ ማብራሪያ የሰጡት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማሜ ጋሩማ የመስኖና ዘመናዊ እርሻ ልማት ለምግብ ዋስትና ወሳኝ አማራጮች ሆነው መተግበር መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹በመስኖ የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ባህላዊ መስኖዎች፣ አነስተኛ መስኖዎችና በዘርፉ የተጀመሩ ትልልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እየሆኑ ናቸው፡፡ ዘንድሮ 16 ሚሊዮን ሔክታር ስንዴ በመስኖ ለማልማት አስበን ዕቅዳችንን አሳክተናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቢያንስ 50 ወይም 75 በመቶ ከውጭ የሚገባን ስንዴ ያስቀርልናል፡፡ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከውጭ የሚገባ ስንዴን የሚያስቀር ምርት በራሳችን ለማምረት እንችላለን፡፡ ካቻምና 20 ሺሕ ሔክታር በበጋ መስኖ ስንዴ አልምተናል፡፡ አምና ደግሞ 16 ሺሕ ሔክታር አርሰናል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ 400 ሺሕ ሔክታር አልምተናል፡፡ ከዚህ ያገኘነው ልምድ እንደሚያሳየው በቀጣይ ዓመታት ከዚህ በተሻለ ማምረት እንደምንችልና ከውጭ የሚገባ ስንዴን እንደምናስቀር ነው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ግርማሜ፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት ስለመገኘቱ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራ ግብርናን ከማዘመንና መስኖን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በተደጋጋሚ ድርቅ ሲከሰት ከሚነሱ የመፍትሔ አማራጮች አንዱ የከብቶች መኖ ባንክ ማቋቋም የሚል ሐሳብ ሲስተጋባ ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በግብርናና በአርብቶ አደር ልማት ዘርፍ የተሠማሩ ተቋማትን ውጤታማ በሆነ መንገድ አስተባብሮ ማሠራት የሚለው ጉዳይም በአንዳንዶች በመፍትሔነት ይጠቀሳል፡፡ የፖሊሲና አሠሪ ሕጎች ጥያቄም አብሮ ይወሳል፡፡ ከእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኛ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) በአንዳንዶቹ እንደማይስማሙ ነው የጠቀሱት፡፡

ድርቅ ደጋግሞ የሚከሰትባቸው ቦታዎች በደቡብና በምሥራቅ የአገሪቱ ጠረፋማ ቦታዎች መስኖ አማራጭ ነው የሚሉት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፣ ለአብነት ያህል በቦረና የከርሰ ምድር ውኃ ልማት በመሥራት ድርቁን መቋቋም ይቻላል ይላሉ፡፡ በደቡብ ምሥራቅና ምሥራቅ አካባቢ ደግሞ ከከርሰ ምድር ውኃ በተጨማሪ፣ ትልልቅ ተፋሰሶች ያሉባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው በገጸ ምድር ውኃ ልማት አደጋውን መከላከል ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሆኖም ባለን ውስን የኢንቨስትመንት አቅም የተነሳ ሁሉንም የድርቅ አካባቢዎች በመስኖ ማዳረስ ሊከብድ ይችላል፡፡ ከዚህ ይልቅ በእነዚህ ድርቅ በሚያጠቃቸው ቦታዎች በቂ ዝናብ በሚዘንብባቸው ወቅቶች ውኃውን ሰብስቦ ማቆየትም አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዝናብ ሲዘንብ በእነዚህ አካባቢዎች የከብቶች መኖ በሰፊው ስለሚበቅል ትርፋማ መኖ ሲገኝ ቆጥቦ በአግባቡ ማስቀመጥም አማራጭ ሆኖ መታየት ይኖርበታል፡፡ ለሰዎች ትርፍ ምርት ሲመረት በጎተራ ተሰብስቦ እንደሚከማቸው ሁሉ፣ ለከብቶችም መኖ ማከማቸት ይቻላል፤›› ሲሉም ሐሳባቸው ያጠናክራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የመኖ ባንክ ሲባል መቆየቱን የሚያስታውሱት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፣ በዘላቂነት ያንን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረት አለመኖር፣ እንዲሁም ችግር ሲፈጠር ብቻ መንቀሳቀስ ችግር አለመፍታቱን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ችግር ከመፈጠሩ በፈት በዘላቂነት መፍትሔ ለመፍጠር ታስቦ አለመሠራቱ ነው ትልቁ ችግር፡፡ ዝናቡ ይቀራል ይመጣል፤›› በዚህ መሀል የታሰበው ሁሉ ያዝ ለቀቅ ዓይነት ሥራ ይሆናል፡፡ ችግሩ በዚህ የተነሳ ትኩረት ያጣል በማለትም ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩልም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ለጋሽ ድርጅቶችን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ የሚሠሩ ተቋማት በዘርፉ የሚሠሩትን ሥራ ለማስተባበርም ሆነ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት አለመቻሉን ነው ማንደፍሮ (ዶ/ር) የሚያወሱት፡፡

‹‹በእርግጥ የእኛ ድርጅት አርብቶ አደር አካባቢዎች እስካሁን አልገባም፡፡ የሰብል አምራችና ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ነው የምንሠራው፡፡ በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ ተቋማት የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት አለመቻላቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሁሉም የየግሉን ትንንሽ ነገር ነው የሚሠራው፡፡ ዘላቂና ትልልቅ ነገር በጋራ መሥራት ቢቻልም፣ ነገር ግን ያንን የሚያስተባብር አካል ይፈልጋል፡፡ ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ የአርብቶ አደር ልማት ዘርፍን የሚያግዙ ድርጅቶች በአርብቶ አደር አካባቢዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እነዚህን ማስተባበርና ዘላቂ የሆነ ግብ አስቀምጦ መሥራት ቢቻል ውጤታማ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ ውስንነት እንደ አገር አለብን፤›› በማለት ነው በዚህ ዘርፍ ያለውን ማነቆ የሚናገሩት፡፡

በግብርናውም ሆነ በአርብቶ አደር ልማት ዘርፍ አሠሪ ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና ስትራቴጂዎች አሉ ወይ? ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹በወረቀት የሚጎድለን ነገር አለ ብዬ አላምንም፡፡ በስትራቴጂም ሆነ በፖሊሲ ብዙ የተባለ ነገር አለ፡፡ መሬት ላይ ማውረድ ካልሆነ በስተቀር እነዚህን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ብንፈትሽ ብዙ ጉድለት አላቸው ብዬ አላምንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ ከፍተኛ የሀብት ውስንነት በመንግሥት በኩል አለ፤›› ብለዋል፡፡

በእሳቸው እምነት ተቋማትን በተመለከተ ሌላው መተኮር ያለበት ደግሞ፣ ‹‹ሁሉም ተቋማት በእኛ ስትራቴጂና በእኛ ፖሊሲ ተመሥርተው ካልሠሩ አቅማችን እንደሚበታተንና ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡  የሀብት ውስንነትን ለመፍታት መንግሥትም ሆነ በዘርፉ የተሠማሩ አጋር አካላት ቅደም ተከተል በመለየት ምግብ ዋስትናን ደረጃ በደረጃ ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ አተኩረው ቢሠሩ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብዬ ነው የማምነው፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን የሚያጠናክሩት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፣ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡ ጥረት ከፍተኛ ቅንጅታዊ ሥራን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም ነው ሐሳባቸውን የደመደሙት፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *