የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ እገዳ አለመጣሉን እና ሕዝቡ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳያገኝ እንቅፋት የሆነው ህወሓት ነው አለ።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከክልሉ ካስወጣ በኋላ ለትግራይ ሕዝብ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያለ ምንም መስተጓጐል በአፋር አብአላ በኩል በቀጥታ እንዲደርስ ማድረጉን አስታውሷል። በዚህም ሐምሌ አጋማሽ 2013 ዓ.ም. አንስቶ ከ10ሺህ በላይ በሚሆኑ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ አድርጓል ብሏል።

ነገር ግን “የህወሓት ቡድን እርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ የገቡትን 1010 ተሽከርካሪዎች እዚያው በማስቀረት በአማራና በአፋር ክልል ላይ ወረራ ሲፈጸም የሠራዊቱ ማጓጓዣ አድርጐ ተጠቅሞባቸዋል” ሲል መንግሥት ከሷል። በተጨማሪም ቡድኑ በኮምቦልቻና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ “የመንግሥትና የግል መጋዘኖችን ከዘረፈ በኋላ ወደ ትግራይ እርዳታ በሚገባበት በአብዓላ በኩል ጥቃት በመክፈት መስመሩ እንዲዘጋ በማድረግ” ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ የእርዳታ አቅርቦት እንዲስተጓጎል አድርጓል ሲል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አስታውቋል።

ጨምሮም ምንም እንኳ ቀደም ሲል እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ገብተው ያልተመለሱ ከ1ሺህ በላይ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እያሉ፤ መንግሥት ሌሎች ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ እርዳታ እንዲያደርሱ መፍቀዱን እና ወደ ትግራይ የእርዳታ አቅርቦት እንዳይገባ ዋነኛው እንቅፋት የሆነው ህወሓት መሆኑን ገልጿል። በዚህም በዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለቤትነት ሥር ያሉ 118 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በሙሉ አቅማቸው በእርዳታ ማጓጓዝ ሥራ እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ሾፌሮችም ሙሉ የደኅንነት ዋስትና እንዲያገኙ መንግሥት ማድረጉን አመልክቷል።

ህወሓት ግን በሁሉም አቅጣጫ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ በመንግሥት ተጥሏል ያለውን እገዳ ለማስነሳት ጦርነቱን ወደ አጎራባች ክልሎች ማስፋፋቱን ሲናገር የነበረ ሲሆን፣ አሁንም እገዳው ባለበት መሆኑን በመጥቀስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ እየጠየቀ ይገኛል። የፌደራል መንግሥት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልሎች ውስጥ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ፣ ጦርነቱ በመባባሱ የእርዳታ አቅርቦት ላይ እንቅፋት ተፈጥሮ ቆይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የእርዳታ ድርጅቶች እና መንግሥታት የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ውስጥ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ያለምንም እንቅፋት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንዲያደረግ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያርቡ ነበር። በተያያዘም የዓለም የጤና ድርጅት መድኃኒቶችንና ሌሎች የህክምና መገለገያዎችን ወደ ትግራይ ለማስገባት በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ቢያቀርብም ያሰበውን እንዳላሳካ አስታውቋል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሰባት ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ከአንድ ዓመት በላይ በተጣለበት ዕቀባ ሰር በመቆየቱ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ አንደሆነ መናገራቸው ተዘግቧል። ነገር ግን “መንግሥት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው” በሚል በህወሓት በኩል የሚቀርበውን ክስ ተቀብለው የሚያስተጋቡ የዓለም ጤና ድርጅትን የመሳሰሉትን ዓለም አቀፍ ተቋማት ወቀሳ “በመንግሥት ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም ጤና ድርጅት ክስ በሰጠው ምላሽ ህወሓት የአማራና የአፋር ክልሎችን “በወረረበት ወቅት ሆስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ሲዘርፍና ሲያወድም ንጹሃንን ሲደፍርና ሲገድል” የቡድኑን ድርጊት አላወገዘም ሲል ወቅሷል። ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ያለችግር እንዲቀርብ ለማስቻል እየሠራ መሆኑንና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ሌሎች አካላት ህወሓት የሚፈጽመውን እርዳታን የማደናቀፍ ተግባር እንዲኮንኑ ጠይቋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች ባለፉት ወራት በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከ9.4 ሚሊዮን በላይ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ከአንድ ወር በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *