ታጣቂዎች በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በሚገኙ ማረሚያ ቤትና የፀጥታ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽመው 139 እስረኞችን ሲያስመልጡ የጦር መሳሪያዎችን መዝረፋቸውን የዞኑ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

የአማራ ክልል ፖሊስ እንዳስታወቀው ታጣቂዎቹ ሰኞ ጥር 30 ለማክሰኞ የካቲት 01/2014 አጥቢያ ከእኩለ ሌሊት በኋላ በዞኑ፣ በላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ ውስጥ በሚገኙት የወረዳው ማረሚያ ቤት፣ የፖሊስ ጣቢያ እና የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ይህንንም ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ከወረዳው ማረሚያ ቤት የሕግ ታራሚዎች እንዲያመልጡ ማድረጋቸውንና በተቋማቱ ላይ ዝርፊያ መፈጸማቸውን የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ገደማ በሦስት ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደ ከተማዋ በመግባት ጥቃት ከፈጸሙት ታጣቂዎቹ መካከል፣ 16ቱ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ገልጸው፣ ሦስት የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውንም አመልክተዋል። የታጣቂዎቹ ቡድን በንፋስ መውጫ ማረሚያ ቤት ላይ በፈጸሙት ጥቃት 139 ሰዎችን ከእስር ያስመለጡ ሲሆን ከ15 በላይ የጦር መሳሪያዎችን እና የእጅ ቦንቦችን መዝረፋቸውን ምክትል አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በፍኖተ ሰላም አስር ቤት ምን ተከሰተ?

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከቀናት በፊት በነፋስ መውጫ የተፈጸመው ጥቃትና አስረኞችን የማስመለጥ ድርጊት ከሳምንት በፊት በፍኖተ ሰላም ከተማ ካጋጠመ ችግር ጋር የተገናኘ ነው ብለዋል። ከአንድ ሳምንት በፊት ምዕራብ ጎጃም ውስጥ በምትገኘው ፍኖተ ሰላም ከተማ ውስጥ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ስልክ በማስገባት ከውስጥ ሆነው በጥበቃዎች ላይ በድንጋይ ጥቃት በመፈጸም ከማረሚያ ቤቱ ለመውጣት ጥረት አድርገው እንደነበር ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።

ነገር ግን የፀጥታ ኃይሉ ይህንን የታራሚዎች ድርጊት ቆጣጠሮ በወቅቱ አመጽ አነሳስተዋል የተባሉ ታራሚዎችን በመለየት ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ማረሚያ ቤት እንዲሄዱ ተደርጎ ነበር። “ወደ ጋይንት ከሄዱ በኋላም ከተለያዩ ወረዳዎች የተሰባሰቡ ‘ፋኖ ነን’ የሚሉ አካላት ጥቃት አድርሰዋል” በማለት የትቃቱ ፈጻሚዎች እውነተኞቹ ፋኖዎች ሳይሆኑ ለዘፈራ የተሰማሩ ወንጀለኞች እንደሆኑ ገልጸው “ዋናዎቹ ፋኖዎች ከእነሱ ጋር ተታኩሰው አካባቢውን ሰላም አድርገዋል” ብለዋል ኮሚሽነር ተኮላ። ኮሚሽነር ተኮላ እነዚህ ጥቃት አድራሾች ከወራት በፊት የህዋሓት ኃይሎች አካባቢውን ሲቆጣጠሩ ከእስር ያመለጡ የሚገኙባቸው መሆኑን ጠቅሰው “ዋና አላማቸውም ታሳሪ ጓደኞቻቸውን ለማስፈታት እና ንብረት ለመዝረፍ ነው” ብለዋል።

የክልሉ ፖሊስም ጥቃት ፈጻሚዎቹ በማረሚያ ቤቱ እና በፀጥታ ተቋማቱ ላይ በሌሊት በፈጸሙት ጥቃት እስረኞች እንዲያመልጡ ሲያደርጉ፣ በተጨማሪም በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ እና የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ውስጥ የነበረን ጦር መሳሪያን መዝረፋቸውን አረጋግጧል። ነገር ግን ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከዘረፏቸው ንብረቶች መካከል የተወሰኑት እንዲሁም ከአስር ካመለጡት ታራሚዎች ውስጥ ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተመልሰው መያዛቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ያመለጡ እስረኞች

በዚህም ከማረሚያ ቤቱ እንዲያመልጡ የተደረጉ ታራሚዎችን መልሶ በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲገቡ የማድረግና ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለሕግ ለማቅረብ ክትትልና ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ፖሊስ ገልጿል። አቶ ጥላሁን ጨምረውም በታጣቂዎቹ ከማረሚያ ቤት እንዲያመልጡ ከተደረጉት እስረኞች መካከል እስካሁን 65 የሚሆኑት በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል።ምክትል አስተዳዳሪው ስለጥቃት ፈጻሚዎቹ ማንነት ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ከዚህ በፊት በተለያየ ምክንያቶች ከመከላከያ እና ከክልሉ ልዩ ኃይል አባልነት የተሰናበቱና በተለያዩ ወንጀሎች ሲፈለጉ የነበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ የጥቃቱ ፈጻሚዎችን በተመለከተ “ድርጊቱን የፈጸሙት ፋኖ ያልሆኑ፣ ነገር ግን ፋኖ ነን የሚሉና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ናቸው” ብለው ነበር። ፖሊስ እንዳለው ይህንን ጥቃት የፈጸመው “በፋኖ ስም የሚነግድ የተደራጀ ቡድን” መሆኑን በመግለጽ፣ ጥቃቱን ተከትሎ የክልሉ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸው አመልክቷል።

የአማራ ፖሊስ እንዳለው ታጠቂዎቹ ከወረዳው የፀጥታ ተቋማት ከዘረፏቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል የተወሰነውን ማስመለስ እንደቻለ ጠቅሷል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ በዋናነት ዒላማ ያደረጉት እስር ቤትና የፀጥታ ተቋማትን እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ የገለጹ ሲሆን ፖሊስም በግልና በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን አረጋግጧል። በክልሉ ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በሚገኘው በላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያና የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ላይ በታጣቂዎች ከተጸፀመው ጥቃት በኋላ፣ ከተማዋ መረጋጋቷንና ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሷን ምክትል አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ጥቃት ፈጻሚዎች ለመረዳት እንደተቻለው ታጣቂ ቡድኑ ከደቡብ ጎንደር፣ ከሰሜንና ከደቡብ ወሎ የተለያዩ ወረዳዎች የተሰባሰቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *