የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳቱን ተከትሎ፣ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ አለባቸው ላላቸው መንግሥት የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ለ13 አገር አቀፍ ፓርቲዎች እንዲሁም 13 ለሚሆኑ ክልላዊ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሄዱና የሰነድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ በማሳሰብ፣ ከየካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የአንድ ወር ጊዜ መስጠቱን አስታውቆ ነበር።

ቦርዱ በሰጠው ማሳሳቢያ ላይ የተወሰኑ ፓርቲዎች ቅሬታ ያነሱ ሲሆን፣ የቅሬታቸው ምክንያትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ የሚያስችል የተሟላ የፀጥታ ሁኔታ አለመኖሩንና አንዳንዶቹም አባሏቻቸው የታሰሩባቸው መሆኑን የሚገልጽ ነው።

በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ምክክር አካሄዷል።በምክክሩ ወቅትም የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ቡርቱካን ሚደቅሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ በመሆኑ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያከናውኑ የተጠየቁ ፓርቲዎች ጉባዔ በማካሄድ፣ እንዲሁም አስፈላጊ የሰነድ ማሻሻያዎችን በማድረግ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ በድጋሚ አሳስበዋል።

የተወሰኑ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ቅሬታ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየትም የፖርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ በጊዜው ሊካሄድ እንደሚገባ ገልጸው፣ ጉባዔ ለማካሄድ ችግር የገጠማቸው ፓርቲዎች በተናጠል የገጠማቸውን ችግር ለቦርዱ ካሳወቁ ቦርዱ እያንዳንዱን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ በመመልከት ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል ገልጸዋል።

ከዚህ ውጪ ግን በደፈናው ጉባዔ ማድረግ አልተቻለም ብሎ መወሰን አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ ጉባዔውን እንዲያካሄዱ አሳስበዋል። በተጨማሪም ቦርዱ አባሎቻቸው የታሰሩባቸው ፓርቲዎችን መረጃ በመሰብሰብ አባሎቻቸውን የሚፈቱበትን ሁኔታ የማመቻቸት ጥረት እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *