የትግራይ እና የአፋር ክልል በሚዋኑባቸው አካባቢዎች በህወሓት ኃይሎች የተከፈተውን ጥቃት ተከትሎ እየተካሄደ ያለው ውጊያ ባለፈው ሳምንት መባባሱን የአፋር ክልል መንግሥት ገለፀ።
እንደ ክልሉ መንግሥት መግለጫ ከሆነ የህወሓት ጥቃት ሰርዶን በመያዝ የኢትዮ ጂቡቲ መተላለፊያ መስመርን ለመቆጣጠር ዒላማ ያደረገ ነው። የአፋር ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የህወሓት ጥቃት ተስፋፍቷል ብሎ ባወጣው በዚህ መግለጫ በኪልበቲ ረሱ ዞን ውስጥ ያሉ የተለያዩ አምስት ወረዳዎችና የአብአላ ከተማን መቆጣጠሩን አመልክቷል።
በመግለጫው ላይ ህወሓት አማፂያን የአብአላ ወረዳን፣ የመጋሌ ወረዳን፣ የኤረብቲ፣ የኮነባ እና የበራህሌ ወረዳዎችን መቆጣጠራቸው ተመልክቷል። ቢሮው እንዳለው አሁን በህወሓት እየተካሄደ ያለው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት “ሰርዶን በመያዝ የኢትዮ-ጂቡቲን መስመርን ለመቆጣጠር እና አፋርን እንደ መደራደሪያ ለመጠቀም” ያለመ መሆኑን ገልጿል።
ህወሓት ቀደም ሲል በአፋር ኃይሎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰዱን የገለጸ ሲሆን አሁን ተጠናክሮ ቀጥሏል በተባለው ጥቃት ዙሪያ ግን እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም። በተጨማሪም የፌደራል መንግሥቱም በአፋር ክልል ስላለው ጦርነት ያለው ነገር ባይኖርም ከሳምንት በፊት የአገሪቱ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በህወሓት በኩል ለሚፈጸሙ ጥቃቶች አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ መግለጹ ይታወሳል።
“የኢትዮ-ጂቡቲ መተላለፊያ ኮሪደር ዋና መስመርን ለመቁረጥ በሜካናይዝድ የታገዘ ከባድ ውጊያ እያካሄዱ ነው”
የአፋር ክልል ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንዳሉት የህወሓት ኃይሎች ከባድ ጥቃት በከፈቱባቸው የክልሉ አካባቢዎች ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ውጪ የፌደራል መከላከያ ሠራዊት የተሰማራባቸው ባለመሆናቸው በነዋሪዎች፣ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት ላይ በከባድ መሳሪያ ጉዳት ደርሷል።
የኮምዩኒኬሽን ቢሮው ባወጣው መግለጫ ህወሓት ከሳምንት በፊት ከተቆጣጠራቸው የአብአላ ከተማ፣ የአብአላ ወረዳ፣ የመጋሌ ወረዳ እና የኤረብቲ ወረዳዎች ባሻገር ገፍቶ እንዳይሄድ የክልሉ ልዩ ኃይል ከባድ የመከላከል ውጊያ አድርጎ እንደነበር ጠቅሷል።
ነገር ግን የህወሓት አማፂያን በአፋር ክልል ላይ በከፈቱት ጥቃት የሜካናይዝድ ጦር በማሰማራት በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመፈፀም “በራህሌ እና ኮነባ ወረዳን በመቆጣጠር የጅምላ ግድያና ዘረፋ እያካሄዱ ነው” ሲል ከስሷል።

ክልሉ እንዳለው የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ላይ እያካሄዱት ባለው ጥቃት “ኪልበቲ ረሱ ዞንን በአጠቃላይ በመቆጣጠር ሰርዶ ድረስ ዘልቆ በመግባት የኢትዮ-ጂቡቲ መተላለፊያ ኮሪደር ዋና መስመርን ለመቁረጥ በሜካናይዝድ የታገዘ ከባድ ውጊያ እያካሄዱ ነው” ሲል ጨምሮ ገልጿል።
የአፋር ክልል እንደሚለው በአዋሳኝ አካባቢዎቹ በህወሓት ጥቃት የተከፈተው ከታኅሣሥ 10/2014 ዓ.ም ጀምሮ እንደ እንደሆነ በመጥቀስ ከወር በላይ በሆነው በዚህ አዲስ ጥቃት ቡድኑ በተቆጣጠራቸው ወረዳዎችና ጦርነት እያካሄደባቸው ባሉ ወረዳዎች ከባድ የሆነ የሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራን ደርሷል።
ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ጦርነቱ ከሚካሄድባቸውና ከአጎራባች አካባቢዎች ተፈናቅለዋል
የአፋር ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በህወሓት አዲስ በተከፈተው ጥቃት ሳቢያ ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ጦርነቱ ከሚካሄድባቸውና ከአጎራባች አካባቢዎች ለመፈናቀል ተዳርገዋል። ጨምረውም በግለሰቦችና በመንግሥት ተቋማት እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና በእምነት ተቋማት ላይ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ክልሉ እንዳለው የህወሓት ኃይሎች ወደ አፋር ክልል አስከ 150 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቀው የገቡ ሲሆን ቡድኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን “ኃይሉን እና ሜካናይዝድ ጦር በማደራጀት በአዲስ መልክ ለሦስተኛ ጊዜ የከፈተው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው” ብሏል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የአፋር ክልል መስተዳደር እንዳስታወቀው ህወሓት ከአዋሳኝ የትግራይ አካባቢዎች ወደ አፋር ክልል ለሳምንታት ሲያካሂድ የነበረውን የከባድ መሳሪያ ድብደባ ተከትሎ በኪልበቲ ረሱ ዞን በኩል ጥሶ በመግባት በርካታ ወረዳዎችን መቆጣጠሩን አስታውቆ ነበር።
በዚህም ሳቢያ አብአላ፣ መጋሌ እና በራህሌ ወረዳዎችን የህወሓት ኃይሎች ከተቆጣጠሩ ሁለት ሳምንት የሞላቸው ሲሆን፣ የከባድ መሳሪያ ጥቃቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አካባቢዎቹ በህወሓት ኃይሎች እስከተያዙበት ጊዜ ድረስ ጦርነቱን በመሸሽ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመክፈት በዞኑ ስር የሚገኙ ሦስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን የአፋር ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ይህም ለሳምንታት ከዘለቀ ጦርነት በኋላ የህወሓት ኃይሎች ወደ አፋር ክልል በመግባት የተጠናከረ ጥቃት ከፍተው በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን የአፋር ክልል ያሳወቀ ሲሆን ህወሓትም ይህንን ክስ አላስተባበለም።
ህወሓት በወጣው መግለጫ ለሳምንታት ከአፋር ኃይሎች በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ሲከላከሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ሰኞ ጥር 16/2014 በአፋር ክልል ኃይሎች ተደቀነብኝ ያውን ስጋት ለማስወገድ ጠንካራ እርምጃ እንደወሰደና ኃይሎቹ በአፋር ክልል ውስጥ የመቆየትና ግጭቱን የማባባስ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጾ ነበር።
ቢሆንም ግን የአፋር ክልል አንዳንድ ባለሥልጣንት እና ነዋሪዎች እንደሚሉት የህወሓት ኃይሎች የጥቃት አድማሳቸውን በማስፋት በአዋሳኝ አካቢዎች ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄዱ ነው። ይህም ተጨማሪ የክልሉን አካባቢዎች ለመያዝ ያለመ እንደሆነ የአደጋ ስጋት ኃላፊው ለቢቢሲ አመልክተዋል። ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ለስምንት ወራት ያህል ሲካሄድ ቆይቶ ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች ተስፋፍቶ መቆየቱ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ለወራት ቆይተው ነበር።
ከኅዳር ወር መጨረሻ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ሜዳ የተሳተፉበት የፌደራል መንግሥቱ ጦር ሠራዊት ከአማራ እና ከአፋር ኃይሎች ጋር በመሆን ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ካካሄዱ በኋላ የህወሓት ኃይሎች ከሁለቱ ክልሎች ለመውጣት ተገደዋል።
ከትግራይ ደቡብ አቅጣጫ ሰሜንና ደቡብ ወሎን አልፈው ሰሜን ሸዋ እንዲሁም በምሥራቅ በኩል ወደ ሜሌ አቅንተው የነበሩት የህወሓት አማጺያን በፌደራሉ እና በክልል ኃይሎች ጥቃት ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዳፈገፈጉ የተነገረ ሲሆን፣ የህወሓት መሪዎች ግን ለሰላም ሲሉ ተዋጊዎቻቸውን ወደ ትግራይ እንዲመለሱ እንዳደረጉ ገልጸዋል።
ከዚህም በኋላ አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ግጭቶች ባሻገር በአብዛኞቹ አካባቢዎች ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ጋብ ብሎ በርካታ ሳምንታት ቢቆጠሩም የትግራይና የአፋር ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የከባድ መሳሪያ ጥቃቶችና ግጭቶች መልሰው አገርሽተዋል።