የኢትዮጵያ መንግሥት በእስር ላይ የቆዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ ቀርቦባቸው የነበረውን ክስ በማቋረጥ ከእስር ቤት እንዲወጡ ማድረጉን ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች ድጋፍና ተቃውሞ እየተሰነዘረ ነው።

ባለፈው አርብ የገና በዓል ዕለት ከእስር እንዲወጡ የተወሰነላቸው ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት በአርቲስት ሃጫሉ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው ሁከት ሳቢያ የታሰሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እንዲሁም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ናቸው። በተጨማሪም ከአንድ ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ አስካሁን መቋጫ ያላጋኘውን ጦርነት ተከትሎ የተያዙት ስድስት የቀድሞ የህወሓት አመራሮች ይገኙበታል።

ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ በእስር ላይ ከነበሩት መካከል በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በእነ አቶ እስክንድር ነጋ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው እንዲነሳ የተደረገው “አገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ” እንደሆነ የፍትሕ ሚኒስቴር ገልጾ፣ አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ ስድስቱ የህወሓት አባላት ክሳቸው የተነሳው ደግሞ በጤናና በዕድሜ ሁኔታ መሆኑን አምልክቷል።

የመንግሥትን ውሳኔውን በተመለከተ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልክና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በአገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት” መሆኑን ገልጿል። ይህ የመንግሥት ውሳኔ ከተለያዩ ወገኖች የተለያየ ምላሽን አግኝቷል። እርምጃውን በአዎንታ በመመልከት ድጋፋቸውን የሰጡ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል የተቃወሙትም አሉ። ከአገሪቱ ዜጎች በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የአህጉራዊና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችም በመሪዎቻቸው በኩል በመንግሥት ውሳኔ ዙሪያ መግለጫን አውጥተዋል።

እናት ፓርቲ

እናት ፓርቲ በመግለጫው እርምጃውን “ሕጋዊ ሂደትን ባልጠበቀና በማን አለብኝነት ውሳኔዎችን መወሰንና ተግባራዊ ማድረግ የገዢው ፓርቲ አሠራር ሆኖ ቆይቷል፤ አሁንም እየሆነ ነው” ሲል ተችቷል። እናት ፓርቲ የትኛውም አካል፣ የሀገር መሪዎችን ጨምሮ፣ ሁሉም ሰው ከሕግ በታች መሆኑ ግልጽ ጉዳይ ነው ካለ በኋላ፣ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብም ይሁን ድርጅት ሕጋዊ ሂደትን ሳይጠብቅ “ክስ በማቋረጥ” ማሰናበት “በሕግ ተቋማት ሥራ ላይ ያለውን ጣልቃ ገብነት ከማሳየቱም ባሻገር የፈላጭ ቆራጭነት ማሳያ” ነው ብሏል።

በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ወንጀል የፈጸሙ፣ የአካል ጉዳት ያደረሱ፣ ንብረት ያወደሙ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራ እና አፋር ሕዝቦችን ያፈናቀሉና ለትግራይ ሕዝብ ለአሥርት ዓመታት በሰቆቃ ሕይወት መኖር ተጠያቂ የሆኑ፣ እናቶችና ሕጻናት እንዲደፈሩ ያደረጉ አመራሮች ላይ ኢሕጋዊ በሆነ ሁኔታ ታኅሣሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም የተወሰነው ውሳኔ የፓርቲውን አምባገነንነት የሚያሳይ ነው ሲል እናት ፓርቲ ተችቷል።

እናት ፓርቲ በመግለጫው ላይ ከብዙ ታሳሪዎች መካከል ” በእድሜ የገፉ ስለሆነ ” በሚል ምክንያት የተለቀቁትን የህወሓት አመራሮች በሚመለከትም፣ “ሀገር ለሕልውና እያደረገች ያለውን ጦርነት ዓላማ የሳተ፣ የሕግ አሠራር ሂደትን የጣሰ፣ በግለሰቦችና ገዢው ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ዜጎች የሚታሠሩበት እና የሚፈቱበት መሆኑን ማሳያ” ነው ብሎታል።

ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በበኩሉ ታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በሕግ ጥላ ስር የነበሩ ሰዎች በክስ ማቋረጥ የተለቀቁት “በእነሱ አነሳሽነት የተቀጠፉ ሕይወቶች ቁስል ባልሻረበትና የወደሙ አካባቢዎች እስካሁን ባላገገሙበት ሁኔታ ነው” ሲል በመግለጫው ላይ ልጿል። የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ ተበዳይ ፍትህ ሳያገኝ እንዲሁም ሳይካስ በዳይን ነፃ ማውጣት “በፍትሕ ሥርዓቱ መቀለድ፣ የሕዝባችንን ጉዳትም ማቃለል ነው” ካለ በኋላ “እንደዚህ በጥድፊያ የሚደረጉ ውሳኔዎች ፍትህን በመጨፍለቅ በተቋማቱ ላይ ያለንን እምነት በሂደት የሚሸረሽሩ ናቸው” ብሏል።

በተጨማሪም የፖለቲካ እስረኞቹን የተፈቱበትን መንገድ የሕዝብ ምክክር የጎደለው መሆኑን ጠቅሶ፣ “ግብታዊ እርምጃ የአገር ባለቤትነትና መብትን ለአመፀኛው፣ የፈለገው ነገር እስካልተፈፀመ ድረስ አገር ብትጠፋ ከቁብ ለማይቆጥረውና የሕዝቧ ስቃይ ግድ ለማይሰጠው ኃይል አሳልፎ ይሰጣል” ሲል አስፍሯል። ኢዜማ አክሎም “አመፀኝነትን የሚያበረታ እና መከፋፈልን የሚያጠነክር እጅጉን አሳሳቢ ተግባር ነው” ሲል የተቸ ሲሆን፣ “የፍትህ ሥርዓቱም በደመነፍስ ከመሰራት ተሻግሮ ለዜጎች ፍትህን የሚያሰፍን ሆኖ ሊደራጅ ይገባዋል” ሲል መክሯል።

የተባበሩት መንግሥታ፣ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን ከእስር በመልቀቅ የወሰደውን እርምጃን በተመለከተ ምላሽ በመስጠት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የመንግሥትን እርምጃ ያደነቁት ጉቴሬዝ፣ መንግሥት በወሰደው “መተማመንን በሚገነባ ታላቅ እርምጃ ላይ ሁሉም ወገኖች የበኩላቸውን ምላሽ በመሰጠት ግጭቶችን በማቆም ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ” እንዲሁም ተአማኒና ሁሉን አካታች ብሔራዊ የምክክርና የእርቅ ሂደት እንዲጀመር ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት፣ ሙሳ ፋኪ ማሐማት

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት በኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ የነበሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መፈታታቸውን በመስማታቸው ደስ እንደተሰኙ ገልጸው፤ ይህም በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታን ለማስተካከል ወሳኝ እርምጃ ነው ብለውታል። ጨምረውም እርምጃው ኢትዮጵያን ለገጠማት ፖለቲካዊና ተቋማዊ ችግሮች ሰላማዊ እና አግባቢ ስምምነት ለማምጣት የሚያስችል ሐቀኛ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክር ሂደትን ለማስጀመር የመነሻ ነጥብ ይሆናል ብለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት፣ ጆሴፍ ቦሬል

የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው የተቃዋሚ ፖለቲከኞች መፈታትና ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለማብቃት አዎንታዊ እርምጃ ነው ብለዋል። ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ማንንም ያላገለለ ነጻና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ብቸኛው አማራጭ መሆኑን የአውሮፓ ሕብረት ሁልጊዜም ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሁሉም ወገኖች ግጭት ለማስቆም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ውይይት እንዲገቡ ቦሬል ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሕብረቱ ይህንን ሂደት ለመደገፍ ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *