የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የከረዩ የገዳ አባላት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ ስለመገደላቸው ያደረገውን ምርመራ ተከትሎ ባወጣው ሪፖርት አመለከተ።

በዚህ ዓመት ኅዳር መጨረሻ ላይ የከረዩ አባ ገዳን ጨምሮ 14 የገዳ አባቶች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ስለመገደላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና ክልሉን የሚያስተዳድረው ብልጽግና ፓርቲ ለአባ ገዳው እና ለገዳ አባቱ ግድያ ተጠያቂው ‘የኦነግ ሸኔ’ የተባለው ታጣቂ ቡድን ነው ብለው ነበር። ኮሚሽኑ ከሁለት ወራት በፊት የተከሰተውን ግድያ ተከትሎ ባደረገው ምርመራ ከግድያው ቀደም ብሎ በአካባቢው በርካታ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን አመልክቷል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ ምን አለ?

ኮሚሽኑ በሰዎቹ ግድያ ላይ በሰበሰባቸው እና ባገናዘባቸው ማስረጃዎች መሰረት 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በመንግሥት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደውና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በጥይት ተመተው የተገድለዋል ብሏል። ይህም ግድያ ከሕግ ውጪ የተፈጸመ ግድያ ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ እንዳገኘው ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

ጥታ ኃይል ባላት ግድያ

የገዳ አባላቱ ከመገደላቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም ኅዳር 21/2014 ዓ.ም. ከክልል፣ ከዞን እና ከፈንታሌ ወረዳ የተወጣጡ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች በመሄድ ውይይትና ቅኝት አድርገው ነበር። ከዚህ በኋላ የፀጥታ ኃይሉ አባላት ከአካባቢው ሲመለሱ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት 11 የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸውን እና በ9 አባላት ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበረ በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ጥቃቱን የተፈጸመው በኦነግ ሸኔ አባላት ነው ያሉ ሲሆን፤ ከጥቃቱ በኋላም ታጣቂዎቹ አስክሬን እንዳይነሳ በመከልከላቸው የሟቾች አስክሬን ለሊቱን ሜዳ ላይ አድሮ እስከ ኅዳር 22/2014 ዓ.ም. ድረስ መቆየቱን ያስረዳሉ። አንድ ከጥቃቱ የተረፈ የፖሊስ አባል፤ “ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩት ‘የኦነግ ሸኔ’ አባላት ሲሆኑ ከመካከላቸው የማውቃቸው የአካባቢው ተወላጆች አሉበት፤ ታጣቂዎቹ በተኮሱት ጥይት ፖሊስ ሲወድቅ እልልታ ያሰሙ ነበር” ሲል ለኢሰመኮ ተናግሯል።

በቀጣይ ቀን ምን ተፈጠረ?

አስራ አንዱ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በተገደሉ በቀጣይ ቀን ኅዳር 22/2014 ዓ.ም. እኩለ ቀን አካባቢ ከ100 ያላነሱ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና የመደበኛ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች የገዳ አባላቱ ሰፍረው ወደሚገኙበት ቦታ መምጣታቸውን የዓይን እማኞች ለኮሚሽኑ ተናግረዋል። የፖሊስ አባላቱ በቦታው እንደደረሱ ቤት ለቤት በመዞር በአካባቢው የነበሩ 39 ወንድ የገዳ አባላትን ትጥቅ አስፈትተው በአንድ ቦታ እንደሰበሰቡ ነዋሪዎች ለኢሰመኮ መርማሪ ቡድኑ አስረድተዋል።

አንድ የዓይን እማኝ የፖሊስ አባላቱ “‘በሀሮ ቀርሳ የተገደሉት ፖሊሶችን ማን ነው የገደላቸው?’ እያሉ ደጋግመው እየጠየቁ . . . ይዝቱባቸው ነበር። እነሱም ድርጊቱ ሌላ ቀበሌ ላይ የተፈጸመ በመሆኑ እንደማያውቁ አስረዷቸው። ፖሊሶቹ ግን ‘ካልነገራችሁን እንገድላችኋለን’ እያሉ ያስፈራሯቸው ነበር’ ይላል። በመቀጠልም የፀጥታ ኃይል አባላቱ የያዟቸው 39 ሰዎች ሰዎችን በጭነት መኪና ላይ ከነበሩበት ቦታ ርቆ ወደሚገኝ እና ‘ሃምሳ አምስት’ ወደሚባል መንገድ አጠገብ ኛቆ በሚባል ቦታ እንደወሰዷቸው ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ሰዎች ያስረዳሉ።

39ኙ ሰዎች በሁለት ቡድን እንዲከፍሉ መደረጉን፤ አባ ገዳ ከድር ሀዋስን ጨምሮ 16 ዋና ዋና የገዳ አባላት በአንድ ቦታ እንዲሆኑ ቀሪዎቹ 23 ሰዎች ደግሞ በመኪና ተጭነው ወደ ሌላ ስፍራ መወሰዳቸውን ለኮሚሸኑ ቃላቸውን የሰጡት የዓይን እማኝ ገልጸዋል። “የ16ቱን ሰዎች ቡድን ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ከወሰዷቸው በኋላ በረድፍ እንዲተኙ ተደረገ፣ በመጨረሻም የሚገደሉበት ሰዓት እየደረሰ እንደሆነ ተነገራቸው። . . . ለእያንዳንዳቸው ገዳዮች ተመደቡ። ከ12፡00 ሰዓት በኋላ እንዲገድሏቸውም ትዕዛዝ ተሰጣቸው።”

ከዚህ በኋላ ኢሰመኮ አባ ገዳ ከድር ሀዋስን ጨምሮ በስም የሚጠቅሳቸው 14 ሰዎች በሆዳቸው እንደተኙ መገደላቸውን እና ሁለት ሰዎች ደግሞ ከተኙበት ተነስተው ወደ ጫካ በመሮጥ እየተተኮሰባቸው ማምለጣቸውን ገልጸዋል ይላል። የገዳ አባላት ግድያን የሰሙ የቤተሰብ አባላት በቀጣይ ቀን ኅዳር 23 ንጋት ላይ የሟቾችን አስክሬን ለማንሳት ወደ ስፍራው ቢያቀኑም፤ ‘አስክሬን አታነሱም’ ተብለው ከብዙ ጥረት እና ድርድር በኋላ አስክሬኖቹ ከሜዳ ላይ ሲነሱ ሟቾች ከጀርባ በኩል ወገባቸውና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሩባቸውና ኅዳር 24 መቀበራቸውን ለኢሰመኮ ተናግረዋል።

በመንግሥት ኃይሎች የተወሰዱት የተቀሩት 23 የገዳ አባላት ወዴት እንደተወሰዱ ለሁለት ሳምንታት ሳይታወቅ ቆይቶ፤ ከተወሰዱት መካከል አንዱ የነበረው ጅሎ ቦረዩ የተባለ የጅላ አባል ሕይወቱ አልፎ አስክሬኑ በሞጆ ከተማ ከሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ለቤተሰብ መሰጠቱ በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል። በአስክሬኑ ጭንቅላት ላይ የመፈንከት፣ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ቁስል እና የድብደባ ምልክቶች እንዳሉት አስክሬኑን የተቀበሉ የቤተሰብ አባላት ለኢሰመኮ ገልጸዋል።

የመንግሥት ምላሽ

ለገዳ አባላቱ ግድያ የክልሉ መንግሥት እና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ወይም መንግሥት ‘ሸኔ’ ሲል የሚጠራውን ቡድን ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይተዋል። ኮሚሽኑ ግድያው ተፈጽሞበታል የተባለውን የቦሰት ወረዳ ፖሊስን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አለመሳካቱን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ለክልሉ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በደብዳቤ ቢጠይቅም ሁለቱም የክልሉ መሥሪያ ቤቶች ምላሽ አለመስጠታቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል። ኢሰመኮ በኢትዮጵያ ሕግም ሆነ አገሪቱ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት ማንኛውም ሰው በፍርድ ቤት ውሳኔ ካልሆነ በስተቀር በዘፈቀደ ሕይወቱን ሊነጠቅ የማይገባ መሆኑንና መንግሥት የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋሉ ሲል ያስታውሳል።

“ኮሚሽኑ በዚህ ጉዳይ በሰበሰባቸውና ባገናዘባቸው ማስረጃዎች መሰረት 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በመንግሥት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ተወስደውና የፀጥታና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመተው የተገደሉ መሆኑን፤ ይህም ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ አግኝቶታል” ይላል የኮሚሽኑ ሪፖርት።

ግድያው ተፈጸመው በአካባቢው ለፀጥታ ተግባር ተሰማርተው የነበሩ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ላይ ባላታወቁ ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞ ከአስር በላይ ከተገደሉ በኋላ እንደሆነ ተነግሯል። በፀጥታ ኃይሎች፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ መሪዎችና ነዋሪዎች ላይ ግድያ የተፈጸመበት የፈንታሌ አካባቢ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በደቡብ ምሥራቅ ከአርሲ ዞን፣ በደቡብ ምዕራብ በቦሰት ወረዳ፣ በሰሜን ምዕራብ ከአማራ ክልል እንዲሁም በሰሜን ምሥራቅ ከአፋር ክልል ጋር የሚዋሰን ቦታ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *