በዚህ ማጣቀሻ ውስጥ ግለሰቦች ግጭቶችን ሲዘግቡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ስናወራ ነበር፤ ሆኖም፣ የዜና ክፍሎች እና ሙሉ የዜና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ ግጭት አገናዛቢ ዘገባዎችን በተመለከተ የተደራጀ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ። ገንቢ ለውጥ ለማምጣት የሚፈልጉ የዜና ድርጅቶች የዘገባቸውን ጥራት በማሳደግ ለተደራሲዎቻቸውም ማራኪ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን እናምናለን። ክሪስ ቺናካ ግጭቶች በሚከሰቱባቸው ጊዜያት የዜና ክፍሎች ኃይላቸውን አሰባስበው አካላዊ እና ዕውቀታዊ ሀብታቸውን በማጣመር ለጉዳዩ ጥልቅ ሽፋን መስጠት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። በዜና ክፍል ውስጥ ምን ያህል ልምድ እንዳለ እና ይህንን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ በአፅንዖት ይናገራሉ። ባርባራ አሞን የሚከተለውን በማለት ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ፦

ጋዜጠኞች ከምንገምተው በላይ ብዙ ነገር ያውቃሉ… ከጋዜጠኞች ጋር ወጣ ካላችሁ የፈለጋችሁትን ሐሳብ በማምጣት መወያየት ትችላላችሁ፤ ምን ያህል መረጃ እንዳላቸው አይታችሁ ትገረማላችሁ። ግጭቶችን በተመለከተ ዘገባ የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፣ እናም መረጃዎቻቸውን በቀላሉ ያጋሯችኋል። በጣም ብዙ ያውቃሉ።

ክሪስ እንደሚጠቁሙት፣ ግጭቶች ሲከሰቱ፣ የዜና ክፍሉ አባላት በሙሉ ተሰብስበው ግጭቱ ምን እንደሆነ፣ እነማን ተሳታፊ እንደሆኑ እና እንዴት ግጭቱ ሊያድግ እንደሚችል ተነጋግረው ግንዛቤ መፍጠር አለባቸው። በዚህ ግንዛቤም ላይ ተመሥርተው፣ ግጭቱን እንዴት ሽፋን እንደሚሰጡት አሳታፊም፣ መረጃ ሰጪም በሆነ መንገድ ዕቅድ ሊያወጡ ይችላሉ። ልክ በስፖርት ጫወታዎች ላይ እንዳሉ ሁለት ተቀናቃኝ ወገኖች ከመመልከት ይልቅ፣ የዜና ክፍሉ የግጭቱን ዘገባ እንዴት መቅረፅ እንዳለበት መነጋገር አለበት። እነዚህ ስብሰባዎች ግጭቶቹን ከሥር ከሥር እየተከታተሉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች የዘነጓቸውን ታሪኮች መምረጥንም ሊያካትቱ ይገባል።  ይህ ሰዎች የሚፈልጉትን ዘገባ ለማሰናዳት ከመርዳቱም ባሻገር፣ ተደራሲዎቹ ስለግጭቶቹ አካሔድ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይረዳል።

በዚህ ማጣቀሻ ክፍል አንድ እና አራት የተሰጡትን መገልገያዎች በመጠቀም ግጭቶች እንዴት እንደሚያድጉ የዜና ክፍሉ ሊገመግም ይችላል። ጋዜጠኞች በዚህ ዘዴ ወደፊት ምን ሊከሰት እንደሚችል እና በውጤቱ ምን ዓይነት ነገር ሊኖር እንደሚችል እየተነበዩ ሊገመግሙ ይችላሉ። ይህንን ትንታኔ በማድረግ ጋዜጠኞች በግንዛቤ የተደገፈ ማነቃቂያ በመፍጠር ግጭቶቹ በቸልታ ከታለፉ እና ከተባባሱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ማመላከት ይችላሉ። ክሪስ የዜና ክፍሎች የግጨት ዘገባ ዕቅድ በማውጣት በቂ ጊዜ እንደማያሳልፉ ያምናሉ። ብሎም፦

ሰዎች ብዙም ስለሥራቸው አያቅዱም፣ ይህም በሥራቸው ውስጥ ይስተዋላል። ቀድማችሁ ካቀዳችሁ ብዙ ታሪኮች ይኖሯችኋል፤ ምክንያቱም የት እንዳላችሁ፣ ወዴት እንደምትሔዱ፣ እና እነማን አብረዋችሁ እንደሚሆኑ አስቀድማችሁ ታውቃላችሁ። ይህ ዐቢይ ድክመት ይመስለኛል።

ከክሪስ ጋር በማቀድ ጉዳይ በመሥማማት፣ ግጭቶቸን ሽፋን ለመስጠት በጋራ የመስራትን ጥቅም በአፅንዖት ይገልጻሉ። ጋዜጠኞች ብዙ ጊዜ ግጭቶችን ሽፋን ከሰጡ በኋላ ግጭቶቹ ሲፈቱ ይዘነጉታል፣ ነገር ግን ከግጭቱ በኋላ የሆነውን ነገር የሚያሳይ ዘገባ መሥራት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። ቡድኖቹ የሆነ ነገር ለማድረግ በሆነ ቀነ ገደብ ተስማምተው ከነበረ፣ ጋዜጠኞቹ በነዚህ ሥምምነቶች መሠረት አቅደው ተከታይ ዘገባ መሥራት መቻል አለባቸው። ባርባራ ከዚህ በተጨማሪም ግጭቶች ባደረሷቸው ጉዳቶች እና ባሳደሯቸው ዘላቂ ተፅዕኖዎች ላይ ሥራ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል። እንዲሁ በደረቁ ቁጥሮችን እና ኪሳራዎችን ከመግለጽ ይልቅ፣ በዚያ ገንዘብ ምን ያህል ቤቶች ሊገነቡ እንደሚችሉ፣ ምን ያህል ልጆች በዓመት ሊመገቡ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምሣሌዎችንም መጠቀም መልካም ነው።

ክሪስ በዜና ክፍሎች ውስጥ ያሉትን ፉክክሮች ባይክዱም፣ ሐሳቦችን እና መረጃዎችን መለዋወጥ ግን ለሁሉም ጠቃሚ እንደሆነ ያሠምሩበታል። ዘጋቢዎች ዘገባቸውን እንደ አንዳቸው ሲያተርፉበት፣ ሌላኛቸው የሚከስሩበት ዜሮ-ድምር ውጤት አድርገው መመልከት አለባቸው ይላሉ። ይልቁንም፣ የዕቅድ ሒደቱ ሁሉንም የተሻለ እና ውጤታማ ሥራዎችን እንዲሠሩ በማገዝ፣ የጣምራ ውጤቱ የሁሉንም የሥራ ልምድ ያሳድገዋል። በዜና ክፍሉ ውስጥ ስኬታማ መሆን በራሳችሁ ሥራ ብቻ ሳይሆን በዜና ክፍላችሁ ስኬትም ይታያል።

ብዙ ጋዜጠኞች በየለቱ ዜና የማድረስ ሥራ መሐል እንዲህ ዓይነት ስብሰባዎችን ማድረግ እንደማችሉ ይናገራሉ። የእኛ አርትዖት ቡድን እነዚህ ስብሰባዎች ሰዓት ቆጣቢ መሆናቸውን ይናገራል። ጋዜጠኞች ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ፣ ሰዎች እንዲያፈላልጉ እና እርስበርስ ችግር የሚያቀል ጥቆማዎችን እንዲለዋወጡ ያስችሏቸዋል። ቡድናችን ከእትም እትም ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የዜና ክፍሎች ሥራቸውን የሚገመግሙበት ባሕል መኖር አለበት።

የአርትዖት ቡድኑ የሠራተኞቻቸውን የግጭት አዘጋገብ ዕውቀት በየጊዜው ማሳደግ አለባቸው ብሎ ያምናል። በጥቆማቸው፣ የዜና ክፍሎች መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ – ማለትም እንደ ግጭት አፈታት ሒደት፣ የሽምግልና ስርዓት፣ በኅብረተሰብ ጤና ላይ የግጭቱ ተፅዕኖ፣ ወዘተ. ጉዳዮች ማብራሪያ የሚሰጣቸው ባለሙያ መጋበዝ አለባቸው ብለዋል። እንዲህ ዓይነት አነቃቂ ክርክሮች የዜና ክፍሉ አባላት ለጊዜው ዕምቅ የሆኑና በጊዜ ሒደት ሊፈነዱ የሚችሉ ግጭቶችንም መለየት ያስችሏቸዋል።

ሰብአዊ ደኅንነት

ይህ ማጣቀሻ፣ ሕይወታቸውን የዓለም ዐቀፍ እና የእርስ በርስ ጦርነቶች እና ነውጥ አዘል ግጭቶችን ለመዘገብ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን የሰጡ ጋዜጠኞችን አብርክቶ ዕውቅና ይሰጣል። እነዚህ ጋዜጠኞች የነውጦችን አስቀያሚ ገጽታ የተመለከቱ ምሥክሮች ናቸውና መደበኛ እና አማፂ ታጣቂዎችን፣ የፖለቲካ ንቅናቄዎችን እና መንግሥታትን ለሥራዎቻቸው ተጠያቂ በማድረግ ወሳኝ ሚና አላቸው።

እነዚህ ጋዜጠኞች ብዙውን ጊዜ በእንደዚህ ዓይነት ነውጦች ውስጥ መትረፍ የሚያስችሏቸውን ሥልጠናዎች እና መከለከያ ቴክኖሎጂዎች አሏቸው። ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ግን ብዙውን ጊዜያቸውን በጦርነቶች መሐል፣ ከጥይቶች ተደብቀው፣ በአማፂ ቡድኖች መሐል እየተንቀሳቀሱ የመሥራት ልምዱ የላቸውም። በግጭት ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው አያውቁም። ይህንን ለማድረግ የሚያስችሏቸው የደኅንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶችም የሏቸውም።  ሆኖም ግን ብዙ ጊዜ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን ያገኛሉ።

ከዚህ የበለጠ ጥልቅ ምክር የሚፈልጉ ጋዜጠኞች በዚህ ማጣቀሻ ክፍል 2.5 የተሰጡትን ምክሮች መመልከት እና ሌሎችም ከፍተኛ ነውጦች የሚስተዋሉባቸው ጦርነቶችና ግጭቶች ውስጥ ዘገባ የሠሩ ጋዜጠኞችን ምክር መጠየቅ ይችላሉ። የሚከተሉት ነጥቦች በአደገኛ ቦታዎች ዘገባ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ሊወስዷቸው የሚገቡ የደኅንነት ጥንቃቄዎችን የሚያሳዩ ሲሆን፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ እነዚህ ምሉዕ አይደሉም፦

  • የራሳችሁ ምርጫ ነው። ማንም አርታኢ ወይም ቀጣሪ ሕይወታችሁን አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል ቦታ እናንተን አስገድዶ የመላክ መብት የለውም። በዚህ ረገድ በጦር ቀጠና እየሠሩ ያሉ ጋዜጠኞችን ደኅንነት በተመለከተ እየሠሩ ያሉት የሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ24F ጋዜጠኞች “ያለ ገለጻ እና ያለ ሙያዊ ሥነ ስርዓት.. የሚሰጣቸውን ሥራ ያለመቀበል መብት አላቸው።” በማለት ይገልጻሉ። ጋዜጠኞቹ ሁሌም ሁኔታውን ለመግምገም ትክክለኛዎቹ ሰዎች ስለሆኑ፣ የመጨረሻው ውሳኔ በነርሱ መወሰድ አለበት።
  • አደገኛ ወደ ሆነ ቦታ ልትሔዱ ከሆነ፣ የዜና ክፍል ኃላፊው የትና መቼ እንደምትሔዱ እና እንደምትመለሱ ይወቁ። የዕቅድ ለውጥ ካለም አሳውቁ። ይህ የሚረዳው ባልደረባዎቻችሁ በታቀደው ጊዜና ቦታ መገኘት ባትችሉ ሊደርሱላችሁ ስለሚችሉ ነው። ነገር ግን ስለ እንቅስቃሴያችሁ ቶሎ ቶሎ መረጃ የማትሰጧቸው ከሆነ በምንም ዓይነት መልኩ ለመርዳት ይቸገራሉ። በነውጦች መካከል ነገሮች ቶሎ ቶሎ ይለዋወጣሉ። እናንተም ሳታስቡት ግጭቶቹን እየተከታተላችሁ ጭልጥ ብላችሁ መሐል ልትገቡ ትችላላችሁ።
  • ሰዎች ለሚዲያ ያላቸውን ምላሽ በቅጡ አስተውሉ። አንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ጋዜጠኞች ይፈለጋሉ፣ ምክንያቱም ባለሥልጣናት ጋዜጠኞች ባሉበት ያልተመጣጠነ እርምጃ አይወስዱም። በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ ሰዎች ጋዜጠኞችን ሊጠሉ ይችላሉ። ምልክቶቹን አስተውሉ። ከፍ ያለ የሚዲያ ጥላቻ ካስተዋላችሁ ተጠንቀቁ።  በግርግር ውስጥ ያሉ ሰዎች በደኅናው ጊዜ የማያደርጉትን ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። መለያ ዕውቅናችሁን ያዙ ነገር ግን ማሳየት እንዳለባችሁ እና እንደሌለባችሁ ብልሐት የተሞላበት ውሳኔ አድርጉ።
  • ችግር ውስጥ ከገባችሁ፣ ግጭቱ ውስጥ የተሳተፉትን አካላት አመራሮች አውቃቸዋለሁ ማለት ሊረዳችሁ ይችላል። የስልክ ቁጥራቸውን መያዝ እና መደወል መቻል ከእንደዚህ ዓይነት አሳሳቢ ሁኔታዎች ሊያድናችሁ ይችላል። የአካባቢው ፖሊስ እና የመከላከያ ኃላፊዎች ቁጥር መያዝም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ችግር ከገጠማችሁ ሊረዳችሁ ይችላል።
  • ከመውጫ መግቢያው ጋር ራሳችሁን በማላመድ ነገሮች ገጽታቸው ቢከፋ በየት በኩል መውጣት እንደምትችሉ አውጠንጥኑ። አንደኛው መውጫ መንገዳችሁ ቢዘጋ የምትወጡበት ቢያንስ አንድ አማራጭ መንገድ አዘጋጁ። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ በተዘዋወራችሁ ቁጥር መውጫ አማራጮቻችሁን እና የነውጡን ሁኔታ ደጋግማችሁ አስቡ።
  • ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር አብራችሁ ቆዩ። ብዙ ዘጋቢዎች ብቻቸውን ሲሆኑ የደረሱባቸውን ብዙ ችግሮች ይናገራሉ። ከቡድኑ ጋር መቆየት ብዙም ደስ ላይላችሁ ይችላል ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይህ ደኅንነታችሁን ያስጠብቅላችኋል።
  • በጥሩ ሁኔታ ልበሱ። ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ሊያመሳስላችሁ የሚችሉ ቀለማትን ያሏቸውን ልብሶች አትምረጡ። የፖለቲካ ቲሸርቶችን ወይም የፀጥታ ኃይሎች መለዮዎችን የሚመስሉ ልብሶች አትልበሱ። እነዚህ ሁሉ አልባሳት ዒላማ ሊያስደርጓችሁ ይችላሉ። ለመሮጥ የሚያስችል ጫማ አድርጉ፣ ከተፈጥሯዊ ክሮች የተሠሩ ልብሶች አነስተኛ የመቀጣጠል ዕድል ስላላቸው ጥሩ ናቸው።
  • የሚከተሉትን የያዘ ትንሽ የጀርባ ሻንጣዎችን ይያዙ፦
  • ቁሳቁሶቻችሁን
  • ተቀያሪ ባትሪ
  • የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ መስጫ፣ ፋሻ፣ የቁስል ማጠቢያ እና ፕላስተር
  • ውኃ እና ቻርጀር
  • የባትሪ መብራት
  • ንፁሕ ጭንቅላት  የመጨረሻ  መተማመኛችሁ  ነው።  አለበለዚያ  ሳይረፍድባችሁ  ቶሎ ውጡ። ንዴታችሁን በሁሉም ሁኔታ ተቆጣጠሩ፣ በፍፁም በአካላዊም ይሁን ቃላዊ የነውጥ ድርጊት አትሳተፉ።
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *