አዲሱ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የቀረበ ረቂቅ ሕግ ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎችን በኢትዮጵያ ላይ ለመውሰድ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡ በኒውጀርሲው ሴናተር በቶም ማሊኖውስኪ መሪነት ተረቆ የቀረበው ሕጉ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል ጦርነት በተፈጸሙ የሰብዓዊ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግና በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ያለመ ነው ተብሏል፡፡ ረቂቅ ሕጉ “Ethiopia Stabilization, Peace and Democracy Act” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፣ በ25 ገጾችና በ12 ክፍሎች የቀረቡ ጠንካራ አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡

ረቂቅ ሕጉ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሕጎችና የውሳኔ ሐሳቦች ላይ የተመረኮዘ አይደለም ይላሉ አንዳንድ ተቺዎች፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ለውጦችንና የቅርብ ጊዜ ሁነቶችን አለመከተሉንም የሚያወሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች አሁን ይህንን ረቂቅ ሕግ ለማዘጋጀት መነሻ የሆናቸው ምክንያት ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም በጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን ተመሳሳይ ሕጎች ተረቀው ለምክር ቤት ቀርበዋል፡፡ በብዙ የማሳመኛ (የሎቢ) ሥራዎች፣ የዲፕሎማሲና የተቃውሞ ዘመቻዎች ሕጎቹ ሳይፀድቁ ውድቅ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ሊመጣባት ከሚችል ጫና ተርፋለች፡፡ የአሁኑን ረቂቅ ሕግም በተመሳሳይ ውድቅ ለማድረግ ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥረቶች ካልሰመሩና ሕጉ እንዳይፀድቅ ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ፣ ሕጉን ሊከተሉ የሚችሉ ዕርምጃዎች ከወዲሁ ያስፈራሉ፡፡

በረቂቅ ሕጉ ክፍል ዘጠኝ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ፣ እንዲሁም የገንዘብና ሚኒስቴር (Treasury Department) አማካሪ በ180 ቀናት ውስጥ በትግራይ ክልል ጦርነት የተካፈሉ ኃይሎች ሚናን አጣርተው ያቅርቡ የሚል አንቀጽ ይገኛል፡፡ በዚህ አንቀጽም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊትና የሕወሓት ኃይል በጦርነቱ ምን ዓይነት የሰብዓዊ ወይም የጦር ወንጀል እንዲፈጸሙ በዝርዝር ለአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ እንዲቀርብ የሚያዝ ንዑስ አንቀጽ ሰፍሯል፡፡

በቀጣዩ ክፍል አሥር ላይ ደግሞ በትግራይ ክልል ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎችን አጣርቶና ለይቶ ለማቅረብ የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ሕጉ ይሰጣል፡፡ በዚህ የሕግ ክፍል ላይም በትግራይ ክልል ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎች የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀል ወይም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች መሆን አለመሆናቸው ተለይተው እንዲቀርቡ ነው ሕጉ ግዴታ የሚጥለው፡፡ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ሲል ተቋማት (ቡድኖችን) ብቻም ሳይሆን፣ የግለሰቦች የወንጀል ተሳትፎ (በተለይ የባለሥልጣናት) በዝርዝር መቅረብ እንዳለበትም የሚያዝ ንዑስ አንቀጽ ይዟል፡፡

ስለይዘቱ የሕግ ባለሙያዎች ሰፊ ትንተና የሚያስፈልገው ይህ አዲስ የሕግ ረቂቅ፣ በዋናነት ትኩረቱ የኢትዮጵያን በተለይ የትግራይ ክልልን ጉዳይ የተመለከተ ቢሆንም፣ በጦርነቱ ጦሯን ያስገባችው ጎረቤት ኤርትራንም ይመለከታል፡፡ ሕጉ የኤርትራና የኢትዮጵያ ፀጥታ ተቋማትን፣ ባለሥልጣናትንና የመንግሥት አካላትን በየደረጃው ለመቅጣት ያለመ ነው ተብሏል፡፡ ዓላማው፣ ‹‹በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍ ነው፤›› ተብሎ በመግቢያው ላይ የሰፈረለት ይህ የማሊኖውስኪ ረቂቅ ሕግ (HR 6600)፣ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማዕቀብ በትር ለማሽመድመድ ያለመ ነው ብለውታል ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን በተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱ ትግራይ ክልል እንዳይገባ በማድረግ ለሰላም ዝግጁነቱን አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕወሓት አመራሮችን ጭምር ከእስር በመፍታት ለብሔራዊ መግባባትና ለሰላም እጁን ዘርግቷል፡፡ ይህ በሆነበት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ምላሹ ይህ መሆን አልነበረበትም፤›› ሲሉ ይናገራሉ የኖርዝ ካሮላይና ስቴት ዩኒቨርሲቲው መምህር ብሩክ ኃይሉ (ፕሮፌሰር) ስለአዲሱ ሕግ ረቂቅ ሲናገሩ፡፡ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማትነት የሠሩትና አሁን ደግሞ በሚኖሩበት አሜሪካ የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክር ቤት (Ethiopian American Civil Council) ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው የሚያገለግሉት ብሩክ (ፕሮፌሰር)፣ ሕጉ ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

‹‹ሪኮርድ በሆነ ፍጥነትና ሳይጠበቅ አድብተው ነው ከዴሞክራትና ከሪፐብሊካን የወገኑ ጥቂት የሕግ አውጪዎች ረቂቅ ሕጉን ያቀረቡት፤›› ይላሉ ስለሕጉ አቀራረብ ሲያስረዱ፡፡ ሚዛናዊነት በጎደለው መንገድ ሕወሓትን አንድም ጊዜ ተጠያቂ ሳያደርግ፣ ኤርትራን በተለይም ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ  ለመክተት የተደረገ ሴራም አድርገው እንደሚያዩት ይናገራሉ፡፡

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 4 ቀን 2022 ተረቆ የቀረበውን ሕግ በተመለከተ፣ ከሦስት ቀናት በኋላ ጠንካራ የውግዘት መግለጫ አውጥቷል፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማምጣት ተብሎ የተረቀቀው ሕግ እንደሚለው ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ለ30 ዓመታት የነገሠውን ውድመትና ቀውስ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው፡፡ ሕጉ የቀውስ ምንጭ የሆነው የሕወሓት ቡድን ምሥራቅ አፍሪካን ዳግም እንዲያወድም የሚያበረታታ ነው፤›› በማለት ነበር፣ የኤርትራ መንግሥት ለዚህ ረቂቅ ሕግ ጠንካራ አፀፋ ምላሽ የሰጠው፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር)፣ ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት መግለጫ፣ ሕጉ ከጅምሩ መቅረብ ያልነበረበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕጉ በሒደት ላይ ያለ ቢሆንም፣ ነገር ግን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነውም ብለውታል፡፡ ይህን ‹‹በተሳሳተ መረጃ ተመርኩዞ የቀረበ›› ያሉትን ሕግም፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ወገን እንዲቃወመው ነው ዲና (አምባሳደር) ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በሌላ በኩል ስለዚሁ ሕግ በትዊተር ገጻቸው ጠንከር ያለ ትችት የሰጡት የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል፣ ሕጉ በቅርቡ የአፍሪካ  ኅብረት በመሪዎች ጉባዔ ላይ ያወጣውን የውሳኔ ሐሳብ የሚፃረር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በቅርቡ በአዲስ አበባ ጉባዔው ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ማንም አገር በሌላ አገር ላይ የሚወስዳቸውን የተናጠል ዕርምጃዎች እንደሚቃወም ግልጽ አድርጓል ብለዋል አቶ የማነ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ያሳለፈውን ይህንን ውሳኔ በመፃረር አሜሪካ በተናጠል ለምትወስደው ዕርምጃ ሕግ መረቀቁ፣ የኅብረቱን ውሳኔ ይቃረናል ሲሉም ነው ሚኒስትሩ የተቹት፡፡

ልክ እንደ ኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሁሉ የሕጉን ዓላማ፣ ‹‹በተንኮልና በሴራ የተለወሰ›› ሲሉ የተቃወሙት ብሩክ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ሕጉ ከፀደቀ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንዲበላሽ ከማድረጉም በላይ እስካሁን የተገኙ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችንም የሚያኮላሽ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ዳግመኛ የበቃ (No More) መፈክሮችን ይዘን ለተቃውሞ ሠልፍ ወደ ጎዳናዎች ልንወጣ ነው፡፡ አሁን ‘ቮተርስ ቾይስ’ (Votters Choice) ተብሎ በተዘጋጀ የማኅበራዊ ሚዲያ መስኮት ለሰባት የአሜሪካ ባለሥልጣናት (ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና ምክትላቸውን ካማላ ሀሪስ ጨምሮ) በሁለት ደቂቃዎች የተቃውሞ ደብዳቤ መልዕክት ማድረስ የሚያስችል ዘመቻ ከፍተናል፤›› በማለት ብሩክ (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል፡፡ ሕጉ ተዘጋጅቶ ለአሜሪካ ሕግ አውጪዎች መቅረቡ ከተነገረ ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ የተቃውሞ ዘመቻዎች በተለያዩ መንገዶች መክፈቱን አብራርተዋል፡፡

አዲሱ የአሜሪካ ሕግ  ከበድ ያሉ የውሳኔ ሐሳቦች የያዘ ነው፡፡ እንደ ቶም ማሊኖውስኪ እና ግሪጎሪ ሚክስ ያሉ ሕግ አውጪዎች በፊታውራሪነት አርቅቀው ያቀረቡት ሕጉ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ፣ እንዲሁም የሕወሓት ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ ዕገዳ እስከ ማድረግ የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ይዟል፡፡ ከግለሰቦች ባለፈም በትግራይ ክልል ጦርነት እጃቸው ያለበት ተቋማትና ድርጅቶችንም የዕቀባ ዒላማ ውስጥ ሕጉ ያስገባል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና የገንዘብ ምንጮች (አይኤምኤፍና የዓለም ባንክን ጨምሮ) ገንዘብ እንዳታገኝ እስከ ማድረግ የሚደርስ ዕርምጃም በሕጉ ተካቷል፡፡ የጦርና የደኅንነት ትብብር ማዕቀብ መጣልም ሌላው ሕጉ ለአሜሪካ መንግሥት ከሚሰጣቸው ሥልጣኖች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ሕግ መፅደቅ የተነሳ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ እጃቸው አለበት ብለው ባመኑትና አጥፊ ነው ባሉት አካል ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ የሚፈቅድ ሥልጣን ሊኖራቸው ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን የማይተባበር አካል ቅጣት እንደሚጠብቀው ይህ ሕግ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በትግራይ ክልል ሰላም እንዲወርድ መንግሥትና ሕወሓት ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር መግባት እንደሚኖርባቸው፣ ሕጉ ጠንከር ያለ የውሳኔ ሐሳብ ይዞ ቀርቧል፡፡

ይህ ረቂቅ ሕግ በሕግ አውጪው ተቋም ፀድቆ እንዳይወጣ የሚደረገው የተቃውሞ ጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሕጉ ቢፀድቅ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖም ከወዲሁ ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ እንዲህ ያሉ የተናጠል የዲፕሎማሲ ጫና መፍጠሪያ ሕጎች በአሜሪካ ተረቀው መተግበራቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ ነገር ግን አሁን ባለው የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን ሊያመጣ የሚችለው ውጤት አሉታዊነት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

በቅርቡ በአንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናት መድረክ ላይ፣ ‹‹ጣልቃ ገብነትና ዓለም አቀፍ ሕጎች›› የሚል ጥናት ያቀረቡት የሕግ ምሁሩ ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ የተናጠል ማዕቀቦች (ዕርምጃዎች) ውጤትን በሰፊው ነበር የገመገሙት፡፡ የተናጠል ማዕቀቦች በአገሮች ላይ ሊወሰድ ስለሚችልባቸው ዓለም አቀፍ የሕግ አግባቦችም ባለሙያው በሰፊው አብራርተዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የዓለም አቀፍ ዳኝነት ሚና ባላቸው አካላት በተደነገጉ ሕጎችም ሆነ መሠረታዊ መርሆዎቻቸው ላይ፣ የተናጠል የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ዕርምጃዎች ድጋፍ የላቸውም ይላሉ ጌታቸው (ዶ/ር) በዚሁ ጥናታቸው፡፡ ‹‹ሆኖም ኃያላን አገሮች ይህን በመተላለፍ ወደ ተናጠል ዕርምጃዎች ይገባሉ፡፡ ይህ ደግሞ በአገሮች የውስጥ የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ችግር ከማባባስ በዘለለ፣ ዘላቂ መፍትሔ የሚፈጥርበት ዕድል የመነመነ ነው፤›› በማለት ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡

የአሁኑ የአሜሪካ ረቂቅ ሕግ (HR 6600) ለኢትዮጵያ በተለይ ለትግራይ ክልል ግጭት መፍትሔ ይዞ ይመጣ ይሆን ወይ የሚለውን ጥያቄ ከወዲሁ መመለስ አይቻልም፡፡ አሜሪካ ግጭት ባለባቸው አገሮች የወሰደቻቸው ዕርምጃዎችና ያንፀባረቀቻቸው አቋሞች ግን ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡ የተናጠል ዲፕሎማሲያዊና የፖለቲካ ጫናዎችን በማሳደር ብቻ ኢትዮጵያ እንደምትገኝበት ያሉ ውስብስብ ቀውሶችን በዚህ መንገድ መፍታት ይቻል ይሆን ወይ የሚለውም፣ ከዓለም አቀፍ ልምዶች በመነሳት ብዙ ጥያቄዎች ሊስተጋባበት ይችላል፡፡ ይህም ሆኖ ሕግ ከማርቀቅ ያልተቆጠቡ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች በቀውስ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ማዕቀቦች ለማሸከም ጥረታቸውን ገፍተውበታል፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን ከወዲሁ ተቃውሞአቸውን ማሰማት የጀመሩት፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *