ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘገበ።

ኤፒ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ለሰዓታት የዘለቀ ውይይት ያደረጉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቡድን አባላት ነግረውኛል ብሎ እንደዘገበው ከሆነ፤ የፌደራሉ መንግሥት ለ15 ወራት ያህል ሲዋጋ ከነበረው ከህወሓት ኃይሎች ጋር ልዩነቱን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ ነው። የአሜሪካውያን – ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቲ) ሊቀመንበር የሆኑት መስፍን ተገኑ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የነበራቸውን የአምስት ሰዓታት ውይይት ሲገልጹ፤ “ይህን ነገር (ጦርነቱን) ለማቆም ጽኑ ፍላጎት አለ . . . በእርግጥር ይህ እንዲሁን ሌላኛው ወገንም ፍቃደኛ መሆን አለበት” ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ “ድርድር ይኖራል። የአገሪቱን ጥቅም የሚያስቀድም ምክንያታዊ ድርድ” ስለማለታቸው ኤፒ ሊቀመንበሩን ዋቢ አድርጎ አስነብቧል። ሊቀመንበሩ ኢትዮጵያን በቅርቡ የጎበኙት አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ስለዚሁ ሂደት ሳያውቁ እንደማይቀሩ መስፍን ለኦሺየትድ ፕረስ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆኑ መንግሥታቸው ከህወሓት ጋር ይደረጋል ስለተባለው ድርድር በይፋ የተባለ ነገር የለም። በኤፒ ዘገባ ላይም የዲያስፖራው ቡድን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር መቼ እንደተገናኙ እና የውይይቱ አጀንዳ ምን ነበር የሚለው አልተጠቀሰም።

የፌደራሉን መንግሥት እና ህወሓትን የማደራደር ጥረት

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ተዋጊ ወገኖችን ለማደራደር ዓለም አቀፍ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይቷል። አሜሪካ እና የአፍሪካ ሕብረት ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በውይይት ፈትተው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው ጥረት ሲያደርጉ ነበር። የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ተገናኝተዋል። የህወሓት ኃይሎችንም በጎረቤት አገር ኬንያ አግኝተው ስለማነጋገራቸው አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛው የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝደንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ እንዲሁ ጠቅላይ ሚንስትሩን በአዲስ አበባ፤ የህወሓት አመራሮችን ደግሞ በመቀለ በተደጋጋሚ አነጋግረዋል። ባለፈው ሳምንት ደግሞ አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳትርፊልድ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል። ይህ ሁሉ ጥረት ግን ሁለቱን አካላት ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ለማስቻል ቢሆንም አስካሁን ተጨባጭ ውጤት አላሳየም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ

‘ጦርነቱን ለማስቆም ተስፋ ሰጪ ጥረት አለ’

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጦርነቱን ለማብቃት እና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ከአንድ ሳምንት በፊት ገልጸው ነበር። ጉተሬዝ ይህን ያሉት የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ ከሆኑት ከኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ጦርነት በስልክ ከተወያዩ በኋላ ባወጡት መግለጫ ነበር።

ኦባሳንጆ ከጉተሬዝ ጋር ከመነጋገራቸው አንድ ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ እና መቀለ በመጓዝ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና ከህወሓት መሪዎች ጋር ውይይት አድርገው ነበር።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት

15 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት በትግራይ ክልል ውስጥ ለወራት ከተካሄደ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ሲያስወጣ የትግራይ ኃይሎች በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ጥቃት መክፈታቸው ይታወሳል። በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው የቆዩት የትግራይ ኃይሎች የፌደራሉ መንግሥት መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ከፍቶ ከአብዛኛው የአማራ እና የአፋር ክልል ክፍሎች ማስወጣት ችሏል።

ይህንንም ተከትሎም ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ የፌደራሉ መንግሥት ሲያካሂዳቸው ከቆየው የአየር ጥቃቶች ውጪ፤ ይህ ነው የሚባል የተጠናከረ ጦርነት ስለመካሄዱ ሳይዘገብ ቆይቷል። ባለፉት ቀናት ግን የህወሓት ኃይሎች በከባድ መሳሪያ በመደገፍ በአዋሳኝ የአፋር ክልል ወረዳዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ሦስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን እና በጥቃቱ በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የአፋር ክልል ገልጿል።

ህወሓት በበኩሉ ለሳምንታት ኃይሎቹ ከአፋር በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ሲከላከሉ መቆየታቸውን በመግለጽ የመንግሥት አጋር በሆኑት በአፋር ክልል ኃይሎች “የተደቀነውን ስጋት ለማስወገድ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ተገደናል” ያለ ሲሆን፣ ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል ውስጥ የመቆየትና ግጭቱን የማባባስ ፍላጎት እንደሌላቸው አመልክቷል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *