ከቀናት በፊት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የወጡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራሮች ‘በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እየተካሄዱ ያሉት ጦርነቶች’ በሰላማዊ ድርድር መፍትሔ ይሰጣቸው ሲሉ ጠየቁ።

አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ በፓርቲው ገጽ ላይ በወጣ መግለጫቸው፤ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ “በተሳሳተ መንገድ ለእስር ተዳርገው” ላለፉት 18 ወራት በእስር መቆየታቸውን አስታውሰዋል። እስራችን “ፖለቲካዊ” ነበር ያሉት ፖለቲከኞቹ፤ ለእስር የተዳረግነው ገዢው ፓርቲ በምርጫ የተሻለ ድምጽ እንዲያገኝ ከፖለቲካዊው ምኅዳር ገለል እንድንል ታስቦ ነው ብለዋል። በእስር በቆዩባቸው ጊዜያት በአገሪቱ በርካታ አሉታዊ ለውጦት መከሰታቸውን ጠቅሰው፤ ክስተቶቹ የነበረውን የዲሞክራሲ ሽግግር ተስፋን ከማጨለማቸው በተጨማሪ፤ አገሪቱን ወደ አስከፊ የእርስ በእስርስ ጦርነት ከተዋታል ብለዋል።

ጃዋር መሐድም እና በቀለ ገርባ፤ በኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በሲቪሎች ላይ የደረሰው ጉዳት አሳዛኝ ነው ብለዋል። ባለፉት 13 ወራት በአገሪቱ እና በሕዝቦቿ ላይ የደረሱትን ጉዳቶችን መቀልበስ ባይቻልም፤ ተጨማሪ ጉዳቶችን ማስቀረት የምንችልበት ጠባብ ዕድል አለ ብለዋል። ይህ ተፈጻሚ እንዲሆን በቅርቡ መንግሥት ሰላም እና መግባባትን ለመፍጠር ያሳየው አዎንታዊ ምላሽ ተጨባጭ እና በማይቀለበሱ ተግባራት መረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።

“በኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች” በሰላማዊ ድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት እስኪደረስ ድረስ ሁሉም ተዋጊ አካላት ንጹሃን ዜጎችን እና መሠረተ ልማቶችን እንዲጠብቁ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የእርስ በእስር ጦርነት በሰላም እንዲጠነናቀቅ እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋገት እንዲሰፍን የውጭ አካላት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱም ጠይቀዋል። በቀይ ባሕር አካባቢ ያሉ አገራት እና ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ጦርነቱን ለማስቆም ተዋጊ አካላት ለድርድር እንዲቀመጡ በአንድ ድምጽ ጫና ማሳደር አለባቸው ብለዋል።

ፖለቲከኞቹ ጨምረውም የውጭ አካላት ለተዋጊ አካላት ፖለቲካዊ እና ቁሳዊ ድጋፎችን በማቅረብ ግጭቱን ከማባባስ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። የአገሪቱ ሕዝብ ወታደራዊ ጥሪዎችን እንዳይቀበል፤ መገናኛ ብዙኃንም የአንድ ወገን ትርክቶችን እና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳዎችን ከማስተላለፈ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል። በመጨረሻም ፖለቲከኞቹ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን በተመለከተ ተዓማኒነት ያለው ምርመራ እንዲደረግ፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ተይዘው ለአንድ ዓመት ለስድስት ወር በአስር ላይ የቆዩት ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮችና አባላት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እያታየ እንደነበር ይታወሳል። አገራዊ መግባባትን ለማጎልበትና አንድነትን ለማጠናከር በሚል መንግሥት በወሰደው እርምጃ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ ግለሰቦች ላይ የቀረበው ክስ ተቋርቶ ከእስር የተፈቱት ባለፈው አርብ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም ነው።

ፍትሕ ሚኒስቴር ይህንን ውሳኔ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እርምጃው በቀጣይ የሚደረገውን “አገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ” መሆኑን አመልክቷል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *