ተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል ያለው ውይይት መቀጠሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬው ረቡዕ የካቲት 02/2014 ዓ.ም ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው ይህንን የተናገሩት። ምክትል ዋና ፀሐፊዋ በጦርነቱ የተጎዱትን የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎችን ከጎበኙ በኋላ ለሰላም ተስፋ እንዳለ የገለጹ ሲሆን “በእርግጥ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው አንፃር አነስተኛ ግጭቶች ናቸው የሚታዩት” ብለዋል። ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ” በማለት አስረድተዋል።

ከትግራይ አመራሮች፣ ከአማራ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ያደረጉት አሚና መሐመድ ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች በቅርቡ ለሰላም ያሳዩትን እርምጃ በበጎ እንደሚያዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከቀናት በፊትም መግለጻቸው ይታወሳል። ሰላም ለማስፈን ግጭቱን እንዲሁም ተኩስ ማቆም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ የተናገሩት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተፋላሚ ወገኖች ይህንን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከዚህ ቀደምም ጦርነቱን ለማብቃትና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው መግለጻቸው ይታወሳል። ዋና ፀሐፊው የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ከሆኑት ከኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት እያደረጉት ስላላው ጥረት ከሕብረቱ ተወካይ መረዳታቸውን በወቅቱ አስታውቀው ነበር። በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ዋና ፀሐፊውን በመወከል የመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በጦርነቱ የተጎዱ የአማራና የትግራይ ክልል ከተሞችን ጎብኝተዋል። እንዲሁም ከክልል አመራሮችም ጋር ተገናኝተዋል።

ምክትል ዋና ፀሐፊዋ በክልሎቹ ከሴቶችና ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ቆይታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሲባዊ እንዲሁም ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንደማይታገስ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል። ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች አጋርነታቸውን የገለጹት አሚና፣ በጦርነቱ ሳቢያ በሴቶች ላይ የደረሰውን ግፍና በደል እንዲሁም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለማቃለል ድርጅታቸው መፍትሄ በማፈላለግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ሴቶች ካለባቸው ህመም እንዲፈወሱ በተሃድሶ እና በመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ውስጥ እንዲካተቱም አመራሮቹን አሳስበዋል።

በተጨማሪም ተመድ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሰላም ጥረትም ይደግፋል ብለዋል። ከአሚና በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ሰኞ ዕለት በአማራ ክልል የኮምቦልቻ ከተማን እንዲሁም ወደ ትግራይ እና አፋር ክልሎችም በመሄድ ጉብኝት አድርገዋል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በትግራይ ክልል ውስጥ 40 በመቶ የሚጠጉ ሰዎች በአስከፊ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጿል። ከአስራ አምስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ ኬንያና ሌሎች አገሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ሲሆን የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆም የትግራይ መሪዎችን አነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘግቦ ነበር። የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ከሳምንት በፊት ተናግረዋል። ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ይህ እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት የተወሰነ ውጤት እያሳየ መሆኑንና የመሻሻል ምልክቶች እንዳሉ አመልክተው ነበር። እየተካሄደ ነው ስለተባለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *