የመምረጥ መብት በአንድ ማህበረሰብ ወይም ህዝብ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማዳበር እንድሁም ሌሎች መብቶችን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው፡: በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሰዎች ይመሩኛል፣ ያስተዳድሩኛል፣ለመብቶቼ መከበር ይሰራሉ ብለው የሚያስቧቸውን አካላት ይመርጣሉ፡፡ የመምረጥ መብት ልክ እንደ ራስን በራስ የማስተዳደር፣በፖለቲካ የመሳተፍ እና ለሌሎችም መብቶች መረጋገጥ መሰረት ወይም ዋልታ ልንለው እንችላለን፡፡
በሁሉም የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የመምረጥ መብት ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል በእድሜ 18 ያልሞሉ ህጻናት፣ የአዕምሮ እክል ያለባቸው (በፍርድ የተከለከሉ) ሰዎች እንዲሁም በአንዳንድ ስርዓቶች ውስጥ ታራሚዎች ከመምረጥ መብታቸው እንዳይጠቀሙ ይከለከላሉ፡፡ በመርህ ደረጃ የህግ ታራሚዎች መምረጥ መብት ያላቸው ሲሆን እንደ አንዳንድ ሀገራት ህግ እና እንደፈጸሙት ወንጀል ግን የመምረጥ መብታቸው ሊታገድባቸው የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡
በአለም አቀፍ የህግ ድንጋጌዎች ማለትም እንደ የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (UDHR) አንቀጽ 21፣3 የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 25 እንዲሁም እንደ የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር (ACHPR) አንቀጽ 13 ያሉት የህግ ማዕቀፎች ለሰዎች በፖለቲካ ተሳትፎ ላይ የመካተት እንዲሁም የመምረጥ እና የመመረጥ መብትን ያጎናጽፋሉ፡፡ የእነዚህ አንቀፆች መንፈስ የሚያስረዳው በሰዎች መካከል ለመብታቸው መከበር በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጾታ፣ በማንነት ወይም ባሉበት ሁኔታ ልዩነት ሊኖር እንደማይገባ እና በዚህም ምክንያት ከመብቶቻቸው ሊገደቡ እንደማይገባ ነው፡፡ እንዲሁም አባል ሀገራት ለሰዎች መብት መከበር ያለ ምንም አድልዎ ሊሰሩ እንደሚገባ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ ቃል ኪዳን ICCPR አንቀጽ 2(1) በግልጽ ይደነግጋል፡፡
የህግ ማዕቀፉ እንዲህ ተቀምጦ ሳለ በተለያዩ ወገኖች ግን የመምረጥ መብት ለታራሚዎች የሚገባ መብት ነው ወይ በሚለው ዙሪያ የሚነሱ ሁለት አበይት ክርክሮች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ታራሚዎች የመምረጥ መብት አላቸው የሚሉ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ታራሚዎች የመምረጥ መብት ሊኖራቸው አይገባም የሚሉ ናቸዉ። ታራሚዎች የመምረጥ መብት አላቸው ብለው የሚከራከሩት ወገኖች የሚያነሱት ነጥብ ፡- የመምረጥ መብት የዜግነት መብት ሲሆን በምንም መልኩ ከቅጣት ጋር መያያዝ የሌለበት እንደሆነና ታራሚዎች ምንም እንኳን ህግ ጥሰው በቅጣት ላይ ቢሆኑም የህብረተሰቡ አካል መሆናቸውን ወይም ዜግነታቸውን ግን አያጡም ፡፡
እነዚህ ታራሚዎች በእስር እያሉም ይሁን ቅጣታቸውን ጨርሰው፣ በምሕረት ወይም በይቅርታ ሲለቀቁ በሚቀላቀሉት ማህበረሰብ በምርጫ ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን የማበርከት መብት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምርጫ ሠዎች መንግስትን ወይም ተመራጮች ላይ ለመብቶች መከበር ግፊት የሚያደርጉበት እና መብታቸውን የሚያስከብሩበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ታራሚዎች ህግን በመጣሳቸው ሊያጡ የሚገባቸው እንደ መንቀሳቀስ መብት (the right to movement)፣ የግለኝነት መብት (the right to privacy)፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብታቸውን እና መሰል መብቶች ሲያጡ እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ የመሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ለእነዚህ መብቶች መከበር ደግሞ ይወክለኛል ለመብቶቼ መከበር ይሰራል ብለው የሚያስቡትን አካል የመምረጥ መብታቸውን ሊነፈጉ አይገባም! ብለው ይከራከራሉ፡፡
በሌላ በኩል ታራሚዎች የመምረጥ መብት ሊኖራቸው አይገባም ብለው የሚከራከሩት ደግሞ፡- ህግን የጣሱ ሰዎች የህብረተሰቡን ደንብ የጣሱ ናቸው ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዲመርጡ መፍቀድ ማለት ህጉን እነሱ በተመቻቸው መንገድ እንዲቀለብሱት እድል ማመቻቸት እንዲሁም በሌሎች ህግን በሚያከብሩ ሰዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠር ማለት ነው፡፡ ታራሚዎች እንዲመርጡ ተፈቀደላቸው ማለት የራሳቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ በማሰብ ለወንጀል ቅነሳ የማይሰራና ለህግ ማስከበር የማይጥር አካል ሊመርጡ ይችላሉ በማለት ተቃውመው ይከራከራሉ፡፡
የሀገራት ተሞክሮ
የተለያዩ ሀገራት በታራሚዎች የመምረጥ መብት ዙርያ የተለያዩ ተሞክሮዎች አሏቸው፡፡ የዩክሬንን ልምድ ስናይ ታራሚዎች በአካባቢያዊ ምርጫ ላይ የመምረጥ መብት የሌላቸው ሲሆን ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት ታራሚዎች በእስር ባሉበት ወቅት የሚኖሩበት አካባቢ አባላት ላይሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ነው፡፡ የኩየት ተሞክሮ ስናይ ታራሚዎች መምረጥ የሚችሉት እንደፈጸሙት ወንጀል ክብደት ነው፡፡በኩየት በተለይም የእምነት ማጉደል እና በመሰል ወንጀሎች የተፈረደባቸው ሰዎች የመምረጥ መብት እንደሌላቸው ጸሃፊያን ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይ በብራዚል ታራሚዎች የመምረጥ
መብታቸውን የሚያጡት ከስነ ምግባር አንጻር የመምረጥ መብት ቢሰጣቸው አግባብ የማይሆን ከሆነና በፖለቲካ ተሳትፎው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ ተብለው በሚገመቱ ታራሚዎች ላይ ነው፡፡11 እንደ ቤልጂየም፣ ኢትዮጵያ እንዲሁም ቱኒዝያ ያሉ ሀገራት ደግሞ የመምረጥ መብት የሚታገደው በዳኞች ውሳኔ እንደ ተጨማሪ ቅጣት መሆኑን እናያለን፡፡
የታራሚዎች የመምረጥ መብት በኢትዮጰያ፡ የህግ ማዕቀፎች እና ተግባራዊ ተግዳሮቶች
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በአለም አቀፍ ደረጃለሰዎች የመምረጥ መብት የሚያጎናጽፉ የሕግ ማዕቀፎችን በተለይም የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (UDHR) አንቀጽ 21፣ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 25 እንዲሁም የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር (ACHPR) አንቀጽ 13 ስናይ ማንም ሰው በቀጥታም ይሁን በመረጣቸው ተወካዮች በሀገሩ ባሉ የፖለቲካ ምህዳሮች ላይ የመሳተፍ መብት አለው፡፡ ይህም ማለት ሰዎች በህግ መብታቸውን እስካላጡ ወይም ብቁ እስከሆኑ ድረስ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት አላቸው ማለት ነው፡፡
ይህ ጉዳይ ወደ እኛ ሀገር ሲመጣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱት የህግ ማእቀፎች አባል ስትሆን የህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 አለም አቀፍ ስምምነቶች ልክ እንደ ሀገሪቱ ህጎች ሁሉ ተፈጻሚነት እንዳላቸው ያሳያል፡፡ ይህ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 38 መሰረት “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሄር፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የመምረጥ ፣ በማናቸውም የመንግስት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄዱ ምርጫዎች የመመረጥ መብት አለው፡፡”
ይህንን የህገ-መንግስቱን አንቀጽ ስንተነትነው በተለይም ሌላ አቋም ወይም በእንግሊዘኛ other status የሚለው ቃል ላነሳነው ሀሳብ እንደ ጥሩ መነሻ በመሆን ለታራሚዎች መብት እንደ መከራከርያ ሊያገለግለን ይችላል፡፡ ይህ አንቀጽ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በማየት መብታቸውን እንዳያጡ የተቀመጠ ሲሆን የአንቀጹን አውዳዊ ፍቺ ሰፋ አድርገን ስናየው ለፍርድ ቀርበው በእስር እያሉም ይሁን ለፍርድ ላልደረሱ ለቀጠሮ እስረኞች መብት መረጋገጥ የቆመ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ አንቀጽ 2 በህጋዊነት መርህ (principle of legality) መሰረት መብት ላይ የሚደረጉ ገደቦች በህግ የተገለጹ ካልሁነ ወይም በግልጽ ክልከላ ወይም ቅጣት ባልተቀመጠበት ሁኔታ መብትን መንፈግ አግባብ አለመሆኑና ከሰብአዊ መብት እሳቤ/ፍልስፍና ተቃራኒ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በወንጀል ህጉ መሰረት በሀገር ላይ የሚደረጉ ወንጀሎችን ልክ እንደ የሀገር ክህደት፣ ስለላ እና መሰል ወንጀሎችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ የመምረጥ መብት እገዳ እንደሚጥል ይጠቁማል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ወንጀሎች እንዳሉ ሆነው ለሌሎች ወንጀሎችም ዳኞች አግባብነቱን እና አስፈላጊነቱ በማየት እንደ ተጨማሪ ቅጣት የመምረጥ መብት ላይ ገደብ ሊጥሉ እንደሚችሉ አንዳንድ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው እስረኛ ወይም ታራሚ በመሆኑ ብቻ የመምረጥ መብቱን አያጣም ማለት ነው፡፡ የመምረጥ መብቱን የሚያጣው የሰራው ወንጀል በሞት ወይም በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን እንዲሁም በችሎት በግልጽ የመምረጥ መብቱን እንዲያጣ የተፈረደበት እንደሆነ ነው፡፡
ከእነዚህ ዋና ዋና የህግ ማዕቀፎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ምርጫ ቦርድ ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕ የሚኖሩ ወታደሮች ሲቪል ሰራተኞች ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ዜጎች ፣ ከመኖርያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንዲሁም በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ የመምረጥ መብታቸው ያልተገፈፈ ዜጎች በምርጫ የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መራጮች በሚገኙበት ቦታ ወይም አካባቢ ልዩ ምርጫ ጣቢያ ሊቋቋም እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ ይህ አንቀጽ በግልጽ በእስር ቤቶች በልዩ ሁኔታ የምርጫ ጣቢያ መቋቋም እንዳለበትና በህግ የመምረጥ መብታቸውን ላላጡ ሰዎች ሁሉ የዚህ መብት ተጠቃሚ እንደሆኑ ያረጋግጥልናል፡፡
ነገር ግን ወደ አፈጻጻሙ ስንመለስ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን መብት የማስከበር ስራዎች ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይታያል፡፡ በሀገራችን እንኳን የተፈረደበት ታራሚ ይቅርና ፍርድ የሚጠባበቁ በቀጠሮ ያሉ እስረኞች እንኳን በምርጫ ይሳተፉሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው፡፡ በተለይም ፍርድን የሚጠባበቁ ሰዎችን መብት ማሳጣት ማለት በህገ መንግሰቱ መሰረት እንደ ንጹህ የመገመት መብት (presumption of innocence) የሚለውን መሰረታዊ መብት መጣስ ይሆናል፡፡ በሀገራችን የታራሚዎችን የመምረጥ መብት የሚያረጋግጥ የህግ ማዕቀፍ ያለ ቢሆንም ይህ ፅሁፍ ትኩረቱ ካደረጋቸው ቡድኖች ማለትም በማረሚያ ቤት ካሉ ሰዎች አንፃር ግን ብዙ ክፍተቶች አሉ፡፡
ይህ ክፍተት በዜጎች መካከል ልዩነት ከመፍጠሩም ባለፈ የታራሚዎችን ወይም ተጠርጣሪዎችን መብት ያላግባብ እንዲጣስ መንገድ ከፍቷል፡፡ ስለዚህ በማረሚያ ወይም ጊዜያዊ ማቆያ ቤት ያሉ ሰዎች የሀገሪቱ ዜጋ እንደመሆናቸው፤ በህግ ጥላ ስር በመሆናቸው ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ በሀገራዊ ምርጫዎች መሳተፍ እንድችሉ መብታቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህ ሲባል ግን በህግ ወይም በዳኞች ውሳኔ ይህንን የመምረጥ መብታቸውን የተነፈጉትን አያካትትም፡፡ ስለሆነም መንግስት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እንደ የመራጮች ስልጠና እንዲሁም ኮሮጆዎችን በማዘጋጀት ልክ እንደሌሎች መብቶች ሁሉ በማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎችም የመምረጥ መብት እንዲከበር፣ እንዳይጣስ አስፈላጊ ሁኔታዎችን በማሟላት ለመብቱ መረጋገጥ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
በማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎች የመምረጥ መብት ካልተረጋገጠ መንግስት ለምርጫ ያሰጉኛል የሚላቸውን ሰዎች ወይም ቡድኖች ወደ ማረሚያ በመወርወር የመምረጥ እንዲሁም የመመረጥ መብታቸውን ሊነፍግ እና ተሳትፏቸውን ሊገድብ የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ በመሆኑ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለታራሚዎች እና በቀጠሮ ላሉ ተጠርጣሪዎች የመምረጥ መብት መረጋገጥ የበኩላቸውን ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡