የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሰተርፊልድ

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙ ተገለጸ።

አምባሳደሩ ትናንት የካቲት 06/2014 ዓ.ም. አዲስ አበባ መግባታቸውን የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ፣ ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ሳተርፊልድ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች እና ከሰብዓዊ ድርጅት አስተባባሪዎች ጋር ይገናኛሉ ብሏል ። ልዩ መልዕክተኛው ለሁለት ቀናት ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ማድረጋቸው የተሰማው በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ግጭቱን በውይይት ለመፍታት ንግግር መቀጠሉ በተገለጸበት ወቅት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ አዲስ አበባ ውስጥ ረቡዕ የካቲት 02/2014 ዓ.ም ለሰላም ተስፋ እንዳለ የገለጹ ሲሆን፤ “በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ” በማለት ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረው ነበር። በተመሳሳይ በየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥር 30/2014 ዓ.ም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች በቅርቡ ለሰላም ያሳዩትን እርምጃ በበጎ እንደሚያዩት ገልጸው ነበር።

በቅርቡ አምባሳደር ፌልትማንን በመተካት የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ስተርፊልድ የአፍሪካ ቀንድ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን በጎበኙበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናንተው ነበር። ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስ ተከትሎ አሜሪካ በያዘችው አቋምና በወሰደቻቸው እርምጃዎች ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።

የአሜሪካ መንግሥት ጦርነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ የቪዛ እገዳ የጣለ ሲሆን፣ እንዲሁም ከሳምንታት በፊት ተግባራዊ የሆነው ኢትዮጵያ ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ታስገባበት የነበረው የአጎዋ ተጠቃሚነት የእገዳ እርምጃ ወስዷል። የኢትዮጵያ መንግሥትም አሜሪካ ለአማጺያኑ የሚያደላ መግለጫና እርምጃ እየወሰደች ነው በማለት አሜሪካን በወገንተኝነት ሲከስ ቆይቷል። ከአንድ ወር በፊት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስልክ መነጋገራቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል ጅማሬ ሊሆን እንደሚችል በስፋት ተነግሯል።

አሜሪካ ጦርነቱ በድርድር መቋጫ እንዲያገኝ ልዩ መልዕክተኛ በመሰየም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ስታደርግ ቆይታለች። አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ዴቪድ ሳተርፊልድ ደግሞ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን በመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀ ልምድ እንዳካበቱ ይነገርላቸዋል። አምባሳደር ሳተርፊልድ በቱርክ፣ በሶሪያ፣ በቱኒዚያ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና ሊባኖስ ውስጥ አገራቸውን ወክለው በዲፕሎማትነት ሰርተዋል።

አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ማይክ ፖምፔዮ ከፍተኛ አማካሪ ነበሩ።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *