ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ ሰዎችን ክስ በማቋረጥ ከእስር እንዲለቀቁ በመንግሥት በኩል የተደረሰው ውሳኔ ቁጣን የቀሰቀሰ መሆኑን እና መወሰድ የነበረበት እርምጃ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለአገራዊ መግባባት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር በሚል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች አመራሮችና አባለት እንዲሁም የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ክስ ተቋርጦ ከእስር እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የአንዳንዶቹን ከእስር መለቀቅ በተመለከተ ከተለያዩ ወገኖች ተቃውሞና ጥያቄ ሲቀርብ ተሰምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት እሁድ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው አዲሱ የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በመንግሥት ውሳኔ ላይ የተሰማውን ተቃውሞ አንስተው ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጉዳይ “እኛንም መጀመሪያ ስንሰማው ያስደነገጠ ነው” በማለት፣ “ነገር ግን ቀኙን ስንፈትሽ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የሚያግዝ፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች የሚቀንስ፣ በአውደ ውጊያ ያገኘነውን ድል በሰላሙ መድረክ እንድንደግም የሚያደርግ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሸነፉ ያሏቸው ኃይሎች “ክስ እንዲቋረጥ እና ከእስር ቤት እንዲወጡ ሲደረግ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል” በማለት ይህም ቁጣ ከሁለት ወገኖች መሰንዘሩን ጠቅሰዋል። አንደኛው ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሲኖር የማይደሰቱ ያሉት ሲሆን፣ “የት እንዳሉ የማይታወቁ . . . አጓጉል ብልጣብልጥነት የሚያጠቃቸውና እምብዛም ጆሯችንን የማንሰጣቸው” በማለት አጣጥለዋቸዋል።

ሁለተኛው ቡድን ደግሞ በዜናው ድንገተኝነት የደናገጠ “ለአገሩ ሁሉን ነገር ያበረከተ . . . ይህንን እኩይ ጠላት አምርሮ የሚጠላ እና ከዚህ ጠላት ጋር የሚደረግ ማንኛውም ንግግር ኢትዮጵያን ይጎዳል ብሎ የሚያምን ቅን ተቆጪ ነው” በማለት ይህንን ወገን መንግሥታቸው “ሙሉ በሙሉ ይረዳል፣ ያደምጣል፣ ለማስገንዘብም ጥረት ያደርጋል” ብለዋል።

መንግሥታቸው ይህንን ውሳኔ ለአገር ሲል የተቀበለው መሆኑን ለማመልከት “እየመረረን የዋጥነው እውነታ ነው” ሲሉ ገልፈው፣ በሁለተኛው ወገን ውስጥ ያሉ ዜጎችን “እናንተም ለአገራችሁ ዘላቂ ድል ስትሉ፣ ለአገራችሁ ክብር እና አሸናፊነት ስትሉ ደጋግማችሁ በማሰብ ይህን ውሳኔ እንድትቀበሉ በትህትና ጠይቃችኋለው” ብለዋል። ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ቤት እንዲፈቱ የተደረጉት ግለሰቦችን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፣ ግለሰቦቹ የመንግሥት ሥልጣን ይዘው የተሳተፉ፣ በቀጥታ የሚወስኑ፣ በቀጥታ የሚያዙ እንዳልሆኑ በመግለጽ “አዛውንቶች ሲቻል ወደ ገዳም፣ አልያም ወደ ቤታቸው እንጂ በእስር ቤት እንዳይቆዩ ወስነናል” ብለዋል።

ጨምረውም መንግሥታቸው ክስ የተቋረጠላቸው ግለሰቦችን ይቅር ማለት የመረጠው ከጀርባቸው ያለውን ሕዝብ በማክበር በመሆኑ በተፈጠረው እድል በአግባቡ እንዲጠቀሙበት፣ ነገር ግን “ክስ ማቋረጥ ማለት ምህረት መስጠት አይደለም በአግባቡ ካልተጠቀሙበት መልሶ የክስ መዝገቡን ሊመዘዝ ይቻላል” ብለዋል። ባለፈው አርብ ከእስር እንዲወጡ የተወሰነላቸው ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እንዲሁም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም፣ ከአንድ ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ እስካሁን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ስድስት የቀድሞ የህወሓት አመራሮች ይገኙበታል።

ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ በእስር ላይ ከነበሩት መካከል በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በእነ አቶ እስክንድር ነጋ መዝገብ ውስጥ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው እንዲነሳ የተደረገው “አገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ” እንደሆነ የፍትሕ ሚኒስቴር ገልጾ፣ አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ ስድስቱ የህወሓት አባላት ክሳቸው የተነሳው ደግሞ በጤናና በዕድሜ ሁኔታ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል። የመንግሥትን ውሳኔ በተመለከተ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልክና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በአገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት” መሆኑን ገልጿል። ይህን የመንግሥት ውሳኔ በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦች የተሰነዘሩ ሲሆን በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተቃውሟቸውንና ድጋፋቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *