በኢትዮጵያ የተከሰቱ ሁለት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቀውሶችን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ የቆዩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች እንዲፈቱ መወሰኑ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም ይፋ ተደርጓል።
በገና ዕለት አመሻሽ ላይ የፖለቲከኞቹ የመፈታት ዜና ከመሰማቱ በፊት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይቅርታና ምህረትን በተመለከተ “ድላችን ዘላቂ ለማድረግ እንድንችል በአሸናፊ ምህረት ግጭቱ የፈጠረውን ውጥረት እናረግባለን” በማለት ፍንጭ የሚሰጥ መግለጫ አውጥተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም “ያጠፋ እንዲቀጣ፣ የበደለ እንዲክስ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ፍትሕ በሽግግር እና በተሃድሶ ፍትህ ዕይታ፣ አገራዊ ባህሎቻችን እና እሴቶቻችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ፍትህ እናሰፍናለን” ብለዋል።
በማስከተልም አመሻሽ ላይ መንግሥት በኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቱ በኩል ስለውሳኔው መግለጫ ቢያወጣም፣ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ የተለያየ ምላሽን እያስተናገደ ከመሆኑ በተጨማሪ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል። የምህረት ውሳኔውን በተመለከተ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት “ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች” በሚል ባወጣው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ችግሮችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ መፍታት እንደሚገባ መንግሥት በጽኑ እንደሚያምን አመልክቷል።
ለዚህም መንግሥት አካታች አገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከሚጠበቅበት ሞራላዊ ግዴታዎች አንዱ ምህረት መሆኑን በመጥቀስ “ለተሻለ ፖለቲካዊ ምኅዳር ሲባል የተወሰኑ እሥረኞችን መንግሥት በምህረት ከእሥር ፈትቷል” ብሏል። ይህ ምህረት ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሠሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን እንደሚጨምርም ጠቅሷል።
ጨምሮም የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና ለአካታች አገራዊ ምክክር ሲባል በምህረት የተፈቱት ግለሰቦች “ካለፈው የጥፋት መንገድ ተምረው፣ የተሻለ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ በማድረግ፣ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ይክሳሉ” ብሎ መንግሥት እንደሚያምን ተገልጿል። መንግሥት ይህንን ውሳኔ የወሰነው “የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልህና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በአገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት” መሆኑን ጠቅሶ፤ ለዘመናት የቆዩ ፖለቲካዊ ችግሮችን በአካታች ምክክር ለመፍታት እንዲቻል መንግሥት ገለልተኛ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝም አስታውሷል።
የፍትሕ ሚኒስቴር በበኩሉ ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥት እና የሽብር ችሎት እየታየ ከነበሩት መካከል በእነጃዋር መሐመድ እና በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው እንዲነሳ መደረጉን አሳውቋል። ለዚህም ምክንያቱ በቀጣይ የሚደረገውን “አገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ” መሆኑን አመልክቷል።
በተጨማሪም የጤና እና የዕድሜ ሁኔታቸውን ከግምት በማስገባት በእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ የተከሰሱ ስድስት የህወሓት አባላትና አመራሮች ክሳቸው እንዲነሳ መደረጉን የፍትሕ ሚኒስቴር ገልጿል። ለመሆኑ እነዚህ ከእስር እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው ግለሰቦች እንማን ናቸው? በአጭሩ እነሆ. . .
ጃዋር መሐመድ
አቶ ጃዋር መሐመድ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ከሚጠቀሱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ ለበርካታ ዓመታት በውጭ አገር ቆይተው ወደ አገር የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ነበር። በውጭ አገር ቆይታቸው በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ተቃውሞ በመምራትና በማስተባበር ጉልህ ሚና የነበራቸው አቶ ጃዋር ኦኤምኤን የተባለውን የሳተላይት ቴሌቪዥን በማቋቋምና በመምራት ጉልህ ሚና ነበራቸው።
ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ወደ ፓርቲ ፖለቲካ ለመግባት በመወሰናቸው፣ ከመታሰራቸው ጥቂት ወራት ቀደም ብለው የነበራቸውን የአሜሪካ ዜግነት መመለሳቸው ይታወሳል። በዚህም በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ወደ’ሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመግባት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረው የነበረ ሲሆን፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ በነበረው ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ ነበር።
ምርጫው ከተራዘመ በኋላ በ2012 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል። በወቅቱም በአቶ ጃዋር መዝገብ ስር ከ20 በላይ ሰዎች የፀረ ሽብር አዋጅን፣ የቴሌኮም አዋጅን፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመተላለፍ ክስ ተመስርቶባቸው፣ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ከአንድ ዓመት በላይ ቆይቷል።
አቶ ጃዋር በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ የተለያዩ የጤና እክሎች አጋጥሟቸው እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት ደግሞ እስራቸውን በመቃወም የረሃብ አድማ አድርገው የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በመድረሱ ሆስፒታል እስከመግባት ደርሰው እንደነበር ይታወሳል።
በቀለ ገርባ
አቶ በቀለ ገርባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩ ሲሆን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባልና ከፍተኛ አመራር ሲሆኑ በአቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ሥር ተመሳሳይ ክስ ከቀረበባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው። አቶ በቀለ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት ከሚያደርጉት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተይዘው ለበርካታ ዓመታት በእስር ቤት ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከእስር የተለቀቁት አቶ በቀለ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በእስር ቆይተው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት ጊዜ ነው የተለቀቁት።
አቶ በቀለ በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ ከአቶ ጃዋርና ከሌሎች ጋር መታሰራቸውን በመቃወም የረሃብ አድማ አድርገው የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በመድረሱ ሆስፒታል እስከ መግባት ደርሰው ነበር።
እስክንድር ነጋ
አቶ እስክንድር ነጋ ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በነበረው አስተዳደር ከጋዜጠኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በእስር ላይ ቆይተዋል። አቶ እስክንድር የተለያዩ ጋዜጦችን በማዘጋጀትና በማሳተም የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ሲሆን መንግሥትን በመተቸትም ይታወቃሉ። በዚህም ሳቢያ በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉ ሲሆን ለረጅም ጊዜ በእስር ከቆዩ በኋላ ነበር ከሦስት ዓመት በፊት ነጻ የወጡት።
አቶ እስክንድር በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ ተካሂዶ ከእስር እንደወጡ ወደ ጋዜጠኝነት ሥራቸው ተመልሰው ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ፣ በተለይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባለውን ፓርቲ መስርተው ሲመሩ ቆይተዋል። ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ እስክንድር የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍና ኃይልን በመጠቀም መንግሥትን ለመቆጣጠር ሙከራ በማድረግ ተከስሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።
አቶ እስክንድርና አብረዋቸው የታሰሩ የፓርቲያቸው አባላት ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ፣ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበው ተቀባይነት አግኝተው ነበር። በዚህም ቀደም ሲል ባልታየ ሁኔታ አቶ እስክንድርን ጨምሮ የባልደራስ ፓርቲ አመራሮች እስር ቤት ሆነው በምርጫው ዕጩ ሆነው በመቅረብ ለመወዳደር ቢችሉም ሳይመረጡ ቀርተዋል።
በተጨማሪም አቶ እስክንድር በእስር ቤት ሳሉ በአንድ እስረኛ ጥቃት እንደደረሰባቸው የተነገረ ሲሆን ጉዳዩን ለፍርድ ቤትና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አቅርበው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው ነበር። አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ የተባሉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም ከእስር ተለቅቀዋል።
አስቴር ስዩም
በኬሚስትሪ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ የሆነችው ወጣቷ ፖለቲከኛ ቀለብ (አስቴር) ስዩም ከዓመታት በፊት የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) የሰሜን ጎንደር ዞን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ታደርግ ነበረ። ከለውጡ በፊት በነበረው የኢህአዴግ አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎች ተይዛ በሽብር ወንጀል ተከስሳ አራት ዓመታትን በማዕከላዊና በቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ ተፈርዶባት ቅጣቷን ጨርሳ ወጥታለች።
የሁለት ልጆች እናት የሆነችው አስቴር ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሲመሰረት ፓርቲውን ተቀላቅላ በአመራርነት እያገለገለች የነበረ ሲሆን ሌሎቹ የፓርቲው አመራሮች በታሰሩበት ክስ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ በእስር ላይ ቆይታ ነው አሁን የተፈታችው።
አስቴር ‘ሀገር ስታምጥ’ እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥንና መሪዎችን የሚተች ‘የመሪዎች ሴራ በኢትዮጵያ’ የሚል መጽሐፍት ለንባብ አብቅታለች። አስቴር በተለያዩ ጊዜያት በፖለቲካዊ ተሳትፎዋ የተነሳ በእስር በቆየችበት ጊዜ በአጋጠማት አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሰቆቃ ምክንያት የተለያዩ የጤና እክሎች እንዳጋጠሟት ይነገራል።
ስብሐት ነጋ
የህወሓት መስራች የሆኑት እና ኢህአዴግን በመምራት ሥልጣን ከያዘ በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ቁልፍ ሰው የነበሩት አቶ ስብሐት ነጋ ባለፈው ዓመት በትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ መንግሥት ለግጭቱና ለቀውሱ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው በማለት የእስር ማዘዣ ካወጣባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ። ይህንንም ተከትሎ የ86 ዓመቱ አዛውንት አቶ ስብሐት ነጋ በኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ትግራይ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተነገረው የዛሬ ዓመት ታኅሣሥ 30/2013 ዓ.ም ነበር።
አቶ ስብሐት ህወሓትን ከመመስረት በተጨማሪ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩ ሲሆን፣ በኢህአዴግና በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው ፖለቲከኛ ነበሩ። አቶ ስብሐት ከፖለቲካው ባሻገር የህወሓት የምርትና የአገለግሎት ተቋማትን የሚያስተዳድረውና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ተቋማትን በስሩ የያዘው ኤፈርትንም መርተዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋምን ጡረታ እስከ ወጡበት ጊዜ ድረስ በዋና ዳይሬክተርነት መርተውት ነበር።
በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሲፈለጉ ከነበሩት የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች መካከል የሚገኙት አቶ ስብሐት፣ ባለፈው ዓመት ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ በሆነ ገደላማ አካባቢ ከባለቤታቸውና ከእህታቸው ጋር ተይዘው ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጡት። አቶ ስብሐት በአገር ክህደት፣ በትግራይ ይገኝ በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በማድረስና በመሳሪያ በታገዘ አመጽና ሁከት በማነሳሳት ወንጀሎች ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው እየታየ ነበር።
ቅዱሳን ነጋ
የህወሓት ነባር አባልና ከፍተኛ አመራር የነበሩት ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ በትግራይ ክልል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ከወራት በኋላ በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ስር የዋሉት ከወንድማቸው ከአቶ ስብሐት ነጋ ጋር ነበር። ወ/ሮ ቅዱሳን በህወሓት ውስጥ ካላቸው ሚና በተጨማሪ የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው ሠርተዋል። ባለቤታቸው አቶ ፀጋይ በርሄ የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን ከመሆናቸው በተጨማሪ የክልሉ ፕሬዝዳንት የፌዴራል መንግሥቱ ደኅንነት አማካሪ ነበሩ።
ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር
ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር የህወሓት አባል ሲሆኑ በፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አባል ከመሆናቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ከአንድ ዓመት በፊት በፌደራሉ ኃይሎች ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የነበረ ሲሆን አሁን እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው ግለሰቦች መካከል አንዷ ናቸው።
ሌሎች
ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ በርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በፌደራሉ የፀጥታ ኃይሎች መያዛቸው የሚታወቅ ቢሆንም አሁን በምህረት የሚለቀቁት ስድስቱ ብቻ መሆናቸውን ከመንግሥት በኩል የወጣው መግለጫ ያመለክታል። በዚህም መሠረት ከአቶ ስብሐት ነጋ፣ ከወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ ከወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር በተጨማሪ የቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አምባሳደርና የክልሉ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ አባዲ ዘሙና አቶ ኪሮስ ሐጎስ ይገኙበታል።
ምንጭ – ቢቢሲ