በአዲስ አበባ ከተማ ምዕራባዊ ክፍል ሐሙስ ከጥምቀት በዓል በኋላ በነበረ የወይብላ ማርያምን ታቦት የማስገባት ሥነ ሥርዓት ላይ በምእመናንና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመላው አገሪቱ የተከበረውን የጥምቀት በዓልን አስመለክቶ ዛሬ አርብ ባወጣው መግለጫ ላይም በሰዎች ላይ ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱን ገልጿል። በዚሁ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ግርግር አለመግባባት የፀጥታ ኃይሎች ጥይት እና አስለቃሽ ጋዝ መተኮሳቸውንና በዚህም ሳቢያ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ክስተቱን የሚያሳዩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ የአድማ በታኝ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ የሚታይ ሲሆን የተኩስ ድምጽን ተከትሎ በርካቶች ሲጮሁና ሲሯሯጡ ይታያሉ። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በዓሉ በመላ ኢትዮጵያ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ መከበሩን አመልክቶ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና በቡራዩ አዋሳኝ ወይብላ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር በዓሉ መስተጓጎሉንና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱ ገልጿል።

የመንግሥት መግለጫ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ያልገለጸ ሲሆን ቢቢሲ ከፖሊስና ከሆስፒታል ምንጮች በክስተቱ ስለሞቱ ሰዎችና ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰዎች ትክክለኛ አሃዝ ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ገዳመ እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ወንጌል የሆኑት መምህር እሱባለው የወይብላ ማርያምን ታቦት ካደረበት ወደ መንበሩ ሲመልሱ መንገድ ላይ በወጣቶች እና በፀጥታ አካላት አታልፉም ተብለው መከልከላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በትናንትናው ዕለት ታቦታቱ ካደሩበት ቦታ ወደ መንበራቸው ሲመለሱ አዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል አካባቢ ላይ የመንግሥት ፀጥታ አካላት እና ዱላ የያዙ ወጣቶች በሕብረት አታልፉም ብለው ግርግር ተከሰተ” ብለዋል መምህር እሱባለው። “ምንድነው ብለን ስንጠይቅ ባንዲራ አድርጎ አታልፉም ተባልን” ይላሉ። መምህር እሱባለው የፀጥታ አካላቱ መሳሪያ እና አስለቃሽ ጪስ በመተኮሳቸው የሰው ሕይወት መጥፋትን ጨምሮ በበርካቶች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ይናገራሉ።

የገዳመ እየሱስ ሰንበት ትምህር ቤት አገልጋይ የሆነችው እና በቦታው የነበረችው ወጣት ንግሥት ጌታቸው ደግሞ አለመግባባቱን ተከትሎ በጥይት የመመታት ጉዳት ያጋጠማቸው ከፊት የነበሩ ምዕመናን መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጻለች። ንግሥት ሐሙስ ጥር 12/2014 ዓ.ም. የነበረውን ሁኔታ ስታስረዳ፤ አመሻሽ 11 ሰዓታ አካባቢ ታቦቱን ወደ መንበሩ እየመለሱ ሳለ በተለምዶ የሺ ደበሌ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ አታልፉም ተባልን ትላለች።

“አምናም ማለፍ አትችሉም ተብለን ነበር። ምን እንደተፈጠረ አስተባባሪዎች እንዲያጣሩ ተላኩ” ትላለች። የሺ ደበሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ አታልፉም ብለው የከለከሉት የመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች ካህናት እና መዘምራን እንዲያልፉ ፈቅደው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ያሉባቸውን አልባሳት የለበሱት ግን እንደማያሳልፉ ተናገሩ በማለት ታስረዳለች። “አብዛኛው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ያለበትን ቀሚሶችን፣ ቲሸርቶችን ለብሷል። እነሱ ደግሞ መርጠን እናስገባለን አሉ። አስተባባሪዎቹ አልተስማሙም። ከዚህ ንግግር በኋላ አስለቃሽ ጪስ መተኮስ ተጀመረ። የወደቁ እና የተረጋገጡ አሉ” በማለት የነበረውን ሁኔታ አስረድታለች።

እስካሁን በምን ያህል ሰው ላይ ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ አልቻልንም የምትለው ንግሥት፤ “ስልካቸው የማይሰራ፤ የት እንዳሉ የማናውቃቸው አገልጋዮች አሉ” ትላለች። መምህር እሱባለው በበኩላቸው፤ ከሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተመሳሳይ ነገሮች ሲከሰቱ እንደነበረ ያስታውሳሉ። “እኔ እንኳ በማውቀው ይሄ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በጉዳዩ ላይ ከአከባቢው ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ሲሞከር ‘ከላይ ነው የታዘዝነው’ የሚል ምላሽ ብቻ ነው የሚሰጡት” በማለት ይናገራሉ። “በአገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ፤ ‘በዚህ አታልፍም፤ በዚህ አትገባም’ መባል በጣም ያሳዝናል” ካሉ በኋላ፤ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጉዳዩን አጣርቶ ምላሽ እንዲሰጠው መምህር እሱ ባለው ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም በጥምቀትና በሌሎች ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ ምእመናን ይዘውት በሚወጡት የፌደራል መንግሥቱ አርማ የሆነው ኮከብ የሌለበት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ምክንያት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር አለመግባባት በተለያዩ ስፍራዎች ሲፈጠር ታይቷል። በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሆነችው ቡራዩ አዋሳኝ አካባቢም ተመሳሳይ ሁኔታ ሲፈጠር ይህ የመጀመሪያ አለመሆኑን ምእመናን የተናገሩ ሲሆን፣ ከዚህ በፊትም ባሉ ተከታታይ ዓመታት ችግር መከሰቱን ያስታውሳሉ። ሐሙስ ዕለት ያጋጠመው ግን የሰው ህእወት የጠፋበት ሲሆን ክስተቱን ተከትሎ ቢቢሲ በሰዎች ላይ የደረሰው ዝርዝር ጉዳት ከሆስፒታል እና ከፖሊስ ምንጮች ለማጣራት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ጉዳት የደረሰባቸው እና ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስክሬን ተወስዶበታል ወደ ተባለው የጤና ተቋም ስልክ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልም። በተመሳሳይ ለሰዎች ግድያ እና ጉዳት በዓይን እማኞቹ ተጠያቂ የተደረገው የኦሮሚያ ፖሊስ አዛዥን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። የቡራዩ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽነርም ለጥያቄዎቻችን ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ቢሰጡንም መልሰን በስልክ ልናገኛቸው አልቻልንም።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ በተከሰተው ችግር ምክንያት በዓሉ በተገቢው መንገድ ባለመከበሩ፣ እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል። ጨምሮም ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለአካል ጉዳት ምክንያት የሆነውን ክሥተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ ያቀርባል ሲል መግለጫው አመልክቷል።

አርብ

ሐሙስ ዕለት በተፈጠረው ግርግር ወደ ኋላ ተመልሳ ቀራንዮ መድኃኔዓለም የቆየችውን ወይብላ ማርያም ታቦትን ለማስገባት በርካታ ምዕመናን በመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተገኝተው ታቦቱን ሸንተው በሰላም ሥነሥርኣቱ መጠናቀቁን ቢቢሲ በስፍራው ካሉ ሰዎች ተረድቷል። ወጣት ንግሥት “ትናንት አታልፉም የተባልንበትን የሺ ደበሌን አልፈናል። ሁሉም ሰላም ነው። “ስትል እኩለ ቀን ላይ ለቢቢሲ ተናግራለች። መምህር እሱባለውም የበዓሉ ሂደት በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ