የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የመርሆዎች ስምምነትን የሚጥስ ነው በማለት ተቃውሞ አሰማ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ትናንት የካቲት 13 ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሯ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር የተደረሰውን የመርሆዎች ስምምነትን የሚጥስ ብሏል። ላለፉት 11 ዓመታት በግንባታ ላይ የቆየው እና ግብፅ፣ ሱዳንን እና ኢትዮጵያን ብዙ ያከራከረው ግድቡ ትናንት የካቲት 13/2014 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል። በቀጣናው የውዝግብ ምንጭ ሆኖ የቀጠለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል በአንዱ ተርባይን ነው 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል። 13ቱም ተርባይኖች ወደ ሥራ ሲገቡ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የማመንጨት አቅም 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት እንደሚደርስ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሯን ተከትሎ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን እርምጃ የመሮሆዎች ስምምነትን የሚጥስ “የተናጠል” ውሳኔ ብሎታል። የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌትም የተከናወነው በኢትዮጵያ “የተናጠል” ውሳኔ ነው ብሏል። “. . . ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል በፈረመችው የ2007 የመርሆዎች ስምምነት የተጣለባትን ግዴት መተላለፏን ግብፅ ታረጋግጣለች” ይላል ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ። ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሯን ተከትሎ ከሱዳን በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የመርሆዎች ስምምነት
የሦስቱ አገራት የአባይ ወንዝን የመጠቀም ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን መሪዎች መጋቢት 2007 ዓ.ም. የወንዙ አጠቃቀም ላይ የመርሆዎች ስምምነቱ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ የመርሆዎች ስምምነት የትብብር፣ ከፍተኛ ጉዳት ያለማድረስ እና የመረጃ ልውውጥ መርህን መሠረት ያደረገ ነው። በሰምምነቱ መሠረት በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ የሚከሰት አለመግባባት በመልካም መርህ ላይ ተመስርቶ በውይይት ወይም በድርድር የሚፈታ ይሆናል ይላል። ይሁን እንጂ ሦስቱ አካላት አለመግባባቱን በስምምነት ወይም በድርድር መፍታት ከተሳናቸው ለአገራቱ ርዕሰ ብሔራን ጉዳዩን ሊወስዱት ይችላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት የህዳሴው ግድብ በሚገኝበት ጉባ ተገኝተው ኃይል የማመንጨት ሥራውን አስጀምረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ግድቡ ኃይል የማመንጨት ሥራውን ሲያስጀምሩ ባደረጉት ንግግር የሕዳሴው ግድብ ኃይል እያመነጨ እንደ ቀድሞው ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚፈስ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ውሃውን ገድበው የሱዳንና የግብጽን ሕዝብ የማስራብና የማስጠማት ፍላጎት እንደሌላቸው በተግባር የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ፍላጎት ይህንን ኃይል በማምረት የጎረቤት አገራትን መጥቀም፣ ውሃውንም ወደ ግብፅና ሱዳን መላክ ብቻ አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቦታ ላይ ያለች፣ ከፍተኛ የዝናብ መጠን የምታገኝ እና ብዙ ወራጅ ውሃ ያላት አገር በመሆኗ በርከት ያሉ ግድቦችን በመገንባት ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች አገራም የሚተርፍ ኃይል ማምረት እና መሸጥም ነው ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ፍላጎት 60 በመቶውን በጨለማ የሚሰቃየውን ሕዝብ፣ አምፖል አይተው የማያውቁ፣ በጀርባቸው እንጨት ተሸክመው ኃይል ለመፍጠር የሚጥሩ እናቶችን ጉልበት መከላከል እና አሁን ካለንበት ድህነት መገላገል ብቻ ነው” ሲሉም ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ሃሳብ፣ ፍላጎትና ድርጊት እንደሌላት አስረድተዋል። እስካሁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታውን ለማደናቀፍ የወጣው ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ ቀርቶ ለልማት በትብብርና በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በዚህ የኃይል ማመንጨት ሥራውን ባስጀመሩበት ንግግራቸው አጼ ኃይለሥላሴ በዘመናቸው ሃሳቡን በማንጨታቸውና ዲዛይኑን አሰርተው ትልቅ ራዕይ በመሰነቃቸው፣ በሞት የተለዩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደግሞ ይህንን ሃሳብ በተግባር በማስጀመራቸው፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም የግድቡ ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል። ከዚህም ባሻገር የጸጥታ ኃይሎችን፣ የግድቡ ሠራተኞችን፣ ዲያስፖራዎችና በግድቡ ላይ ለተሰታፉ በሙሉ ላደረጉት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን ቸረዋል።