ባለፉት ሦስት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ ማለትም በአራቱ የወለጋ ዞኖች ግድያዎች፣ የንብረት ውድመት እና ማፈናቀሎች በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ሆነው ከርመዋል።

ይህ ግድያ፣ ንብረት ማውደም እና ማፈናቀል በአሁኑ ጊዜ ከወለጋ ወደ መካከለኛው የአገሪቱ ክፍል፤ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሸጋግሯል። ይህም መንግሥት በሽብርተኝነት የሰየመውና ‘ሸኔ’ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን የእንቅስቃሴ አቅጣጫ ጋር የተያያዘ ነው። በምዕራብ ኦሮሚያ በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ ዞን በስፋት እንደሚንቀሳቀስ ይነገር የነበረው ይህ ታጣቂ ቡድን በአሁኑ ጊዜ በበርካታ የምዕራብ ሾዋ ዞን አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ባለፉት ጥቂት ወራትም አምቦ ዙሪያ በሚገኙ ወረዳዎች ንጹሃን የኦሮሞ እና የአማራ ብሔር ተወላጆች ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች በግፍ ተገድለዋል፤ ቤታቸው ተቃጥሎ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ የሁለቱ ብሔር ተወላጆች፣ የዓይን ምስክሮች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሚሉት፤ በዞኑ ባለፉት ጥቂት ወራት መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ቡድን የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሰንዝሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአማራ ብሔር ተወላጆችን ተገድለዋል። ይህን ተከትሎ የአማራ ተወላጆች በወሰዱት “የበቀል እርምጃ” በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸው ይነገራል።

የጫንዶ ግድያ

ጫንዶ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ውስጥ የምትገኝ ቀበሌ ናት። ጫንዶ የተዘራባትን የምታበቅል በለምነት የታደለች ስፍራ ናት። በዚህም ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከወሎ አካባቢ ከ80 ያላነሱ አባ ወራዎች በአካባቢው እንዲሰፍር መደረጉን ነዋሪዎች ይናገራሉ። በአካባቢው ቀድመው የነበሩ ነዋሪዎችና ኋላ ላይ ወደ አካባቢው የመጡት ሰዎች ለረጅም ዘመናት ያለ ችግር በሰላም የኖሩባት ጫንዶ፤ ታኅሣሥ 22/2014 ዓ.ም. ላይ ግን አሰቃቂ ሁኔታን አስተናግዳለች።

በዕለተ ዓርብ የአንድ ዓመት ተኩል ታዳጊን ጨምሮ ከ20 ያላነሱ የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን ሦስት በጥቃቱ የቅርብ የቤተሰብ አባላት የተገደሉባቸው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ብቻዬን ቀረሁ”

አበባው መኮንን የጫንዶ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን በዚያን ዕለቱ ጥቃት 15 የቅርብ ዘመዶቹን አጥቷል። “ባለቤቴ ከእነ ልጆቻችን፣ ወንድሜ ከነ ልጆቹ፣ እህቴ ከነልጆቿ ተገድለዋል። ጎረቤቶቼም ተገድለዋል። ከእነርሱ ጋር በአጠቃላይ 25 ሰዎች ናቸው የተገደሉት” በማለት ከታኅሣሥ 22ቱ ግድያ በኋላ፤ “ብቻዬን ቀርቻለሁ” ሲሉ የገጠማቸውን መከራ ይናገራሉ።

የአካባቢው ሚሊሻ ታጣቂ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አበባው ወደ ቀበሌያቸው ከመጣው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው እንደነበረ ያስታውሳሉ። ቡድኑ በጫንዶ ቀበሌ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት፤ “በቀበሌዋ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ሰፍረው በነበሩ የኦሮሚያ ሚሊሻ አባላት ላይ ተኩስ ከፍቶ ነበር” ይላሉ አቶ አበባው።

“ለ30 ደቂቃ ያህል ተታኩሰው እነሱን ጨርሰው ከመጡ በኋላ የአማራ ቤቶችን እየለዩ መግደል ጀምሩ” በማለት አበባው የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ። ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት እንደቻለው ታጣቂ ቡድኑ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ሰፍሮ አካባቢውን ሲጠብቅ በነበረው የክልሉ የሚሊሻ አባላት ላይ በተከፈተ ጥቃት ቢያንስ አምስቱ በዕለቱ ተገድለዋል። አበባውም ከትኩስ ልውውጡ በኋላ ከአካባቢው ሸሽቶ ሄዶ ሲመለስ፤ በቀበሌዋ ተወልደው ያደጉት ልጆቹ እና ባለቤቱን በሕይወት አላገኛቸውም።

የአምቦ ከተማ

በታኅሣሥ 22ቱ ግድያ ወላጅ አባቱን እንዳጣ የሚናገረው ደግሞ ጀማል ሙሳ ነው። “ከአማራነታችን በተጨማሪ እኛን ዒላማ ያደረጉበት ምክንያት ወንድሜ ሚሊሻ ነው። 15 ሰው የተገደለበት ቤተሰብ ውስጥም ሚሊሻ አለ” በማለት እንዴት በታጣቂ ቡድኑ ዓይን ውስጥ እንደገቡ ይናገራል። በተመሳሳይ ዑመር አበባው የተባለው ግለሰብ በጥቃቱ ወንድም እና እህቱን ጨምሮ ልጆቻቸው ያሉበት አምስት የቅርብ ቤተሰቦቹን አጥቷል።

ዑመር በጥቃቱ የተገደሉትን ሰዎች ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በተከለተ መልኩ መቅበር እንዳልቻሉ እና “በስንት ችግር በአንድ ጉድጓድ እስከ 6 ሰው ለመቅበር ተገደናል” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል። ይህ ጥቃት ከተፈጸመ ሳምንታት ቢያልፉም ጥቃቱን ተከትሎ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀበሌዋ እንዳልተመለሱ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በተለያዩ ስፍራዎች ተበታትነው የሚገኙ ሰዎችም ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ወገን ምንም አይነት የእርዳታ ድጋፍ ሳያገኙ በችግር ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ።

“ከአሁን በኋላ ምን ተስፋ አለን? ቢወራ ቢወራ ምንም ለውጥ የለም። የወለጋው ወሬ ሆኖ ቀርቶ የለ? ከወሬ ያለፈ ነገር የለም። የእኛም መጨረሻ ይሄው ነው” በማለት ብሶቱን ገልጿል።

የበቀል እርምጃዎች

መንግሥት ‘ሸኔ’ እያለ የሚጠራው ቡድን በንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ ከፈጸመ ከሳምንታት በኋላ አማራ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በበቀል በወሰዱት እርምጃ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸውን በጥቃቱ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጡና አካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል። ዳኖ ከኖኖ ወረዳ ጋር የምትዋሰን ወረዳ ነች። በዚህ ወረዳ የአማራ ታጣቂዎች ሰኞ ጥር 23/2014 ዓ.ም. በፈጸሙት ጥቃት 13 የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መገደላቸውን እና ከ97 በላይ ቤቶች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች እና የዳኖ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ይናገራሉ።

የዳኖ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሾመ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ሰኞ ጥር 23 ላይ ከመንግሥት እውቅና ውጪ የአማራ ታጣቂዎች “‘ሸኔን እናጠፋለን’ በማለት አዲላ ዳሌ በምትባለው ቀበሌ ላይ በፈጸሙት ጥቃት የ13 ንጹሃን ሰዎች ሕይወት አልፏል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ምክትል የወረዳ አስተዳዳሪው በዳኖ ወረዳ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ጦር ምክንያት በርካታ ግድያዎች እና መፈናቀሎች ሲያጋጥሙ ነበር ይላሉ።

“ሸኔ አማራ የሆነን እየገደለ ንብረት ይዘርፋል፤ ቤት የማቃጠል ተግባር ሲፈጸም ነበር። ይህ ተከትሎ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ናቸው የሚባሉ የአማራ ታጣቂዎች በሚወስዱት የአጸፋ እርምጃ በርካቶች እየተጎዱ ነው” በማለት ሁኔታውን ያስረዳሉ።

ከዳኖ ወረዳ በተጨማሪ ከታኅሣሥ 2014 መጨረሻ እስከ ጥር 2014 መጀመሪያ ባሉት ቀናት በኖኖ ወረዳ ባሉ አምስት ቀበሌዎች ውስጥ በተፈጸሙ የበቀል ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኖኖ ወረዳ ነዋሪ “በወረዳዋ በተለያዩ ጊዜያት ተፈጽመዋል ባሏቸው የበቀል ጥቃቶች እስከ 18 ሰዎች መገደላቸውን አውቃለሁ” ይላሉ። ይህ ነዋሪ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአንድ ስፍራ እንዲቀበሩ መደረጉንም አስረድተዋል። የማቱ ሥላሴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ነዋሪም፤ የ27 ዓመት ወጣት ልጃቸው መገደሉን እና ንብረታቸው እንዲወድም መደረጉን ይናገራሉ። በተመሳሳይ የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪው አሮ ወርቅነህ ፉርጋሳ፤ የሸኔ ታጣቂዎች በወረዳው ባሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ በበቀል ሌሎች ንጹሃን እንደሚገደሉ ያስረዳሉ።

“ሸኔ ገብታ አራት የአማራ ተወላጆችን ገደለች። አምስተኛ አንድ ወጣትን ገድላ መኪናውን አቃጠለች ከዚያ ነገሩ ተያያዘ። ሰዎች ቂም በቀል ለመወጣ ሲሉ ጉዳት ተከሰተ” ይላሉ። ልክ እንደ አማራ ብሔር ተወላጆች ሁሉ፤ ጥቃትና ግድያን ሽሽት ከቀያቸው የተፈናቀሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችም ከመንግሥት አካል ምንም አይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ነዋሪዎች እራሳቸውን ከታጣቂዎች እንዳይከላከሉ መንግሥት ትጥቅ በግዴታ እያስፈታን ነው ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ።

የኖኖ ወረዳ አስረዳዳሪ አቶ ወርቅነህ ፉርጋሳ በበኩላቸው ትጥቁ “በሸኔ እጅ ሊገባ ስለሚችል ትጥቅ ማስፈታቱ አግባብ ነው” ይላሉ።

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውን አንድ የአካባቢውን ባለሥልጣን ጠቅሶ ዘግቧል። በዚህም በወረዳው 168 መገደላቸው እና ከእነዚህ ውስጥ የ87 ሰዎች አስከሬን በአንድ ቦታ ላይ መገኘቱን ባለሥልጣኑ የጠቀሱ ሲሆን በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱንም አመልክተዋል።

ከምዕራብ ኦሮሚያ ወደ ማዕከላዊው የክልሉ ክፍል እየተስፋፋ በመጣውና በተደጋጋሚ በንጹሃን ላይ ለተፈጸሙት ግድያዎች በነዋሪዎች እና በመንግሥት አካላት ክስ የሚቀርብበት የኦሮሞ ነጻነት ጦር በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም። ባለፉት ዓመታት ታጣቂው ቡድን ይንቀሳቀስባቸዋል በተባሉት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች፣ በነዋሪዎች ላይ ከሚፈጸመው ጥቃት በተጨማሪ የአካባቢ ባለሥልጣናት፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ሹፌሮችና ወደ ለተለያዩ ሥራዎች ወደስፍራው የሄዱ ሰዎች ሰለባ መሆናቸው ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *