ከዚህም በተጨማሪ የምርመራ ሪፖርት በሚዘጋጅበት ጊዜ እንደሚደረገው ተጠቂና ባለድርሻ አካላትን ለየብቻ ከማናገር በተለየ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ ውስጥ ቀርበው የሚነጋገሩበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ወ/ሮ ራኬብ ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ዓይነቱን የብሔራዊ ምርመራ ማካሄድ ሰፊ ጊዜና በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ በሁሉም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ መተግበር አስቸጋሪ እንደሚሆን ያነሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ በዚህ ፕሮጀክት ትኩረት የተሰጠው ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች የሚለው ሐሳብ በተለያዩ ጉዳዮች በፖሊስ ጣቢያ ያሉ፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙ፣ ወይም ሰዎች ሊታገቱ የሚችሉባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሰዎችን እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡ አገራዊ ምርመራው እነዚህ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ባሉበት ቦታ በሚያጋጥሟቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን እንደሚመለከት አብራርተዋል፡፡ ‹‹ይኼ ፕሮጀክት ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረው ከቀደመው ሥርዓት ጀምሮ ያልተፈቱ ጉዳዮች ስላሉ ነው፤›› በማለት የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ያስረዱት ወ/ሮ ራኬብ በውስጡ ብዛት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚይዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ራኬብ፣ ግለሰቦቹ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በእስርና በፍርድ ቤት ውስጥ ችግር እንደሚያጋጥማቸው አንስተው፣ በሕጉ ባስቀመጠው ጊዜ ፍርድ ቤት ያለመቅረብና በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች መታሰርን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ አንዳንዱ እንደዚህ ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸመው ሕግ ስለተጣሰ ሳይሆን፣ ሕጉ በራሱ ያስከተለው ሊሆን እንደሚችል በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡ የሕፃናት ታሳሪዎች ጉዳይ ከእነዚህ መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት እስር ቤት ውስጥ የሚያጋጥማቸው ሁኔታ የወደፊት ሕይወታቸውን ሊያበላሽ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም ሲባል ሕፃናቱን ከእስር ቤት ይልቅ የሕፃናት ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ማስገባት የተሻለ አማራጭ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከልጆቻቸው ጋር የሚታሰሩ እናቶችንም በተመለከተም ከፍተኛ የሆነ ወንጀል እስካልፈጸሙ ድረስ፣ እናቶችን ከእስር ቤት ማስወጣት ለልጆቹ ጤንነትና የወደፊት ሕይወት እንደሚበጅ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አስረድተዋል፡፡ አገራዊ ምርመራው እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች አማካይነት ባለመብቶችና ባለድርሻ አካላት ፊት ለፊት ተገናኝተው ውይይቶችን የሚያደርጉ ሲሆን፣ ይኼም የችግሩን ጥልቀት ለመረዳትና መፍትሔ ለማምጣት እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ ለሦስት ዓመታት የሚቆየውን ይኼንን ፕሮጀክት የሚተገብረው በ15 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ሲሆን፣ ድጋፉን ያገኘው ከአውሮፓ ኅብረት መሆኑ ታውቋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *