የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሌፍተናንት ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተዋል።

ጄነራል ዳጋሎ ላለፉት ሦስት ዓመታት በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ባለችው ሱዳን ከጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን በመቀጠል ቁልፍ ሰው ሲሆኑ ከጀርባቸው ባሰለፉት ወታደራዊ ኃይልም በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሰው ናቸው። ሔሜቲ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ፣ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ከቆየው የሻከረ ግንኙነት አንጻር ድንገተኛና ያልተጠበቀ ነበር።

በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች እጅ የቆየውንና ሁለቱ አገራት የይገባኛል ጥያቄ አንስተው ለዓመታት ሲነጋገሩበት የነበረውን የድንበር አካባቢን በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የሱዳን ጦር ከተቆጣጠረ በኋላ ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቷል። ኢትዮጵያ አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና መካረር በማርገብ በኩል ትልቅ ሚና ነበራት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በአገሪቱ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወታቸው ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያና የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ካርቱምና አዲስ አበባ በመሄድ በሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ ተደጋጋሚ ምክክር ያደርጉ ነበር። ከድንበር አለመግባባቱ በኋላ ግን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከመቀዛቀዝ ባሻገር አልፎ አልፎም ሲካሰሱ ቆይተዋል። ይህ የጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሁለት ቀናት የአዲስ አበባ ቆይታ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በከፍተኛ የሱዳን ባለሥልጣን የተደረገ የመጀመሪያው ጉብኝት ነው።

ከቁልፍ ባለሥልጣናት ጋር የተደረገ ቆይታ

ዳጋሎ አዲስ አበባ ሲደርሱ ከተቀበሏቸው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንጻር ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ በኩል በቀላሉ የታየ እንዳልነበረ መረዳት ይቻላል። ለሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄኔራል ዳጋሎ አቀባበል ያደረጉላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስትር፣ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ነበሩ። በማስከተልም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ከአገሪቱ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ከሆኑት ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር መገናኘታውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ይህም የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በወታደራዊ እና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መወያየታቸውን የሚያመለክት ሲሆን፣ የሱዳን ዜና ወኪል በበኩሉ ጄነራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነቶችና የአገራቱን ሕዝቦች የበለጠ በሚጠቅም እና የበለጠ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ዘግቧል። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብረሃም በላይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውንና “ተቀራርበን መስራት እንደሚገባን ተግባብተናል” ብለዋል።

ንታዊ እርምጃዎች

በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ሌላኛው ያለመግባባት ምንጭ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እየተገነባ ባለበትና ከሱዳን ጋር ተወሳኝ በሆነው የቤኒሻንጉል ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታም ሌላኛው የአገራቱ ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል። በአዋሳኝ ድንበሩ አካባቢ ባለው ክልል ውስጥ ከሱዳን በኩል የሚገቡ ናቸው የሚባሉ ታጣቂዎች ጥቃት እየፈጸሙ፣ ለበርካታ ሰዎች ሞትና መፈናቀል ከመሆናቸው ባሻገር የክልሉ አብዛኛው አካል በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን አድርጓል።

በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በሚመለከት ከሳምንታት በፊት የሱዳን ብሉ ናይል ግዛት እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውይይት ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን፣ በጋራ ለመሥራትም ስምምነት አድርገዋል። በተጨማሪ ደግሞ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት መሻከርን ተከትሎ ለስድስት ወራት ተዘግቶ የቆየው ሁለቱን አገራት የሚያገናኘው የጋላባት መተማ ዋና መንገድ ተከፍቶ እንደነበር ይታወሳል።

ምንም እንኳን ይገባኛል በተነሳበት እና ኢትዮጵያ ሱዳን በወረራ ይዛዋለች ባለችው አወዛጋቢው የድንበር አካባቢ የታየ ለውጥ መኖሩ ባይዘገብም ባለፈው ታኅሣሥ ወር የመቀራረብ ሁኔታዎች ታይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ጋር በአዲስ አበባ

የከረመ ውዝግብ

ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ጦሯን ከሱዳን ጋር ከሚያዋስናት ድንበር ማስወጣቷን ተከትሎ ነበር ሱዳን ወታደሮቿን ወደ አወዛጋቢው አካባቢ ያሰማራችው። ይህም በኢትዮጵያ በኩል ከፍ ያለ ቅሬታን ፈጥሮ ቆይቷል። የሱዳን ጦር በአካባቢው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን አርሶ አደሮች ሰፋፊ የሰሊጥ እርሻዎችንና መጋዘኖችን በመቆጣጠር ለቅቀው እንዲወጡ ማድረጉ ተዘግቧል። የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ጦር ኃይሉ ሕጋዊ ግዛታቸውን ማስመለሳቸውን በመግለጽ የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር መግለጻቸውም ተዘግቧል።

ሁለቱም አገራት ወደ ወታደራዊ ግጭት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በሌላ ግጭት ውስጥ የገባችበትን ጊዜ ጠብቃ ሱዳን ከያዘቻቸው ቦታዎች እንድትወጣና ለዓመታት ጉዳዩ ሲታይ በነበረበት የድንበር ኮሚሽን በኩል እንዲፈታ ስትወተውት ነበር። ከዚህ ባሻገርም ሱዳን ከአንድም ሁለት ጊዜ ከኢትዮጵያ በኩል ያሉ ሚሊሻዎች በወታደሮቿና በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል ብላ ከስሳለች። ከኢትዮጵያ ኃይሎች በኩል ተሰነዘሩብኝ ባለቻቸው ጥቃቶችም ጥቂት የማይባሉ ወታደሮቿ እንደተገደሉ ገልጻለች።

በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ሁለቱ አገራት በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ ታጣቂዎች ሰርገው እየገቡ ጥቃት እንደሚያደርሱ በመግለጽ፣ የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እንደሚወስዱ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ምላሽ ሰጥተዋል።

ግንኙነትን ማሻሻል

ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ፣ ከኤታማዦር ሹሙ እና ከደኅንነት ኃላፊው ጋር መገናኘታቸው፤ ምንም እንኳ በይፋ የተገለፀ ነገር ባይኖርም፣ ከሱዳን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ቀውስ ባሻገር የሁለቱ አገራት መቃቃር ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገራቸው ማሳያ ነው። ከአንድ ዓመት በላይ ከቆየው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ቀጥሎ የአገሪቱ ሠራዊትና የደኅንነት ተቋም ቅድሚያ ትኩረት ከሚሰጧቸው ጉዳዮች መካከል፣ ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ቀዳሚ ርዕስ መሆኑ አይቀሬ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ከህወሓት ጋር ለወራት ባካሄዱት ጦርነት በአማጺያኑ የተያዙ ቦታዎችን መልሰው መያዛቸውን ተከትሎ፣ የተለያዩ ወገኖች ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ለዓመታት በቆየ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን በበላይነት እየመራ ያለው ጦር ሠራዊት፣ በሕዝባዊ ተቃውሞ ተወጥሮ ባለበት በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር ላለው የድንበር ቁርሾ የውይይት መፍትሔ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ይመስላል።

በተጨማሪም አምባገነኑ ኦማር ሐሰን አልበሽር ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ፍጥጫ በማርገብ ጉልህ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ፣ አሁንም እየተባባሰ ያለውን ቀውስ በመፍታት በኩል እንድትረዳ ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ቢሆንም ግን ከኢትዮጵያም ሆነ ከሱዳን በኩል የውይይቱን ዝርዝር ይዘት በተመለከተ አስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም፤ እንዲሁ በጥቅሉ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ማተኮሩ ተገልጿል።

የአሜሪካ ልዑካን ጉብኝት

በሱዳን ውስጥ የዘለቀውን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሰየማቻው ይታወቃል። የመጀመሪያውን ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ተክተው ሥራቸውን የጀመሩት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ በቀዳሚ ጉዟቸው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የሆኑትን ሞሊ ፊን አስከትለው ካርቱምና አዲስ አበባን ጎብኝተው ነበር።

ባለፈው ሳምንት ወደ ሱዳን በመሄድ ከሱዳን ጦር ኃይል ባለሥልጣናትና ከአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች ጋር ተወያይተው በአገሪቱ መረጋጋት እና የሽግግር ሂደቱን በተመለከተ ተወያይተዋል። ስለ ልዩ መልዕክተኛው ቡድን ቆይታ ዝርዝር መረጃ እስካሁን ድረስ ይፋ ባይሆንም ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም መወያየቱ ተነግሯል። ምንም እንኳ ቀጥተኛ ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ባይታወቅም ሌፍተናንት ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሁለቱ አገራት ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የመጣ ነው።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *