የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የማስቆም “ልዩ ኃላፊነት” አለባቸው አለ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ላሳዩት ተነሳሽነት 2019 (እአአ) ላይ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ግንባታ ለተጫወቱት ሚና እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ በምሥራቅና በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፅኦ ሽልማቱ እንደተበረከተላቸው የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር ቤሪት ሬይሳ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ከተረከቡ በኋላ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውና ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን ያስከተለው ጦርነት የተቀሰቀሰው። በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካካሄደ ባለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ምዕራባውያን መንግሥታት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴም ዛሬ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጦርነቱን ለማስቆም ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ በመጠየቅ ጦርነቱን ለማስቆም ዓለም አቀፍ ጥሪውን ተቀላቅሏል።  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገር ላይ ህወሓት ያወጀውን ጦርነት ለማስቆም ጥረት ማድረጋቸውን ለአጅንስ ፕሬስ ተናግረዋል። “. . . ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት በአገር ላይ የከፈተውን ጦርነት ብቻ ሳይሆን አፍራሽ እንቅስቃሴዎቹን ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ ነበር” ብለዋል።

በዚህ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የክልል ኃይሎች እና የኤርትራ ሠራዊት ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ባለፉት 14 ወራት ጦርነት ሲካሄደ ቆይቷል። በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ኃይሎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የጅምላ ግድያዎችን መፈጸማቸውን በሚመለከት የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ያመለክታል።

ጦርነቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን ስለማጣታቸው የተገለጸ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ለችግር መጋለጣቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ጦርነቱ ጋብ ቢልም የፌደራሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን እየሰነዘረ ሰለመሆኑ እና ይዘዋቸው ከነበሩት የአማራ እና አፋር ክልሎች የወጡት የህወሓት ኃይሎችም ለዳግም ጦርነት ዝግጅ እያደረጉ ስለመሆናቸው እየተገለጸ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ